Skip to content
Advertisements

​የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 5ኛ ሳምንት ጨዋታ ዳሰሳ – ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ አዳማ ከነማ /የሳምንቱ ታላቅ ጨዋታ/

በፈይሰል ኃይሌ | ህዳር 29፣ 2009 ዓ.ም


በሊጉ 5ኛ ሳምንት ከሚደረጉ  ጨዋታዎች መሀል ግንባር ቀደም ተጠቃሹ የፊታችን እሁድ በአዲስ አበባ ስቴዲየም ቅዱስ ጊዮርጊስ እና አዳማ ከነማ የሚያደርጉት ጨዋታ ነው፡፡ ፈረሰኞቹ ባሳለፍነው አመት ሙሉ ነጥቦች ካላገኙባቸው ጥቂት ክለቦች መሀል በቀዳሚነት የሚጠቀሰው አዳማ ከነማ ነው፡፡ 2ቱ ክለቦች ባሳለፍነው አመት በሊጉ ባደረጓቸው 2 ጨዋታዎች አዳማ ከነማዎች የበላይነት አላቸው፡፡

በ2008 በሊጉ የመክፈቻ ጨዋታ ፈረሰኞቹ ከአዳማ ጋር ባደረጉት ጨዋታ 2-0 የተሸነፉ ሲሆን በመልሱ ጨዋታ ደግሞ በአዲስ አበባ ስቴዲየም 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ጨዋታቸውን አጠናቀዋል፡፡ በ4 ጨዋታዎች በፋሲል ከነማ ብቻ መረባቸው የተደፈረባቸው ፈረሰኞቹ በሊጉ 9 ነጥቦችን በመያዝ ከ 7 ንጹ ግቦች ጋር ሊጉን መምራታቸውን ቀጥለዋል፡፡ ያለፉት 3 አመታት የሊጉ አሸናፊ በመሆን አይበገሬነታቸውን ያሳዩት ፈረሰኞቹ በሊጉ 5ኛ ሳምንት ከአዳማ ከነማ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶታል፡፡ 

የ2008 የሊጉ ኮከብ ተጫዋች ሆኖ የተመረጠው አስቻለው ታመነ በጉዳት ምክንያት ባልተሳተፈባቸው ጨዋታዎች የፈረሰኞቹን የኋላ ደጀን ሆኖ የተከላካይ ክፍሉን ሲመራ የነበረው ምንተስኖት አዳነ በዚህም ጨዋታ የቋሚነት እድሉን እንደሚያገኝ ከወደ ፈረሰኞቹ ካምፕ ተሰምቷል፡፡ በሊጉ 3 ግቦችን በስማቸው ማስቆጠር የቻሉት የፊት መስመር ተሰላፊዎች ሰላዲን ሰይድ እና አዳነ ግርማ ጥምረት ከወዲሁ የአዳማ ተከላካይ ክፍልን እንደሚፈትን ይጠበቃል፡፡
አዳማ ከነማዎች ምንም እንኳ ከመሪዎቹ በ2 ነጥቦች ርቀው በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ 4ኛ ደረጃ ላይ ቢመቀመጡም አሁንም ስብስባቸው በሊጉ ካሉት ክለቦች የተሻለ ደረጃን ይይዛል፡፡ 7 ነጥቦችን በ4ቱ ጨዋታዎች ሰብሰብው ከመሪዎቹ አንገት ስር እየተነፈሱ ይገኛሉ፡፡ ባለፉት 3 የሊጉ ጨዋታዎች ባሳለፍነው አመት ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ጨምሮ ለቀድሞ ክለቡ በመሀል ተከላካይነት ይጫወት የነበረውን ሙጂብ ቃሲምን  በአጥቂ ስፍራ ላይ እያጫወቱ የሚገኙት አዳማ ከነማዎች ከወዲሁ በግዙፉ መጠቀም ጀምረዋል፡፡ ጠጣር እንደሆነ የሚነገርለት የተከላካይ ክፍሉም በወላይታ ዲቻ እና በኢትዮጵያ ቡና ከተቆጠሩበት ግቦች ውጪ መረቡን አላስደፈረም፡፡ ባሳለፍነው እሁድ በአዳማ አበበ ቢቂላ ስቴዲየም ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ባደረጉት ጨዋታ ከደጋፊዎች ስርአት አልበኝነት ጋር ተያይዞ በተነሳ ብጥብጥ ክለቡ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቅጣት እንደሚጠብቀው ከወዲሁ ተነግሯል፡፡

Advertisements
%d bloggers like this: