የቅዳሜ ከሰዓት ልዩ የሀገር ውስጥ እና ውጭ እግር ኳሳዊ ዜናዎች [በኢትዮአዲስ ስፖርት]


image
ፈይሰል ሀይሌ

ቅዳሜ መስከረም 21 ¦ ለኢትዮ አዲስ ስፖርት በፈይሰል ሀይሌ የቀረበ

➡ ዋልያዎቹ በቀጣይ ሳምንት የወዳጅነት ጨዋታ ያደርጋሉ
➡ አሌክሲስ ሳንቼዝ በፊት አጥቂነት ይዘልቅ ይሆን?
➡ ሆዜ ሞሪንሆ የሰርማት በዝቢን ሪከርድ ተጋርቷል
➡ ሊዪኔል ሜሲ መቼ ይመለሳል ?
➡ ዝላታን በማይክል ኦውን ተተችቷል
ከላይ የጠቀስናቸውን እና ቅዳሜ ቅዳሜ ብቻ በሚቀርቡ ልዩ ዜናዎች ተጨማሪ በሌሎች ሚዲያዎች ያልሰሟቸውን ምሽቶን መልካም የሚያደርጉ እግር ኳሳዊ ወሬዎችን ከአስገራሚ ቁጥራዊ እውነታዎች እና ይህን ያውቁ ኖሯልም አሰናድተናል፡፡ የሀገር ውስጥ ዜናዎችም ይኖሩናል፡፡

image የሀገር ውስጥ ዜና
  የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከታንዛንያ አቻው ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ያደርጋል   

🎄 የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከታንዛንያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የወዳጅነት ጨዋታ ጥሪ ቀርቦለታል፡፡ ጥያቄውንም መቀበሉን ነገር ግን እስካሁን ማረጋገጫ ለታንዛንያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አለመላኩን በቀናቶች ውስጥም ማረጋገጫውን እንደሚልክ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ህዝብ ግንኙነት እና ዋና ጸሀፊ ወንድምኩን አላዩ ለኢትዮአዲስ ስፖርት ተናግረዋል፡፡ የሁለቱ ሀገራት ጨዋታም በቀጣዩ ሳምንት መጨረሻ እንደሚደረግ ቀነ ቀጠሮ እንደተያዘለት እና ለብኄራዊ ቡድኑ ተጫዋቾችም በሳምንቱ መጨረሻ ጥሪ እንደሚደረግላቸውም ጽህፈት ቤት ሀላፊው ለኢትዪአዲስ ስፖርት ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡  የታንዛንያ ብሄራዊ ቡድን ለጨዋታው ለ24 በሀገር ውስጥ እና በውጭ ለሚገኙ ተጫዋቾቹ ጥሪ ያደረገ ሲሆን ከቀናት በዋላም ተሰባስቦ ልምምዱን ይጀምራል፡፡

image

ቀይ ቀበሮዎቹ ከማሊ አቻቸው ወሳኙን ፍልሚያ ነገ ከሰአት ያደርጋሉ   

🎄 የ2017 ከ17 አመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ የመጨረሻ ማጣሪያ ጨዋታዎች ዛሬ ነገ ይካሄዳሉ ፡፡ ከ10 ቀናቶች በፊት ማሊ ባማኮ አቅንቶ 2-0 በሆነ ውጤት የተረታው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንም አዲስ አበባ እና አበበ ቢቂላ ስቴዲየሞች ላይ ከማሊ መልስ ልምምዶችን ሲያከናውን ቆይቷል ፡፡ የብሄራዊ ቡደኑ ዋና አስልጣኝ አጥናፉ አለሙ ለኢትዪአዲስ ስፖርት ባሳለፍነው ሀሙስ እንደተናገሩት ከሆነ በነገ ከሰአቱ የታዳጊዎቹ ጨዋታ ላይ ኳስን መሰረት ያደረገ አጨዋወት ይዘው ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይፋ ያደረጉ ሲሆን የአዲስ አበባ ነዋሪም ነገ በአዲስ አበባ ስቴዲየም በመገኘት ለታዳጊዎቹ ድጋፉን እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡ የቀይ ቀበሮዎቹ እና የማሊ አቻቸው ጨዋታ ነገ በ10 ሰአት በአዲስ አበባ ስቴዲየም የሚደረግ ሲሆን ኢትዮአዲስ ስፖርትም በስፍራው በመገኘት እንደተለመደው ጨዋታውን በጽኀፍ ዘገባ እና በምስል በቀጥታ የምታስተላልፍ ይሆናል፡፡  

የአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ ድልድል ይፋ ሆኗል    

ለ 11ኛ ጊዜ የሚደረገው የ አዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የእጣ ማውጣት ፕሮግራም በኢትዮጵያ ሆቴል ተከናውኗል።
በዘንድሮው ውድድር ላይ 6 የአዲስ አበባ ቡድኖች እና ሁለት ተጋባዥ ቡድኖች የሚሳተፉ ይሆናል። ተሳታፊ ቡድኖቹ ደደቢት፣ኢትዮ ኤሌትሪክ፣መከላከያ፣አአ
ከተማ፣አዳማ ከተማ፣ቅ/ጊዮርጊስ፣ኢት ንግድ ባንክ እና KCCA ናቸው።

ከሌላው ጊዜ ለየት የሚያደርገው የዩጋንዳው ሻምፕዮን KCCA ተጋባዥ የሚሆን ሲሆን ቡድኑ ከወዲሁ ፍቃደኛነቱን በማሳየቱ እንደሚሳተፍ ይጠበቃል።
ውድድሩ በቀጣይ ሳምንት መስከረም 28 ጀምሮ ጥቅምት 13 እንደሚጠናቀቅ ታውቋል።

በእጣ ማውጣት ፕሮግራሙ ላይ ተካፉይ ቡድኖች በሁለት ምድብ የተመደቡ ሲሆን
በምድብ አንድ
ኤሌትሪክ
KCCA
መከላከያ
ቅ/ጊዮርጊስ

በምድብ ሁለት
ኢትዮ ንግድ ባንክ
ደደቢት
አዳማ ከተማ
አ/አ ከተማ ተደልድለዋል።

የመክፈቻ ጨዋታውም ቅዳሜ መስከረም 28 በ ኢትዮ ኤሌትሪክ እና በቅ/ጊዮርጊስ መካከል የሚደረግ ይሆናል።
ከውድድሩ የተመረጡ ጨዋታዎች ተመርጠው የቀጥታ ስርጭት የሚኖራቸው ይሆናል።

የውድድሩ አሸናፊ ከተጋባዥ ቡድኖች ከሆነ ሁለተኛ ለወጣው የዋንጫ ሽልማት እንደሚበረከትለት ነገርግን ለአሸናፊው የተለየ ዋንጫ እንደሚሸለም ታውቋል።

image ዜና ማንችስተር ዩናይትድ
ማይክል ኦውን የዝላታን አጨዋወት እንዳልተመቸው ገልጽዋል

⚽ የቀድሞ የማን ዩናይትድ አጥቂ ማይክል ኦውን አዲሱ የማን ዩናይትድ አጥቂ ዝላታን ኢብራሂሞቪች ብቃት ደስተኛ እንዳልሆነ ተናግሯል፡፡ እንግሊዛዊው በአሁኑ ሰአት ለስካይ ስፖርት በተንታኝነት እያገለገለ የሚገኝ ሲሆን የዝላታን ኢብራሂሞቪች ከኳስ ውጪ የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች እንዳልማረኩት የገለጸ ሲሆን “እርሱ ከግቡ በስተጀርባ ሆኖ ኳሶችን በተመሳሳይ ቦታዎች ላይ ይጠብቃል ፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ እንቅስቃሴዎችን አያደርግም ሲል ተችቶታል፡፡ ” ኦውን ይህንን ይበል እንጂ ዝላታን ኢብራሂሞቪች ለዩናይትድ ባደረጋቸው 8 ጨዋታዎች 6 ግቦችን ከመረብ በማገናኘት የክለቡ ኮከብ ግብ አግቢ ነው፡፡ በሜዳ ላይ በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎችም ግብ ሳያስቆጥር በወጣባቸው ጨዋታዎች ላይ የተሻሉ ነጥቦች በማስመዘገብ ዝላታን ቀዳሚው ነው፡፡

image

ሆዜ ሞሪንሆ የሰርማት በዝቢን ታሪክ ተጋርተዋል 

⚽ አጀማመራቸው በዩናይትድ ቤት ቢያምርም 3 ጨዋታዎች በተከታታይ ተሸንፈው ሲብጠለጠሉ የነበሩት ፖርቱጋላዊ አሁን ኡፎይ ያሉ ይመስላል፡፡ በሶስት የተለያዩ ውድድሮች 3 ተከታታይ ጨዋታዎችን በማሸነፍ ወደ ቀድሞ አሸናፊነት ስነ ልቦናቸውም መመለስ ችለዋል፡፡ በዚህም በዩናይትድ ታሪክ የመጀመሪያ 10 ጨዋታቸው ላይ ብዛት ያላቸውን ጨዋታዎች በማሸነፍ የሰር ማት በዝቢን ታሪክ ተጋርተዋል፡፡ ሆዜ ሞሪንሆ በዩናይትድ ቤት በሁሉም ውድድሮች ላይ ካደረጉት 10 ጨዋታዎች 7ቱን በማሸነፍ ከሰር ማት በዝቢ እኩል መሆን ችለዋል፡፡ ዴቪድ ሞይስ 5 ፣ ፈርጉሰን እና አትኪንሰን 4 ፣  ቫንሀል 3 ጨዋታዎችን ከመጀመሪያ 10 ጨዋታዎች ውስጥ በማሸነፍ ተከታዮቹን ደረጃዎች ይዘዋል፡፡ የሆዜ ሞሪንሆ የማሸነፍ ስሌት በመቶኛ ሲሰላም 70% የሚሆነውን ድርሻ ይይዛል፡፡

ሁዋን ማታ ከዩናይትድ ጋር የሊጉን ዋንጫ ማንሳት እንዳለመ ተናግሯል

⚽ ዩናይትዶ ስፔናዊው ሁዋን ማታ ቋሚ ሆኖ በተሰለፈባቸው ጨዋታዎች ላይ ምንም አይነት ሽንፈት አልቀመሱም በሊጉ ካደረጉት 4 ጨዋታም 4ቱንም ማሸነፍ ችለዋል እርሱ ወደ ሜዳ ቋሚ ተሰላፊ ሆኖ ባልጀመረበት ጨዋታ ግን ዩናይትድ 2 ጨዋታ ተረትቷል፡፡ የአማካይ አጥቂው እንደተናገረው ከሆነም በቼልሲ ቤት ያላሳካውን የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን በዩናይትድ አሁን ካሉት ተጫዋቾ ጋር የማሳካት ጉጉት እንዳለው ተንፍሷል፡፡ እመኑኝ ዋንጫውን ከዚህ ምርጥ ስብስብ ጋር የማንሳት አቅም አለን ብሏል፡፡ ከሞሪንሆ ጋር ስላለው ወዳጅነት ተጠይቆም የእኔ እና የእርሱ ግንኙነት ተበላሽቶ አያውቅም በማለት ከዚህ ቀደምም ከፖርቱጋላዊው አለቃ ጋር የልብ ወዳጅ እንደነበር አውግቷል፡፡

image ዜና አርሰናል
  አርስን  ዌንገር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል 

⚽ ላለፉት 20 አመታት በመድፈኞቹ  ቤት ማሳለፍ የቻሉት አርሰን ዌንገር በሳምንቱ አጋማሽ ድፍን 20ኛ አመታቸውን ይዘዋል፡፡ የለንደኑን ክለብ ከትቢያ እንስተው የእንግሊዝ ሀያል ክለብ ማድረግ የቻሉት ፈረንሳዊው አለቃ በያዝነው የውድድር ዘመን 8 ተከታታይ ጨዋታዎችን ድል በማድረግ የውድድር አመታቸውን በድል ጉዞ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ላለፉት 20 አመታት ክለቡን በታማኝነት ማገልገላቸውን ተከትሎም ከአርሰናሉ ሊቀ መንበር ሰር ቺፕስ ከስዊክ ልዩ የምስጋና ስጦታ በክለቡ ስም አበርክተውላቸዋል፡፡ እንደ ዴይሊ ሜይል ዘገባ ደግሞ የመድፈኞቹ ባለስልጣናት ሊጠናቀቅ ወራቶች ብቻ የቀሩትን  ለአርሰን ዌንገር ኮንትራት ለተጨማሪ 2 አመታት ለማራዛም ማቀዳቸውን አስነብቧል፡፡

image

አሌክሲስ ሳንቼዝ ቁጥር 1 ምርጫቸው መሆኑን ተናግረዋል 

⚽ አርሰናል  በአውሮፓ ቻምፕየንስ ሊግ ለመጨረሻ ጊዜ ካስቆጠራቸው 16 ግቦች ውስጥ 11 የሚሆኑት የአሌክሲስ ሳንቼዝ አስተዋጾ የተገኙ ናቸው ተጫዋቹ 4 ግቦችን በቻምፒየንስ ሊጉ ያስቆጠረ ሲሆን 7 ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን በውድድሩ አመቻችቶ ማቀበል ችሏል፡፡ ይህም በመቶኛ ሲሰላ 69% የሚሆነውን ድርሻ ይይዛል፡፡ ይህንን ኮከብ ታዲያ አርሰን ዌንገር በያዝነው የውድድር ዘመን ከሚጫወትበት የመስመር አማካይ  ቦታ አንስተው የፊት መስመር ላይ አጥቂ አድርገው እያጫወቱት ይገኛሉ፡፡ ክለቡ ምንም እንኳ በክረምቱ ስፔናዊውን ሉካስ ፔሬዝን ከዲፖርቲቮ ላካሮኛ ቢያስፈርምም በፊት መስመር ላይ የመጀመሪያ ምርጫቸው ግን አሌክሲስ ሳንቼዝ መሆኑን ከረቡዕ ምሽቱ የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታ በዋላ ተናግረዋል፡፡

ፍራንሲስ ኮከለን በአስገራሚ ሁኔታ በፍጥነት አገግሟል

⚽ ባሳለፍነው ሳምንት በጉልበት ጉዳት ምክንያት በትንሹ ከሜዳ ለአንድ ወራት ያህል እንደሚርቅ ተነግሮለት የነበረው ፈረንሳዊው የአማካይ ስፍራ ተጫዋች ፍራንሲስ ኮክለን ከጉዳቱ ሙሉ ለሙሉ አገግሞ ልምምድ መስራት መጀመሩ ተሰምቷል፡፡ የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ አርሰናል ነገ ምሽት ከበርንሌ ጋር በሚያደርገው ጨዋታ ላይም ምን አልባትም የመሰለፍ እድል ሊያገኝ እንደሚችልም ተሰምቷል፡፡ በተያያዘ በሀምስትሪንግ ምክንያት በውድደር አመቱ ለአርሰናል 1 ጨዋታ ብቻ ያደረገው አሮን ራምሴ ከኢንተርናሽናል ብሬክ በዋላ መድፈኞቹን ማገልገል እንደሚጀመር ተሰምቷል፡፡ 

image ዜና ሊቨርፑል
የርገን ክሎፕ በሊቨርፑል ቤት የአሰልጣኝነት ህይታቸውን ማገባደድ ይፈልጋሉ 

⚽ ጀርመናዊው ህይወት በአንፊልድ ተመችቷቿል፡፡ ከሳምንታት በዋላ ቀዮቹን ከተቀላቀሉ አመት የሚሞላቸው የ49 አመቱ የርገን ክሎፕ በሊቨርፑል ቤት የአሰልጣኝነት ህይታቸውን ማገባደድ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ሜይንዝ እና ዶርትመንድን ማሰልጠን የቻሉት አሰልጣኙ እድሜያቸው 60 እስኪደርስ በአሰልጣኝነት መዝለቅ እንደሚፈልጉ ለሬዳክሽን ኔትዝወርክ ያወሩ ሲሆን በሊቨርፑል ቆይታቸውም ደስተኛ እንደሆኑና በመርሲሳይዱ ክለብም ለረጅም ጊዜያት መቆየት እንደሚፈልጉ ለጋዜጣው ተንፍሰዋል፡፡

image

ፖል ስኮልስ “ ሊቨርፑል የሊጉን ዋንጫ የማንሳት አቅም አለው ”

⚽ የቀድሞ የማን ዩናይትድ አማካይ ስፍራ ተጫዋች ፖል ስኮልስ በአሁኑ ሰዓት ለቢቲ ስፖርት በተንታኝነት እያገለገለ ይገኛል፡፡ አይን አፋሩ የመሀል ሜዳ ኮከብ በተንታኝነት ስራው የቀድሞ ተቀናቃኞቹ ሊቨርፑሎች የዘንድሮውን የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ የማንሳት አቅም እንዳላቸው ተናግሯል፡፡ ለዚህም እንደምክንያትነት ያቀረበው እንደ ቡድን መጫወታቸው እና ማጥቃት ላይ ቡድኑ ያለው ጥራት የሊጉ ሻምዮን መሆን እንደሚያስችለው ጠቅሷል፡፡ የመርሲሳይዱ ክለብ በውድድር ዘመኑ በሊጉ በ6 ጨዋታዎች 13 ነጥቦች በመያዝ 5 ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡

image ዜና ቼልሲ
ጆን ቴሪ እና ጆን ኦቢ ሜኬል ከሀል ሲቲው ጨዋታ ውጪ ሆነዋል

⚽ የሰማያዊዎቹ የኋላ ክፍል ክፍል ደጀን የሆነው ጆንቴሪ ልምምድ ቢጀርም ለዛሬው ጨዋታ ግን ዝግጁ እንዳልሆነ አንቶንዮ ኮንቴ አሳውቀዋል፡፡ በእግር ጉዳት ምክንያት ያለፉት 4 የሰማያዊዎቹ ጨዋታዎች ያመለጠው እንግሊዛዊውን ጨምሮ ሌላኛው ናይጄሪያዉ አማካይ ጆን ኦቢ ሚኬል ይፋ ባልሆነ መጠነኛ ችግር ምክንያት ከምሽቱ ጨዋታ ውጪ ሆኗል፡፡ የጆን ቴሪን ወደ ሜዳ አለመመለስ ተከትሎም ዛሬም ጋሪ ካሂል እና ዴቪድ ሊዊዝ በመሀል ተከላካይነት እንደሚጣመሩ ተሰምቷል፡፡

image

image ዜና ሪያል ማድሪድ
የሪያል ማድሪድ ተጫዋቾች ለኢንተርናሽናል ብሬክ ከየሀገራቸው ጥሪ ተደርጎላቸዋል

⚽ ሩሲያ በ2018 የምታሰናዳው የአለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች በቀጣዩ ሳምንት ይጀመራሉ የስፔን ብሄራዊ ቡድንም ከጣሊያን አቻው እና ከአልቤንያ ጋር ላለበት ወሳኝ ጨዋታ ለ23 ተጫዋቾች ጥሪ አድርጓል፡፡ የሪያል ማድሪዶቹ ናቾ ፣ ካራቫጃል ፣ ራሞስ ፣ ሞራታ ፣ ቫስኬዝ እና እና ኢስኮ ጥሪው የደረሳቸው የሎስ ብላንኮዎቹ ተጫዋቾች ናቸው ፡፡ በነጮቹ ቤት ለሀገራቸው ጥሪ ከቀረበላቸው ተጫዋቾ መካከል ጋሬት ቤል ከዌልስ ፣ ሉካ ሞድሪች እና ኮቫቺች ከክሮሺያ ፣ ቶኒ ክሩዝ ከ ጀርመን እና ክሎይር ናቫስ ከኮስታሪካ ጥሪ የቀረበላቸው ተጫዋቾች ናቸው፡፡

image ዜና ባርሴሎና
ሊዊስ ሄነሪኬ ሊዮኔል ሜሲን እና ኡምቲቲን በቀጣዩ የላሊጋ ጨዋታ ላይ ለመጠቀም አስቧል

⚽ ለሶስት ሳምንታት በጉዳት ምክንያት ከሜዳ ርቆ የነበረው የ2015 የባሎን ዲኦር አሸናፊው ሊዮኔል ሜሲ ከጉዳቱ እያገገመ ይገኛል፡፡ ባርሴሎና ከሴልታቪጎ የሚያደርገውን ጨዋታ ጨምሮ ሀገሩ ብራዚል በአለም ዋንጫው የምታደርጋቸው 2 የማጣሪያ ጨዋታዎች የሚያልፉት ጥበበኛው ከ15 ቀናት በዋላ ባርሴሎና በኑካምፕ ከዶፖርቲቮ ላካሮኛ ጋር በሚያደርገው ጨዋታ ሊሰለፍ እንደሚችል ስፖርት ጋዜጣ ዘግቧል፡፡ እንደ ጋዜጣው ዘገባ ከሆነ አሰልጣኝ ሊዊስ ሄነሪኬ ለሊዮኔል ሜሲ 30 ደቂቃዎች በጨዋታው ለመስጠት የወጠነ ሲሆን በጉዳት ያለፉት ጨዋታዎች ያለፉት ሳሙኤል ኡምቲቲም ቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ሊገባ እንደሚችል ጋዜጣው አክሎ ገልጽዋል፡፡

image

ጄራርድ ፒክዊ የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ 3ኛ ተከላካይ ሆኗል 

⚽ ስፔናዊው ተከላካይ ጄራርድ ፒክዌ በቀያይ ሰይጣኖቹ ቤት የመሰለፍ እድል ቢያጣም በባርሴሎና ነግሷል፡፡ በካታሎኑ ክለብ ሁሉንም ዋንጫዎች ማሳካት ችሏል፡፡ በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታ ላይ በርካታ ግቦችን ማስቆጠር የቻሉ ተከላካዮች ሁሉ 3ኛ ደረጃን እንዲያገኝ ያደረገችውን ግብ ደግሞ ባሳለፍነው ረቡዕ ቦርሲያ ሞንቼግራላርባሀ ላይ አሳርፏል፡፡  ይህ ግቡ በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግም በስሙ ማስቆር የቻለው 11 ኛ ግቡ ስትሆን  ለማን ዩናይትድ 2 ለባርሴሎና ደግሞ 9 ግቦችን ከመረብ አገናኝቷል፡፡

ሰሞንኛ ቁጥራዊ እውነታዎች
🎦 ማንችስተር ዪናይትድ በአውሮፓ መድረክ ባለፉት አመታት በስኬት ባይጓዝም በ2013 በሪያል ማድሪድ በሜዳው ኦልድትራፎርድ ከተሸነፈ በዋላ በውድድ ላይ በሜዳ ያለፉትን 11 ጨዋታዎች አልተረታም የላንክሻየሩ ክለብ ከ11ዱ ጨዋታዎች 8ቱን የረታ ሲሆን በ3ቱ ደግሞ አቻ ተለያይቷል፡፡ 

🎦 እንግሊዛዊው የማንችስተር ሲቲ የመስመር አማካይ ስፍራ ተጫዋች ራሂም ስተርሊንግ በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ላይ ራሱ መረብ ላይ እና ተጋጣሚ መረብ ላይ ግቦችን ማሳረፍ የቻለ የመጀመሪያው እንግሊዛዊ ነው፡፡ ፈጣኑ እንግሊዛዊ ማንችስተር ሲቲ እና ሴልቲክ ባደረጉት የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታ ግቦችን ያሳረፈው፡፡

🎦 ከ2012 አንስቶ እንደ ክርስትያን ቤንቴኬ በሊጉ በርካታ ግቦችን በጭንቅላቱ በመግጨት ያስቆጠረ ተጫዋች የለም፡፡ ቤልጄማዊው ግብዳ በሊጉ ላይ ከመረብ በአስቶንቪላ በሊቨርፑል እና በአሁኑ ክለቡ ክርስታል ፓላስ ካስቆራቸው 54 ግቦች 19ኙ በጭንቅላት ተገጭተው የተቆጠሩ ናቸው፡፡

🎦 የሌስተር ሲቲው አጥቂ ኢስላም ስሊማኒ የፖርቶ ግብ ጠባቂ ኢከር ካሲያስ ላይ በ3 ጨዋታዎች 5 ግቦችን  ማስቆጠር ችሏል፡፡ አልጄሪያዊው የጎል ቀበኛ ስፔናዊው የግብ ዘብ ላይ ያሳለፍነውን የውድድር ዘመን ጨምሮ በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ እና በፖርቱጋሉ ፕሪሚየራ ሊጋ ነው ግቦቹን ማስቆጠር የቻለው

🎦 የኤቨርተኑ አጥቂ ሮሜሎ ሉካኮ የፈረንጆች አዲስ አመት ከገባ ጀምሮ በአንግሊዝ ፕረሚየር ሊግ ያለቀላቸው የግብ እድሎችን በማምከን በጂሚቫርዲ ብቻ በ1 ይበለጣል፡፡ ቤልጄማዊው ግዙፍ አጥቂ በአመቱ 14 ለጎል በእጅጉ የቀረቡ ኳሶችን አምክኗል፡፡ 

ይህን ያውቁ ኖሯል 

💰 የሪያል ማድሪዱ ኮከብ ክርስትያኖ ሮናልዶ በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ 100ኛ ግቡን 3 ግቦች ብቻ ይቀሩታል፡፡ የ2014 የፊፋ ባሎን ዲኦር አሸናፊው 97ቱን ግቦች በስፖርቲንግ ሊዝበን ማን ዩናይትድ እና ሪያል ማድሪድ ቆይታው ማስቆጠር ችሏል፡፡

💰 የማንችስተር ዩናይትዱ አጥቂ ዝላታን ኢብራሂሞቪች በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ እና ኢሮፓ ሊግ ውድድሮች ላይ ለ7 የአውሮፓ ክለቦች ተጫውቶ ለ7ቱም ክለቦች በአውሮፓው መድረክ ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡

💰 በጥንቃቄው እና በከባድ የመልሶ መጥቃት ሲስተማቸው የሚታወቁት አትሌቲኮ ማድሪዶች በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ላይ በዲያጎ ሲሞኔ መሰልጠን ከጀመሩ ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ በ23 ጨዋታዎች ላይ መረባቸውን አላስደፈሩም ፡፡

💰 ማንችስተር ሲቲን ገጥሞ ያልተረታው ክለብ እስካሁን የስኮትላንዱ ሴልቲክ ብቻ ነው ሲቲ ከዚህ ቀደም ባደረጋቸው 11 ጨዋታዎች ሁሉንም ያሸነፈ ሲሆን ባሳለፍነው ሳምንት ግን ጉዞው በሴልቲክ ተገቷል፡፡

💰 በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ታሪክ የመጀመሪያ የምድቡን 2 ጨዋታዎች ረትቶ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ የተሳነው እንግሊዝን ወክሎ በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የተወዳደረ ክለብ የለም፡፡ 

ከዜናዎቹ ጋር ፈይሰል  ሀይሌ ነበርኩ መልካም የቅዳሜ ከሰአት ይሁንላቹ

Advertisements