Skip to content
Advertisements

የላ ሊጋው የውድድር ዘመኑ ምርጥ ቡድን

ወንድወሰን ጥበቡ | ታህሳስ 14፣ 2009 ዓ.ም


​የስካይ ስፖርቱ የስፔን እግርኳስ ልዩ ባለሙያ የሆነው ቴሪ ጊብሰን የ2016-17 የውድድር ዘመን የስካሁኑ የስፔኑ ላ ሊጋ ምርጥ ቡድንን በሚከተለው መልኩ መርጧል። እኛም በሚከተለው መልኩ አሰናድተንልዎታል።

በእስካሁኑ የመጀመሪያው አጋማሽ የስፔኑ ላ ሊጋ ውድድር ማራኪ ጨዋታዎችና ድንቅ ብቃቶች ታይተዋል። በአሁኑ ጊዜ ሪያል ማድሪዶች እጃቸውን ወደዋንጫው አቅርበው የደረጃ ሰንጠረዡን ይመራሉ። የአምናው ሻምፒዮን ባርሴሎናዎች ደግሞ ከተቀናቃኛቸው በቅርብ ርቀት ይከተላሉ።

የጊብስን የላ ሊጋው የውድድር ዘመን የመጀመሪያ አጋማሽ ምርጥ ቡድን ምርጫ አሰላለፍም ከዚህ እንደሚከተለው 4-2-3-1 ነው።

ግብ ጠባቂ፡ ሰርጂዮ አሰንጆ

በሊጉ ላይ ያሉ ሌሎች ግብ ጠባቂዎችን ተመልክታችሁ በጉዳት ላይ ስለሚገኘው ኬይሎር ናቫስ ብዙ ይባልም ይሆናል። በተለምዶም የምንመርጠው ግብ ጠባቂ ጥቂት ብቻ ግቦች የተቆጠረበትን ነው። በዚህም የሪያል ማድሪዱ ግብ ጠባቂ ተመራጭ ነው። ነገር ግን ለአሁኑ የላ ሊጋው የውድድር ዘመኑ ምርጥ ግብ ጠባቂ ምርጫዬ ግን የተሻለው የቪላሪያሉ ግብ ጠባቂ  አሰንጆ ነው። አሰንጆ ለሶስት ጊዜያት ያህል የጡንቻ ስር ጉዳት አጋጥሞትም እንኳ ጥሩ ብቃቱን ማሳየት ችሏል። እናም በዚህ ችግር ላይ ሆኖም ስኬታማ መሆኑን በእጅጉ ያስደንቀኛል።

የቀኝ ተከላካይ፡ ማሪዮ ጋስፐር

በ16 የላ ሊጋው ጨዋታዎች ላይ በሙሉ ተሰልፎ ቢጫወትም መረቡን ያስደፈረው ለ11 ጊዜያት ብቻ ነው። ጋስፐር 10 የላ ሊጋ ጨዋታ ላይ መሰለፍ ከቻለው የማድሪዱ ዳኒ ካርቫሃል ለጥቂት የተሻለ ተጫዋችም አድርጌዋለሁ።

የመኃል ተከላካይ: ጄራርድ ፒኬ

በዚህ የውድድር ዘመን በባርሴሎና የኋላ ደጀን ላይ ድንቅ ነበር። እንዲሁም እንደሴልታ ቪጎና ማላጋ ካሉ ክለቦች ጋር ቡድኑ ወደፊት ለማጥቃት በሚቸገርበት ጊዜ ቡድኑን ለመምራትና ግቦች እንዲቆጠሩ ለማድረግ ጥረቶችን ያደረግ ነበር። በጨዋታዎች የመጨረሻዎቹ 10 ደቂቃዎች ራሱን በተቃራኒ ቡድን ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ በሚገባ ያሳትፍ ነበር። በመሆኑም ድንቅ የሆነ ብቃት ነበረው።

የመሃል ተከላካይ፡ ሰርጂዮ ራሞስ

የበዛ የራስ መተማመን ያለው በመሆኑ የተነሳ በእኔም ሆነ በሌሎች ሰዎች ትችት የደረሰበት ተጫዋች ነበር። ነገር ግን እስከመጨረሻው ድረስ ማንም በእሱ ችሎታ ላይ ጥርጣሬ አልነበረውም። ብስለቱንም በሚገባ ማሳየት ችሏል። በጨዋታዎች ላይ ብዙ መሳተፉ በእሱና በቪክቶር ሩዝ መካከል ያለውን ቀጭን የድንበር መስመር እንዲያስወግድልኝ አድርጎኛል። ምንም እንኳ ከ16ቱ የላ ሊጋ ጨዋታዎች በዘጠኙ ላይ ብቻ መሰለፍ ቢችልም ካስቆጠራቸው አራት ግቦች በተጨማሪ በውድድር ዘመኑ ላይ መፍጠር የቻላቸውን ተፅዕኖዎች ቸል ማለት አንችልም። በሁለት ሳምንታት ልዩነት በባርሴሎና እና በዲፖርቲቮ ላይ ያስቆጠራቸው ወሳኝ ግቦች የእሱን ተፅእኖ እንዳንዘነጋው የሚያስገድዱን ነገሮች ናቸው።

የግራ ተከላካይ: ማርሴሎ

በሪያል በዚህ የውድድር ዘመን በጥሩ አቋም ላይ የሚገኝ አንድ ተጫዋች ቢኖር ማርሴሎ መሆኑ ግልፅ ነው።  ማድሪድ ያለምንም ሽንፈትም በሊጉ አናት ላይ ይገኛል። በተለምዶ ከዚህ ቀደም በባርሴሎና ይታይ እንደነበረው በሪያልም ስድስትና ሰባት መሰል ተጫዋቾች ይኖሩ ነበር። ነገር ግን በዚህ የውድድር ዘመን ማድሪድ በመላው ተጫዋች ላይ የተመሰረተ ቡድን ነው። በዚህ የውድድር ዘመን የነበራቸውም ጥንካሬ ይኸው ነበር።

የመኃል አማካኝ: ስቴቨን ን’ዞንዚ

በዚህ የውድድር ዘመን በሲቪያ ጥሩ ቡድን ውስጥ ድንቅ ተጫዋች ነበር ብዬ አስባለሁ። በፈረንሳይ ቡድን ውስጥ አለመካተቱንም ላምን የምችለው ነገር አይደለም። ሲቪያዎችም ከዚህ ቀደም እንደሚያድረጉት ጥይት የሆኑ ተጫዋቻቸውን ከመሸጥ ይልቅ በክለቡ ያቆዩታል የሚል ተስፋ አለኝ። የሚሸጡት ከሆነ ደግሞ በዚህ የውድድር ዘመን ካሳየው ብቃት አንፃር ተጫዋቹን የሚሸጡት በኮንትራት አንቀፁ ላይ ባሰፈሩት የውል ማፍረሻ እንደሚሆንም ተስፋ አለኝ። 

የመኃል አማካኝ: ቶኒ ክሩዝ

ክሩዝን በዚህ ስፍራ ላይ መምረጤ ምንም የሚደንቅ ነገር የለውም። ምክኒያቱም የዓለማችን ድንቅ ተጫዋች ነው። የሚደንቅ ነገር ቢኖር በጉዳት የተነሳ በመጀመሪያ ተሰላፊነት መጫወት የቻለው በ11 ጨዋታዎች ላይ ብቻ መሆኑ ነው። ስለዚህ በተወሰኑ ጨዋታዎች ላይ እረፍት ወስዶ ነበር የሚል ሃሳብ ማከሌ ብቻውን በቂ ነው። በጉዳቱ የተነሳ ያመለጠው ነገር ቢኖር የብሄራዊ ቡድን ጨዋታዎች በመሆኑ የሁለት ሳምንት የእረፍት ጊዜያትን እንዲያገኝ አስችሎታል እንጂ ብዙ ጨዋታዎች እንዳያደርግ አላገደውም። እሱን እንድመርጠውም በዚህ የውድድር ዘመን ለሪያል ማድሪድ ትልልቅ ጨዋታዎች ላይ የመጫወት በቂ ዕድል ያገኘም ይመስለኛል።

የቀኝ ክንፍ: ያኒክ ካራስኮ

ከአትሌቲኮ ማድሪድ ተጫዋቾች መላውን የተከላካይ ክፍል ብምረጥም በቀኝ በኩል ለመመርጥ የምችለው ብቸኛ ተጫዋቻቸው ቢኖር እሱን ነው። ካራስኮ በዚህ የውድድር ዘመን እውነተኛ ኮከባቸው ነበር! ተጫዋቾች የእውነተኛ መሻሻል ሲያሳዩ ማየት ሁልጊዜም ጥሩ ነገር ነው። በተለይ ደግሞ ደካማ የሆኑበትና መሻሻል የሚገባው ቦታ መሻሻል ሲያሳይ። ለዚህ ማሳያ ደግሞ በ11 ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ ስድስት ግቦችን በማስቆጠር በአትሌቲኮ ቡድን ውስጥ ማሳደር የቻለው ትልቅ ተፅዕኖ ነው።

ግራ ክንፍ: ኬቨን ፕሪንስ ቦቲንግ

ይህን ተጫዋች የመረጥኩት በተወሰኑ ምክኒያቶች ነው። አንደኛው የላስ ፓልማስ ተጫዋች መሆኑ ሲሆን ሌላው ደግም በቪላሪያል ላይ ባስቆጠረውና እኔን ባስደመመኝ በዚያ ድንቅ ግብ ምክኒያት ነው። በግራ ክንፍ ላይ በሚገባ መጫወት የሚችል ሲሆን በላስ ፓልማስ ውስጥ የተጫዋችነት ዘመኑን ካጠናቀቀ ደግሞ የሚያስገርም ነው። እውነት እንነጋገር ከተባለም ገና መልካም ጊዜያት ከፊቱ የሚጠብቁት ተጫዋች ነው። ምንም እንኳ በላስ ፓልማስ ለመቆየት የወሰነበት ምክኒያት አክብሮት ሊቸረው የሚገባ ቢሆንም አብዛኛው የእግርኳሱ ሰው ወድፊት ገና ቀሪ ጊዜ እንዳለው ግን ይስማማል። በዚያ የሚያበቃ ከሆነም የክለቡ ትክክለኛ ጥቅም ነው። ለእኔ እሱን መመልከት የሚያዝናናኝ ነገር ነው። ለበርካታ ጊዜያትም ስመለከተው ቆይቻለሁ። የአጨዋወት መንገዱንም የምወደው ነው። ለላስ ፓልማስና እንደ1970ዎቹ የብራዚል ቡድን ላለ ክለብ የሚመጥን ተጫዋች ነው። በተለይ ደግሞ ያ ግብ! ከዚህ ቀደም ይህን ያህል ቁጥር ያለው የኳስ ቅብብል፣ የተረከዝ አሰጠጥና በመቀስ ምት የተቆጠር ግብ አይነት የተሻለ አጨዋወት አይቻለሁ ብዬ አላስብም።

የጨዋታ አቀጣጣይ: ሊዮኔል መሲ

በፈለገው አዲስ የመጫወቻ ስፍራ ላይ መጫወት ይችላል። በተወሰኑ ምክኒያቶች በዚህ የውድድር ዘመን በመልካም ብቃቱ ላይ እንደማይገኝ ሲነገር ቆይቷል። ነገር ግን በሁሉም ውድድሮች ላይ 23 ግቦችን አስቆጥሯል። እሁድ ዕለት [ከስፓኞል ጋር] ያደረገው የመጨረሻው ጨዋታ ደግሞ በላ ሊጋው ላይ ያደረገው 13ኛ ጨዋታው ሲሆን በእነዚህ ጨዋታዎች ላይም 12 ጊዜ ኳስና መረብን ማገናኘት ችሏል። እንዲሁም በርካታ የግብ ዕድሎችንም ፈጥሯል። ታዲያ መሲ የተለመደው ዓይነት በጥሩ አቋሙ ላይ የማይገኘው የቱ ጋር ነው?

አጥቂ: ልዊስ ስዋሬዝ

ሌላኛው ሁለት ልብ እንድሆን ያደረገኝ ቦታ እንደዊሊያን ጆሴ፣ ኢያጎ አስፓስ እንዲሁም ከሁለቱም በላይ በጀመሪያ ልመርጠው ይገባኛል ብዬ ያስበኩት ክርስቲያኖ ሮናልዶ ያሉ ተጫዋቾች የሚገኙበት የመሃል አጥቂ ስፍራ ነው። ከእሁድ ምሽቱ ጨዋታ በኋላ ግን ልዊስ ስዋሬዝን ለመምረጥ ውሳኔ ላይ ደረስኩ። በዚህ የውድድር ዘመን መስፍረት ያደረግኩት ደግሞ ተጫዋቾች ያደረጓቸውን ጨዋታዎችና የጨዋታ ተሳትፎዎች ነው። ከዚህ አንፃር ደግሞ ሮናልዶ የተጫወተው በ11 ጨዋታዎች ላይ ሲሆን አምስት ጨዋታዎችም አምልጠውታል።10 ግቦችን ቢያስቃጥርም ሶስቱ በፍፁም ቅጣት ምት የተቆጠሩ ናቸው። ይህ ማለት ደግሞ በትክክል ግብ ማስቆጠር የቻለው በአምስት ጨዋታዎች ላይ ብቻ ነው። ስለዚህ ግብ ያላስቆጠረባቸው በርካታ ጨዋታዎች አሉ። ልዊስ ስዋሬዝ ግን 15 ጨዋታዎችን ሲያደርግ 12 ግቦችን ያለምንም ፍፁም ቅጣት ምት መረብ ላይ አሳርፏል። ከእነዚህ ጨዋታዎች መካከልም በዘጠኙ ላይ ግብ አግብቷል። ስለዚህ ይህን ተመልክቼ በመደበኛው ቦታ ላይ መሆን የሚገባው እሱ ነው ስል ውሳኔ ላይ ደረስኩ። በዚህ ቁጥራዊ መረጃም መሰረትም ልዊስ ስዋሬዝ የመጨረሻ ምርጫዬ ሆነ። 

Advertisements
%d bloggers like this: