Skip to content
Advertisements

የሰኞ አመሻሽ የአውሮፓ ጋዜጦች የዝውውርና ሌሎች አስደንጋጭ እንዲሁም አዝናኝ ወሬዎች


በሚኪያስ በ. ወርዶፋ| ሰኞ ታህሳስ 17, 2009

በ 44 ሚሊዮን ፓውንድ ፒኤስጂን ተቀላቅሎ 18 ወራትን በፈረንሳዩ ክለብ ያሳለፈውና ወደ ቀድሞ ብቃቱ ለመመለስ እየታገለ የሚገኘው የቀድሞው የማድሪድና የዩናይትድ አማካኝ አንጌል ዲማሪያ ወደ ቻይና ይዘዋወራል ተብሎ የሚጠበቅ ቀጣዩ ተጫዋች እንደሆነ ተገልጿል፡፡ (ሚረር ሌኪፕን ጠቅሶ እንደጻፈው)

ታዋቂው የሀይል ሰጪ መጠጥ አምራች ሬድ ቡል ዌስትሀምን በ 200 ሚሊዮን ፓውንድ ለመግዛት አልሟል፡፡ (ዘ ሰን) 

አዲሱ የክሪስታል ፓላስ አሰልጣኝ ሳም አላርዳይስ ቡድናቸውን በፕሪምየር ሊጉ ለመቆየት በሚያደርጉት ጥረት እገዛ እንዲያደርግላቸው የሰንደርላንዱን አጥቂ ጀርሜን ዴፎን ማስፈረም ፈልገዋል፡፡ (ሚረር) 

ነገር ግን የሰንደርላንዱ አለቃ ዴቪድ ሞየስ ዴፎ ለሽያጭ የማይቀርብ ተጫዋቻቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ (ሰንደርላንድ ኤኮ)

በሌላ በኩል ሳም አላርዳይስ በቶትነሀም የሚፈለገውን የክንፍ ተጫዋቻቸውን ዊልፍሬድ ዛሀን በክለቡ ለማቆየት ትልቅ ፈተና ከፊታቸው ይጠብቃቸዋል፡፡ (ዴይሊ ስታር)

የፈረንሳዩ ሀብታም ክለብ ፒኤስጂ ለሊቨርፑሉ ጨዋታ አቀጣጣይ ፍሊፔ ኩቲንሆ 40 ሚሊዮን ፓውንድ የዝውውር ገንዘብ ለማቅረብ እየተዘጋጀ ነው፡፡ (ዴይሊ ኤክስፕረስ)

የእንግሊዝ እግር ኳስ ማህበር(FA) ለ 21 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝነት ላወጣው የስራ ማስታወቂያ ከ 10 በላይ የተወዳዳሪዎች የስራ ማመልከቻ ደርሶታል፡፡ (ዴይሊ ሜል)

የቼልሲው አለቃ አንቶኒዮ ኮንቴ በፕሪምየር ሊጉ ላይ የመጫወት እድልን ለማግኘት እየተጋ ያለውን ወጣቱን አጥቂ ሚቺ ባትሱሀዪን ጥሩ ተጫዋች መሆን ከፈለገ ዲያጎ ኮስታን ማየትና ከእሱ ትምህርት መቅሰም እንዳለበት ነግሮታል፡፡ (ዴይሊ ስታር) 

ባርሴሎና የፖርቹጋሉን ቀኝ ተከላካይ ጃኦ ካንሴሎን በ 25.5 ሚሊዮን ፓውንድ ለማስፈረም ከቫሌንሺያ ጋር መስማማት ላይ ደርሷል፡፡ (ስፖርት)

የኤቨርተኑ አለቃ ሮናልድ ኩመን በመጪው ጥር የሳውዛምፕተኑን አማካኝ ቨርጂል ቫን ዲጂክን ጨምሮ አምስት ተጫዋቾችን ለማስፈረም አቅደዋል፡፡ (ዘ ሰን)

በመጨረሻም … 

ቼልሲዎች በረኛቸው ቲቤት ኮርትዋ በመጪው ክረምት ጥሏቸው ወደ ማድሪድ የሚያመራ ከሆነ በሲቲው በረኛ ጆይ ሀርት ሊተኩት አስበዋል፡፡ በሲቲ ቤት በጋርዲዮላ ተገቢ ባልሆነ መልኩ የተገፋው ሀርት የእንግሊዝ የወቅቱ ቁጥር 1 ግብ ጠባቂ ሲሆን በውሰት በሚገኝበት ጣሊያንም አስደማሚ ብቃቱን እያሳየ ይገኛል፡፡ (ዴይሊ ኤክስፕረስ)

የቶትነሀሙ አለቃ ማርኮ ፖቸቲኖ የሳውዝአምፕተኑን ኮከብ ጄይ ሮድሪጌዝ ለማስፈረም ክለባቸው በተጠንቀቅ እንዲቆም አሳስበዋል፡፡ (ዘ ሰን)

የአምናው ሻምፒዮን ሌሽተር አሰልጣኝ የሆኑት ክላውዲዮ ራዬሪ ባለፈው አመት የሊጉን ዋንጫ በስጦታ መልክ ያበረከቱላቸው ተጫዋቾቻው ዘንድሮ ምንም ስጦታ እንዳላበረከቱላቸው አጣብቂኝ ውስጥ ያለውን ቡድናቸውን ሁኔታ እያሰቡ በትካዜ መልስ ሰጥተዋል። 

ባለፈው አመት ገና ለነበራቸው የሊግ መሪነት ስኬት ማጀቢያ እንዲሆን ለሁሉም ተጫዋቾቻው ደውል ገዝተው ያበረከቱት ክላውዲዮ ራዬኔሪ ስለ ዘንድሮው ሁኔታው ሲያስረዱ “ዘንድሮ ተጫዋቾቼ እጃቸውን ወደ ኪሳቸው አልከተቱም። ከተጫዋቾቼ ምንም ስጦታ አልደረሰኝም።” ብለው መልሰዋል። 

በዚህ ሳያበቁም ቡድናቸው ከፍተኛ ችግር ላይ እንደሚገኝና በፕሪምየር ሊጉ ነጥብ ማስመዝገብ እንዳለባቸው ገልፀዋል። በመጨረሻም ቡድናቸው ቻምፒዮንስ ሊጉን ረስቶ ለሊጉ ትኩረት መስጠት እንዳለበት በአፅዕኖት በመናገር ዘንድሮ የገቡበትን ማጥ ክብደት አስረድተዋል። (ዴይሊ ስታር)

ቼልሲን በ 21.4 ሚሊዮን ፓውንድ ባሳለፍነው ነሀሴ የተቀላቀለው ስፔናዊው የአጥቂ መስመር ተጫዋች ፔድሮ ከባርሴሎና የወጣበትን ምክንያት ይፋ አድርጓል። 

ከስፔን ጋር የአለም ዋንጫን ማንሳት የቻለውና በኒውካምፕ ከክለቡ ጋር ብዙ ስኬትን ያጣጣመው ፔድሮ በከዋክብት በተሞላው የባርሴሎና ቤት የቋሚ ተሰላፊነት አለማግኘቱና ወደ ሜዳ የሚገባበት ደቂቃ ይበልጥ እያጠረ መምጣቱ ለተስፋ መቁረጥ ዳርጎት ክለቡን እንደለቀቀ ተናግሯል።

በአሁኑ ወቅት ሜሲን፣ ሱዋሬዝንና ኔይማርን በመሰሉ ኮከቦች የተገነባውን የባርሴሎና አጥቂ ክፍል ሰብሮ መግባት ያልቻለው ፔድሮ ስምንት አመታት የተጫወተበትን ባርሴሎና በትዝታ እያስታወሰ ከቼልሲ ጋር የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ለማንሳት እያለመ ይገኛል። (ዘ ሰን)
    

Advertisements

ሚኪያስ በቀለ View All

ይህን ዘገባ ያቀረብኩላችሁ የኢትዮአዲስ ስፓርት ኤዲተርና ፀሀፊ እኔ ሚኪያስ በቀለ ነኝ።

%d bloggers like this: