ማርክ ክላተንበርግ የዓመቱ ምርጥ ዳኛ  የሚል ስያሜ አገኙ

በወንድወሰን ጥበቡ | ረቡዕ ታህሳስ 19፣ 2009


ማርክ ክላተንበርግ በግሎብ ሶከር አዋርድ የዓለማች ምርጥ ዳኛ ተሰኝተዋል።

እንግሊዛዊው ዳኛ በ2016 በሪያል ማድሪድና በአትሌቲኮ ማድሪድ መካከል የተደረገውን የሻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ እና በፈረንሳይ የተደረገውን የዩሮ 2016 የፍፃሜ ጨዋታዎችን በመዳኘት ድንቅ ጊዜን አሳልፈዋል።

እንዲሁም ክላተንበርግ በክሪስታል ፓላስና በማንችስተር ዩናይትድ መካከል የተደረገውን የእንግሊዙን የኤፍኤ ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታም በዋና ዳኛነት መርተውታል።

በዱባይ በተደረገው በዚህ የግሎብ ሶከር አዋርድ ሪያል ማድሪድ ሻምፒዮንስ ሊጉን ያሸነፈው ሪያል ማድሪድ የዓመቱ ምርጥ ክለብ ሲባል፣ ፕሬዝደንቱ ፍሎረንቲኖ ፔሬዝ ደግሞ የዓመቱ ምርጥ የክለብ ፕሬዘደንት የሚል ስያሜ አግኝተዋል። ሌላው የሪያል ማድሪድ ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ብዙም በማይደንቅ ሁኔታ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች የሚለውን ሽልማት ማግኘት ችሏል።

እንዲሁም ወቅታዊው የፒኤስጂ አሰልጣኝና ባለፈው የውድድር ዘመን ከሲቪያ ጋር የዩሮፓ ሊግ ዋንጫን ያነሱት ኡናይ ኤምሬ ከፊፋው ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ እጅ ልዩ ተሸላሚ ሆነው ሽልማታቸውን ተቀብለዋል።

ሌላው በዚህ ተቋም ሽልማት ያገኙ ታዋቂ ሰው የዓመቱ ምርጥ አሰልጠኝ የተሰኙት ፖርቱጋልን ለዩሮ 2016 ዋንጫ ድል ያበቁት ፈርናንዶ ሳንቶስ ናቸው።

Advertisements