“ፖል ፖግባ የአለማችን ምርጡ አማካይ ነው” ሞሪንሆ

በዘውዱ በሬሳ | ታህሳስ 18,2009


የቀያዮቹ አሰልጣኝ ሆዜ ሞሪንሆ በክረምቱ የዝውውር መስኮት የዓለምን ክብረወሰን በሰበረ ዋጋ ወደክለቡ ያመጡትን ፈረንሳያዊ “የአለማችን የጊዜው ምርጥ አማካይ ነው” በማለት አሞካሽተዋል፡፡

በውድድር አመቱ ጅማሮ ላይ ባሳየው ደካማ እንቅስቃሴ ትችቶችን ሲያስተናግድ የቆየው ፖል ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን ብቃቱን በማሻሻል ለክለቡ ውጤት ማማር ቁልፍ አስተዋፅኦ ማበረከቱን ተያይዞታል፡፡

ይህን አስመልክቶ ጆዜ ሲናገሩ”ፖል ድንቅ ተጫዋችነቱን በደምብ እያስመሰከረ ነው፡፡ በአዲሱ አመት ደግሞ ከዚህ በበለጠ ብቃቱን እንደሚለግሰን አውቃለሁ፡፡ አራት አመት ካሳለፈበት ጣልያን መጥቶ ፕሪምየር ሊጉ ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆን ችሏል ፤ በደምብ ሲመቻች ደግሞ ልዩ ክህሎቱን ማየት የኛ ስራ ይሆናል ” በማለት የ 93 ሚልየን ፓውንድ ኮከባቸው ላይ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡

ጆዜ በተጨማሪም ፈረንሳያዊው የቀጣዩን አመት ባሎን ዶ’ር ክብር የማግኘት ዕድል እንዳለው ያሳወቁ ሲሆን”መራጭ አካሎቹ ጎልን ብቻ መሰረት ማድረጋቸውን ትተው ከመረጡ እንደፖግባ አይነቶቹ አማካዮች ሽልማቱን የማግኘት ከፍተኛ ዕድል ይኖራቸዋል፡፡ ፖልም ጎል አስቆጣሪ ተጫዋች ባይሆንም በመጪው አመት በርከት ያሉ ጎሎችን እንደሚያስቆጥር አምናለሁ ” በማለት ሀሳባቸውን አካፍለዋል፡፡

Advertisements