Skip to content
Advertisements

በዘንድሮ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መታየት ያለባቸው 11 ተስፈኛ ተጫዋቾች

 

ለኢትዮአዲስ ስፖርት በፈይሰል ኃይሌ  ፧   2009 

በተተኪዎች እጥረት የሚታማው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ምን አልባትም ዘንድሮ ከታች ስማቸውን የተቅስናላቹ ተጫዋቾች ደምቀው ከታዩበት እና ካንጸባረቁበት ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እና ለሊጉ ተከታታዮች መልካም ዜናን ይዟል፡፡ ተጫዋቾቹ ከዚህ ቀደም በቦታቸው ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴን ያሳዩ በያዝነው አመትም ብቃታቸውን ይደግማሉ ተብለው ተስፋ የተጣለባቸው ታዳጊዎች እና በሊጉ እምብዛም ያልታዩ ተጫዋቾች ናቸው፡፡

picsart_11-05-05-51-17

ተክለማሪያም ሻንቆ / ክለብ ፡- አዲስ አበባ ከተማ/ ግብ ጠባቂ   

➡ 2008 ለእርሱ በእጅጉ ጥሩ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ለታዳጊው እና ዋና ብሄራዊ ቡድን ጥሪ ደርሶት የነበረ ሲሆን በተለይም ከ20 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን ጋር ረጅም ጉዞ መጓዝ ችሏል፡፡ የ19 አመቱ ተክለማሪያም ሻንቆ ባሳለፍነው አመት በሱፐር ለሊጉ ከአዲስ አበባ ከነማ ጋር መልካም የሚባል ጊዜን አሳልፏል፡፡ በአብዛኛዎቹ ጨዋታዎች ላይም ቡድኑን እየመራ የግብ ክልሉን ጠብቋል፡፡ የአየር ላይ ኳሶችን ነቅቶ የሚጠብቀው እና ፊት ለፊት አጥቂዎችን የሚጋፈጠው ግብ ጠባቂው ኳስን መስርቶ በመጫዋትም የቡድኑን ሚዛን ይጠብቃል፡፡ ጨዋታዎችን የማንበብ አቅሙ በጣም ድንቅ ሲሆን የተከላካይ ክፍሉን በማደራጀቱም አይታማም፡፡ ቡድኑ ወደፊት በሚያጠቃ እና በሚከላከል ሰአት የቡድን አጋራቹን ያግዛል፡፡ ይህንን ድንቅ የበረኛ ብቃቱን ዘንድሮም በሊጉ ከደገመ እና በግብ ጠባቂዎች እጥረት ባለበት ሊግ ላይም ራሱን በሚገባ  ካቀረበ በታላላቆቹ የሊጉ ክለቦች ትኩረት ውስጥ መግባቱ እና በሊጉም መድመቁ አይቀሬ ነው፡፡

   ሄናክ አዱኛ / ክለብ ፡- ድሬዳዋ ከተማ / የቀኝ መስመር ተከላካይ  

➡ የድሬው ልጅ ባሳለፍነው አመት በሊጉ ተስፋ ሰጪ እንቅሰቃሴን ካደረጉ ተጫዋቾች መሀል ይጠቀሳል፡፡ በቀኝ መስመር ተከላካይ ቦታ ላይ የኢትዮጵያ ቡናው አብዱልከሪም መሀመድ ባሳለፍነው አመት ቢያንጸባርቅም የድሬዳዋ ከነማው ሄኖክ አዱኛ ከእርሱ ቀጥሎ በሊጉ ላይ ከታዩ ተስፈኛ የቀኝ መስመር ተከላካዮች ቁጥር አንዱ ነው፡፡ በተለይም የተከላካይ ስፍራ ተጫዋቾችችን ብቁ እና ሙሉ በማድረግ በሊጉ ካሉ አሰልጣኞች ቀዳሚው በሆነው ዘላለም ሽፈራው በዘንድሮ የውድድር ዘመን መሰልጠኑ ከልጁ አዲስ ነገር እንድንጠብቅ ያስገድደናል፡፡ ቶሎ ቶሎ ወደ ተቃራኒ የግብ መስመር የሚሄደው ሄኖክ ባሳለፍነው አመት በሊጉ የመጀመሪያ አጋማሽ ጥሩ በሆነው የድሬዳዋ ከነማ ቡድን ውስጥ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ሲሆን ኳሶችን አመቻችቶ በማቀበል ፣ ኳሶችን ከመስመር በማሻማት እንዲሁም ወደ ግብ በመሞከር የቀኝ መስመር ተካላካይ ሊያሟላቸው የሚገባቸውን ብቃቶች ይዟል፡፡

picsart_11-06-05-27-59

   ያሬድ ባየህ / ክለብ ፡- ፋሲል ከተማ / የመሀል ተከላካይ 

➡ ባሳለፍነው አመት ኢትዮጵያ ሴካፋን ስታዘጋጅ ያሬድ ባየህ የብሄራዊ ቡድኑ አባል ነበር፡፡ የቀድሞ የአማራ ውሀ ስራዎች ተጫዋች አስገራሚ እድገትን ባለፉት 2 አመታት ማሳየት የቻለ ሲሆን ምንም እንኳ ዳሽን ቢራ ወደ ታችኛው ሊግ ባሰላፍነው አመት ቢወርድም ተከላካዩ ያሬድ ባየህ ግን በግሉ ጥሩ ነበር፡፡ ኳስ መስርቶ መጫወት ፡ ቡድን መምራት ፣ መረጋጋት እንዲሁም የአየር ላይ ኳሶችን በመመከት ጥሩ የሆነው ያሬድ ባየህ በውድድር አመቱ በፋሲል ከተማ የምንመለከተው ይሆናል፡፡ ቁመት እና በተክለ ሰውነት በሚጠይቀው በመሀል ተከላካይ ክፍል ቦታ ላይም በያዝነው አመት በሊጉ ደምቀው ይታያሉ ከሚባሉት ተጫዋቾች አንዱ ያሬድ ባየህ ነው፡፡ በተደጋጋሚ ለብሄራዊ ቡድኑ መሰለፍ የቻለው ቁመተ መለሎው ተከላካይ ለአዲስ መጪዎቹ ፋሲል ከነማዎች በቦታው ከፍተኛ ግልጋሎቱን እንደሚሰጥም ከወደሁ በአጼዎቹ ደጋፊዎች ተገምቶለታል፡፡

   አህመድ ረሺድ  / ክለብ ፡- ኢትዮጵያ ቡና / የግራ  መስመር ተከላካይ 

➡ አህመድ ረሺድ (ሽሪላው) ባሳለፍነው አመት በሊጉ ከታዩ እና ተስፋ ከተሰነቀባቸው ተጫዋቾች አንዱ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ቡና ያለፉትን አመታት በግራ መስመር ተከላካይ ቦታ ላይ መጫወት የቻለው ተከላካይ ዘንድሮ በሊጉ ላይ በግራ መስመር ይደምቃሉ ከተባሉላቸው ተጫዋቾች አንዱ ነው፡፡ ያለፈው አመት የሊጉ 2ኛ አጋማሽ ላይ ጠንካራ የነበረው የኢትዮጵያ ቡና የተከላካይ መሰመር አባል የነበረው አህመድ ረሺድ ፈጣን ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚ የግብ መስመር በመሄድ የሚያጠቃ ፡ በፍጥነት ቦታው ላይ ተመልሶም የቡድኑን የመከላከል ሚዛን የሚጠብቅ አስፈላጊ በሆኑ ቦታዎች ላይ ኳሶችን ወደ ግብ የሚሞክር እንዲሁም አማካይ ክፍሉን የሚያግዝ ተጫዋች ነው፡፡ በአሰልጣኝ ገብረ መድህን ሀይሌ ስርም ለብሄራዊ ቡድኑ ጥሪ ተደርጎለት ኢትዮጵያ ወደ ማሴሮ አቅንታ ሌሴቶን በጌታነህ ከበደ ግቦች በረታችበት ጨዋታ ላይ ቋሚ ተሰላፊ ሆኖ ድንቅ ብቃቱን ማሳየት ችሏል፡፡ ዘንድሮም ይህንን ብቃቱን በዚህ ስፍራ ከደገመ በቦታው ቁጥር አንድ ተመራጭ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡

   ሳምሶን ጥላሁን / ክለብ ፡- ደደቢት / አማካይ  

➡ ደደቢቶች አስራት መገርሳን ከዳሽን ቢራ ማስፈረማቸውን ተከትሎ በሊጉ በያዝነው አመት ሊታዪ ከሚገባቸው ተጫዋቾች ሳምሶን ጥላሁን ቀዳሚው ነው፡፡ ባለፉት 2 አመታት የክለቡ የአማካይ ተከላካይ ሆኖ ያሳለፈው የቀድሞ የፈረሰኞቹ ወጣት ቡድን ተጫዋች ሳምሶን ጥላሁን  አስራት መገርሳ ደደቢትን  መቀላቀሉን ተከትሎ በዚህ የውድድር ዘመን ወደ ከአማካይ ተከላካይ ወደ ማጥቃት ሚና ወደ ሚያዘወትርበት የአማካይ አጥቂ ስፍራ ላይ እንደሚመለስ ይጠበቃል፡፡ ከአማካይ ተከላካይ ቦታ በተሻለ በአማካይ አጥቂ ቦታ ላይ ድንቅ የሆነው ሳምሶን አይበገሬዎቹ አጥቂዎች ጌታነህ ከበደ እና ዳዊት ፍቃዱ ባሉበት የደደቢት የፊት መስመርንም ከኋላ ሆኖ በሚገባ እንደሚያግዝ ተነግሮለታል፡፡ በተደጋጋሚ ተመርጦ ያልተጫወተለት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ስፍራ ላይም ዘንድሮ ጥሪ ይደርሳቸዋል ተብለው ከሚጠበቁ ተጫዋቾች ግንባር ቀደሙ ነው፡፡

   አቡበከር ሳኒ  / ክለብ ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ / አማካይ   

➡ ባሳለፍነው አመት ጥቂት የመሰለፍ እድሎችን በቅዱስ ጊዮርጊሱ አሰልጣኝ ማርት ኖይ ያገኝ የነበረው አብበከር ሳኒ በያዝነው አመት የተሻለ የመሰለፍ እድልን ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በአዲስ አበባ ሲቲካፕ ውድድር ላይ ያንጸባረቀው አማካዩ በሁሉም ጨዋታዎች ላይ ቋሚ ሆኖ የተሰለፈ ሲሆን በውድድሩ ላይም 5 ግቦችን ከመረብ በማገናኘት የውድድሩ ኮከብ ግብ አግቢ ሆና ማጠናቀቅ ችሏል፡፡ በ4-2-3-1 አሰላለፍ ላይ እየደመቀ የሚገኘው አቡበከር ሳኒ በያዝነው አመት የተሻለ የመሰለፍ እድልን ካገኘ በፈረሰኞቹ ቤት ማንጸባረቁ አይቀሬ ነው፡፡ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ታዳጊ ቡድን የተገኘው አማካይ ፈጣን ፣ ግብ አስቆጣሪ ፣ እንዲሁም ኳሶችን በተገቢው ሰአት ለቡድን ጓደኞቹ አመቻችቶ በማቀበል የተወደሰ ሲሆን የሊጉ እንዲሁም የቀጣይ አመታት የብሄራዊ ቡድኑ ተስፋም ነው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በአፍሪካ እና በሀገር ውስጥ መድረኮች ተሳታፊነታቸውን ተከትሎም ተጫዋቹ በውድድር አመቱ በርከት ያሉ የመሰለፍ እድሎችን እንደሚያገኝ የበርካቶች ግምት ቢሆንም ለቋሚነት ግን ከበሀይሉ አሰፋ እና ራምኬል ሎክ እንዲሁም ምን ያህል ተሾመ ጋር መፎካከር ይጠበቅበታል፡፡

   ፍሬው ሰለሞን  / ክለብ ፡- አዋሳ ከተማ / የአማካይ አጥቂ   

➡ ፍሬው ሰለሞን (ጣቁሩ)  ስሙ በስፋት በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ቢያያዝም ማረፊያውን ግን በመጨረሻም አዋሳ ከነማ አድርጓል፡፡ በርካቶች በአጨዋወቱ ከሽመልስ በቀለ ጋር የሚያመሳስሉት ጨዋታ አቀጣጣዩ በውድድር ዘመኑ ጅማሮ በደብብ ሲቲ ካፕ ላይ መልካም የሚባል ብቃቱን ማሳየት ችሏል፡፡ በፍጥነት ፣ በፈጣሪነት ፣ ቶሎ ቶሎ ኳሶችን ወደ ግብ በመላክ እና ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ በማቀበል በሊጉ ካሉ ጥቂት የአማካይ አጥቂዎች አንዱ የሆነው ፍሬው ሰለሞን በ2009 በሊጉ ሊታዪ ከሚገባቸው ተጫዋቾች መሀል አንዱ ነው፡፡ በተደጋጋሚ ለብሄራዊ ቡድን ጥሪ ቀርቦለት የመጫወት እድል የተነፈገው አማካዩ በውድድር አመቱ በአዋሳ ቤት ማንነቱን ካሳየ አዲሱን የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ መማረኩ አይቀሬ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ተጫዋቹ በውጤታማው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ስር መሆኑ እና ለእርሱም አጨዋወት የሚበጅ አይነት ታክቲክ በመያዙ ሊጉ ላይ ማንጸባረቁ አይቀሬ ነው፡፡

   ቢኒያም በላይ  / ክለብ ፡- ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ  / የመስመር ተጫዋች 

➡ ወደ ሀገረ ጀርመን አቅንቶ ከሙከራ በዋላ የተመለሰው ታዳጊው ተስፈኛ ኮከብ ቢኒያም በላይ በዘንድሮ የውድድር አመት የሊጉ ተመልካቾች ሊመለከቱት የጓጉለት አዲሱ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ተስፋ ነው፡፡ የድሬው ልጅ ባሳለፍነው አመት በኢንስትራክተር ዩሀንስ ሰሀሌ አማካኝነት በሴካፋ ውድድሮች ላይ በርካታ የመሰለፍ እድሎችን ማግኘት የቻለ ሲሆን በውድድሩም ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴን ማድረግ ችሏል፡፡ ምንም እንኳ ባሳለፍነው አመት ለብሄራዊ ቡድኑ ተሰላፊ ቢሆንም ለክለቡ ንግድ ባንክ በቁጥር በርከት ያሉ ጨዋታዎችን ባለማድረጉ በሊጉ ተመልካቾች ያልታየው ተስፈኛው የመስመር ተጫዋች በ2009 ግን በሊጉ ላይ ሊታዪ ከሚገባቸው ተጫዋቾች ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ አብዶኛ የሆነው ቢኒያም በላይ ኳሶችን ከመስመር ክሮስ በማድረግ እንዲሁም ያለቀላቸውን ኳሶችን አመቻችቶ በማቀበል መልካም ብቃት አለው፡፡ ክለቡን በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት የለቀቀውን ኤፍሬም አሻሞንም በሚገባ እንደሚተካ ታምኖበታል፡፡

   አዲስ ግደይ  / ክለብ ፡- ሲዳማ ቡና  / የመስመር ተጫዋች 

➡ የሲዳማ ቡናው ኮከብ አዲስ ግደይ በዚህ የውድድር ዘመን በሊጉ ሊታዩ ከሚገባቸው ተጫዋቾች መሀል በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡፡ ባሳለፍነው አመት በሊጉ ከሲዳማ ቡና ጋር አሪፍ የሚባል የውድድር ዘመን ያሳለፈው የመስመር ተጫዋቹ ዘንድሮም ብቃቱን አሻሽሎ በመቅረብ የሊጉ ክስተት ለመሆን ተዘጋጅቷል፡፡ በደቡብ ሲቲ ካፕ የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች እና ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ ማገባደድ የቻለው አዲስ ግደይ ድንቅ የሆኑ ግቦችን አስቆጣሪ ፣ ፈጣን ፣ ግቦችን አሳሽ እንዲሁም የቡድኑን የማጥቃት ሚና የሚቃኝ ሲሆን ኳሶችንም አመቻችቶ በማቀበል የሚስተካከለው የለም ፡፡ ከወዲሁም በበርካቶች እይታ አዲስ ግደይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የወደፊት ተስፋ ሆኗል፡፡ በአለማየሁ አባይነህ የሚሰለጥነው ሲዳማ ቡና ፍጹም ተፈሪ እንዲሁም በካሜሮናዊው ባሪ ዱለም ፊት መስመሩን ቢመራም የአዲስ ግደይ መስመር ላይ መሆን ቡድን በማጥቃቱ ረገድ በውድድር አመቱ የተሻለ ውጤታማ እንደሚያደርገው ይጠበቃል፡፡

   ዳዋ ሁጤሳ  / ክለብ ፡- አዳማ ከተማ  / የፊት መስመር   

➡ በዘመነ ማሪያኖ ባሬቶ ለብሄራዊ ቡድኑ የአጥቂ ስፍራ ተመራጭ የነበረው ታዳጊው ዳዋ በ2006 አጋማሽ መልካም ስምን ይዞ በርካታ ተስፋ የተሰነቀበት የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን አባል ነበር ፡፡ በወንድም አገኝ ከበደ ይመራ የነበረው እና በወቅቱም ቪክቶሪያ ድረስ  አቅንቶ የሲሰልስ አቻውን 2-0 ሲያሸንፍ ዳዋ የቡድኑ አባል የነበረ ሲሆን በመልሱ ጨዋታ ላይም ብሄራዊ ቡድኑ አዲስ አበባ ስቴዲየም ላይ ባደረገው ጨዋታ ላይም 1 ግብ ማስቆጠሩ ይታወሳል፡፡ ይህ ወጣት በዛው አመት ከዴሬዳዋ ሲሚንቶ ፈረሰኞቹን ቢቀላቀልም በግሉ ያልተሳኩ 2 አመታትን ከክለቡ ጋር ካሳለፈ በዋላ በክረምቱ የዝውውር መስኮት አዳማ ከተማን ተቀላቅሏል፡፡ በሲቲ ካፑም ራሱን በሚገባ ማሳየት የቻለው ዳዋ በውድድር አመቱ ከናዝሬቱ ክለብ ጋር መድመቁ አይቀሬ ይመስላል፡፡ ፍጥነት ቅልጥፍና እንዲሁም ጉልበትን ቀላቅሎ የሚጫወተው አጥቂው በሊጉ ሊታዩ ከሚገባቸው ተጫዋቾች መሀል አንዱ ነው፡፡ በተለይም በቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ በሚገባ ያላገኘውን በርካታ ጨዋታዎች ላይ የመሰለፍ እድልን በአዳማ የሚያገኝ መሆኑ እና ለወጣቶች እድልን በመስጠት የሚታወቀው በአሸናፊ በቀለ መሰልጠኑ በተጨማሪም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ የራሳቸውን አሻራ ጥለው ካለፉት አጥቂዎቹ አንዱ ከሆነው ታፈሰ ተስፋዪ ጋር መጣመሩ ደግሞ የልጁ ቀጣይ ፍሬያማ እድገት ላይ በበርካቶች እምነት እንዲጣል አድርጓል፡፡

   አሜ መሀመድ  / ክለብ ፡- ጅማ አባቡና / ፊት መስመር   

➡ የከፍተኛው ሊግን ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ ያጠናቀቀው ተስፈኛው ፊት አውራሪ አሜ መሀመድ በ2009 ሊጉ ሊመለከታቸው ከጓጓላቸው አጥቂዎች ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ ባሳለፍነው አመት በክለብም ሆነ በወጣት ብሄራዊ ቡድን በግሉ መልካም ብቃቱን ያሳየው አጥቂው ከታዳጊ ብሄራዊ ቡድኑ ጋር በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ላይ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መድረስ ችሎ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን በስሙ 3 ግቦችን ማስቆጠር የቻለው አሜ ከወዲሁ ከሳላዲን ሰይድ ጋር በርካቶች እያመሳሰሉት ይገኛሉ፡፡ በቴክኒኩ ረገድ የተዋጣለት የሆነው ታዳጊው በዚህ አስደናቂ ብቃቱ የሚቀጥል ከሆነ ለብሄራዊ ቡድን ጥሪ  ይደረግለታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ፍጥነት ቅልጥፍና ጉልበትን ጨራሽነትን በሚጠይቀው የአጥቂ ስፍራ ላይ ሁሉንም በሟሟላት በርካቶችን እያስደነቀ የሚገኘው አሜ መሀመድ ከወዲሁ የሊጉ አፍቃሪያንን ትኩረት ስቦ ይገኛል፡፡ ምንም እንኳ ክለቡ ጅማ አባ ቡና በሲቲ ካፑ ከምድቡ እንኳ ማለፍ ቢሳነውም አጥቂው በተሰለፈባቸው ጨዋታዎች ግን አስገራሚ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን በማድረግ በተመልካቾች ከፍተኛ የሆነ ውዳሴን ማግኘት ችሏል፡፡

Advertisements
%d bloggers like this: