Skip to content
Advertisements

​የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የትናንት ምሽት ጨዋታዎች ቅኝት

በMikiyas B. Wordofa | ታህሳስ 2፣ 2009 ዓም


በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በሳምንቱ መጨረሻ ቅዳሜ የአምናውን ሻምፒዮን ሌስተር ሲቲንና ማንችስተር ሲቲን ካገናኘው ትልቅ ጨዋታ በተጨማሪ አምስት ወሳኝ ጨዋታዎች ተደርገዋል። የኢትዮአዲስ ስፓርቱ ፀኃፊ ሚኪያስ እንዚህን ጨዋታዎች ቅኝት በሚከተለው መልኩ በአጭር በአጭሩ  አዘጋጅቷቸዋል።

አርሰናል 3 – 1 ስቶክ ሲቲ


መድፈኞቹ በሜዳቸው ስቶኮችን አስተናግድው ምስጋና ለቲዎ ዋልኮት፣ ሜሶት ኦዚልና የመጨረሻ ሰአት የአሌክስ ኢዎቢ ጎሎች ይግባና ከመመራት በማንሰራራት ሶስት ነጥቦችን በሜዳቸው በመሰብሰብ በፕሪሚየር ሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ አናት ላይ በመቀመጥ ቼልሲ ላይ ውጥረት መፍጠር ችለዋል፡፡ 

በጨዋታው ላይ በትናንትናው እለት 31ኛ አመቱን የደፈነው ቻርሊ አዳም የአርሰናሉ ዣካ በጆ አለን ላይ በፈፀመው ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት በማስቆጠር ለቡድኑ የቅድሚያ መሪነትን ቢያስገኝም የስቶክ መሪነት የዘለቀው ግን ለ40 ደቂቃዎች ያክል ነበር፡፡ ቲዎ ዋልኮት የጨዋታው የመጀመሪያ ግማሽ ከመጠናቀቁ ጥቂት በፊት የአቻነቷን ግብ ማስቆጠር ሲችል ከእረፍት መልስ ደግሞ ገና ጨዋታው ከመጀመሩ ጥቂት ቆይታ በኋላ ሜሶት ኦዚል ከቻምበርሊን የተሸገረለትን ኳስ ተጠቅሞ አርሰናልን መሪ ማድረግ ቻለ፡፡ ከዚህ በኋላ የነበሩት ደቂቃዎች ስቶክ ወደ አርሰናል ግቦች በጥቂት አጋጣሚዎች በመመላለስና አንዳንድ የግብ እድሎች በመፍጠር ለማስጨነቅ የሞከረበት ነበር፡፡

ነገር ግን ጨዋታው ሊጠናቀቅ 15 ደቂቃዎች ሲቀሩ የአርሰናልን ማሸነፍ እርግጥ ያስመሰለና ልዩነቱን ያሰፋ መድፈኞቹንም ከቼልሲ (ቼልሲ ዛሬ ከዌስትብሮም ጨዋታ አለው) እኩል በ34 ነጥብ የጠረጴዛው አናት ላይ ያስቀመጠ ግብ በአሌክስ አይዎቢ ተቆጥሮ ጨዋታው 3-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል፡፡


ሁል ሲቲ 3 – 3 ክሪስታል ፓላስበጣም ፉክክር የታየበትና ስድስት ግቦችን ያስተናገደው ይህ ግጥሚያ ክሪስታሎች በመጨረሻ ሰዓት ባስቆጠሩት ግብ በአቻ ውጤት ሊጠናቀቅ ችሏል፡፡ 

በጨዋታው ነብሮቹ በ26ኛው ደቂቃ ያገኙትን ፍፁም ቅጣት ምት ስኖድግራስ አስቆጥሮ መሪ መሆን ቢችሉም ሁልሲቲዎች ይህን መሪነት ማስጠበቅ የቻሉት ቤንቴኬ ከእረፍት መልስ ለንስሮቹ ፓላሶች የአቻነቱን ግብ እስካስቆጠረበት ጊዜ ነበር፡፡

ከዚያም ፓላሶች በዊልፍሬድ ዛሀ ግብ ጨዋታውን መምራት ቻሉ፡፡ ነገር ግን አዳም ዳይሞንዴ ለሁል ሲቲ የአቻነት ግብ ማስመዝገብ ችሎ ጨዋታው 2-2 በሆነ ግለት ቀጠለ፡፡ ብዙም ሳይቆይ ግን ነብሮቹን ወደ መሪነት የመለሰ ግብ በጃክ ሊቨርሞል መቆጠር ቻለ፡፡ የፓርዲው ልጆች ግን እስከ መጨረሻው እጅ ሳይሰጡ በመጫወት በ 89 ደቂቃ በፍሬዘር ካምቤል የጭንቅላት ኳስ አንድ ነጥብ ማግኘት ቻሉ፡፡ 

በርንሌይ 3 – 2 በርንማውዝ


በዚህ በርንሌዮች እራሳቸውን ከወራጅ ቀጠና ባወጡበት ግጥሚያ ተርፍ ሙር ላይ ቦርንማውዝን አስተናግደው 3-2 በሆነ ውጤት ሶስት ነጥቦችን ማግኘት ችለዋል፡፡ 

ጨዋታው በተጀመረ በደቂቃዎች ውስጥ በሄንድሪክ አስደናቂ ምት በርንሌዮች መሪነትን መጨበጥ የቻሉ ሲሆን ከዛም ስቴፈን ወርድ ሁለተኛ ግብ አስቆጥሮ መሪነታቸውን ወደ ሁለት ማስፋት ቻሉ፡፡ በርንማውዞች በበኩላቸው በመጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቂያ ህይወት የዘሩበትን አንድ ግብ በቤኒክ አፎቤ ማስቆጠር ችለው ነበር፡፡ ነገር ግን ከእረፍት መልስ በ75ኛው ደቂቃ በርንሌዮች ሶስተኛ ግብ በማስቆጠር የበርንማውዝን የማንሰራራት ህልም ማገደብ ችለው ነበር፡፡

በርንማውዞች ግን በሶስተኛው ግብ ሳይደናገጡ ግብ ለማስቆጠር ባደረጉት ጥረት በመጨረሻ ደቂቃ በዳንዬልስ ሁለተኛ ግብ ማስቆጠር ቻሉ፡፡ ነገር ግን ሌላ ግብ ማከል ሳይችሉ ቀርተው ሶስቱን ነጥብ ለባለሜዳዎች አስረክበው ተመልሰዋል፡፡


ስዋንሲ 3 – 0 ሰንደርላንድስዋንሲዎች ተቀናቃኛቸውን ሰንደርላንድ ወደ ታች ረግጠው ባስቀሩበት ግጥሚያ 3-0 በሆነ ሰፊ ውጤት በማሸነፍ ድመቶቹን የሰንጠረዡ እታችኛው ግርጌ ላይ ተደላድለው እንዲቀመጡ አድርገዋቸዋል፡፡

ለሁለቱም በጣም ተስፋ አስቆራጭ በሆነው የመጀመሪያ ግማሽ ምንም ግብ ሳይመዘገብ በ 0-0 ውጤት ጨዋታው ተጠናቋል፡፡ ከእረፍት መልስ ሲጉድረሰን የከፈተውን የጎል በር እንደ መነሳሻ የተጠቀመበት ፈርናንዶ ሎረንቴ ሁለት ግቦችን አከታትሎ በማስቆጠር የቦብ ብራድሊ ቡድን ሁለተኛ ድሉን እንዲያገኝ መርዳት ችሏል፡፡ ሰንደርላንድም የደረጃው ሰንጠረዥ መጨረሻ ሆኖ መቀጠል ግድ ብሎታል፡፡ 

ዋትፎርድ 3 -2 ኤቨርተን


በዚህ ግጥሚያ ዋትፎርዶች ከ1987 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰማያዊ ለባሾቹን ኤቨርተኖች መርታት ችለዋል፡፡ 

ስቴፈን ኦካኩም ለዋትፎርዶች የመጀመሪያ ግቡን ማስቆጠር ችሏል፡፡ በጨዋታው ላይ ኤቨርተኖች በሉካካ ጎል የቅድሚያ መሪነትን ማግኘት ችለው የነበረ ሲሆን ስቴፋኖ ኦካኩ የአቻነቷንና የማሸነፊያውን ሶስተኛ ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው 3-2 ተጠናቋል፡፡ ሉካካ በጨዋታው ላይ ሁለተኛ ግብ ማስቆጠር ችሎ የነበረ ቢሆንም ቡድኑን ከመሸነፍ መታደግ ሳይችል ቀርቶ ሶስቱ ነጥብ በህርትፎርድ ሻየር ሊቆይ ችሏል፡፡ 

ሌስተር 4 – 2 ማንችስተር ሲቲ


ጂሚ ቫርዲ በአስር ተከታታይ የፕሪምየር ሊግ ግጥሚያ የነበረውን የጎል ማግባት ድርቅ በሰበረበት ጨዋታ ሶስት ግቦችን አስቆጥሮ ቀበሮዎቹ ሲቲዎችን ያስደነገጠ አሸናፊነት ማስመዝገብ ችለዋል፡፡ ጨዋታው በተጀመረ አምስት ደቂቃዎች ውስጥ ሁለት ግቦችን ያስቆጠሩት ሌሽተሮች በቫርዲ ሁለተኛ ግብ በ 20 ደቂቃ ውስጥ ጨዋታውን 3-0 መምራት ቻሉ፡፡

ከዛም ቫርዲ ሀትሪኩን በሰራበት ሶስተኛ ግብ መሪነታቸውን ማጠናከር ቻሉ፡፡ አሌክሳንደር ኮላሮቭና ኖሊቶ በበኩላቸው የሲቲን ማስተዛዘኛ ሁለት ግቦች አስቆጥረዋል፡፡ በጨዋታው ላይ የታየው የክላውዲዮ ብራቮ ደካማ አቋምም ብዙዎች ጋርዲዮላ በጆይ ኸርት ላይ በሰራው ጥፋትና ማግለል የመጣ እንጂ እንደ አምናና ካቻምናው ጆይ ኸርት ቢሆን በረኛው ሲቲ ይሄን ያህል ጎል አይቆጠርበትም ሲሉ ተችተዋል፡፡

Advertisements
%d bloggers like this: