ዝውውር : ትውልደ ኢትዮጵያዊው ተጫዋች ወደ ጀርመን ሊያመራ ነው።


በሚኪያስ በ. ወርዶፋ| ሰኞ ረፋድ ታህሳስ 24, 2009

የእንግሊዙ ተነባቢ ጋዜጣ ሚረር እንዳወራው ከሆነ በአርሰናል ቤት ከ 16 አመቱ ጀምሮ የተቀላቀለው ትውልደ ኢትዮጵያዊው ጌዲዮን ዘላለም የሼንገርን ስብስብ ሰብሮ ገብቶ በዋናው ቡድን ቦታ ማግኘት ስላልቻለ ወደ ቦርሺያ ዶርትሙንድ ሊያመራ ነው። 

እንደ ዘገባው ወሬ ከሆነ ጌዲዮን ዘላለም በአርሰናል ቤት የጠበቀውን የመሰለፍ እድል ማግኘት እንዳልቻለና ባለበት ሁኔታ ተስፋ መቁረጡ ተሰምቷል።  

ይህንን የልጁን ተስፋ መቁረጥ ያወቁት የጀርመኑ ክለብ ሀላፊዎችም በጀርመን በርሊን ከኢትዮጵያ ወላጆች የተገኘውን የ 19 አመት ታዳጊ በያዝነው የጥር የዝውውር መስኮት ወደ ክለባቸው ሊወስዱት ፈልገዋል። 

በአስደናቂ ሁኔታ የጀርመንና የአሜሪካ ወጣት ብሄራዊ ቡድኖች ወክሎ መጫወት የቻለው ጌዲዮን ወደ አርሰናል ቤት ሲመጣ ትልልቅ ነገሮቹን ጠብቆ የነበረ ቢሆንም በአርሰናል ቤት ያሰበውን ትልቅ ነገር እንዲያሳካ የመሰለፍ እድል ማጣቱ ውጪ ውጪውን እንዲመለከት ምክንያት ሆኖታል።  

ያለፈውን የውድድር ዘመን በስኮትላንድ ሁለተኛ ሊግ ከሬንጀርስ ጋር በውሰት ስላሳለፈው ጌዴዮን አስተያየቱን የሰጠው የቡድን አጋሩ ጃክ ዊልሻየር “ብዙ ተጫዋቾች የማይችሉትን የኳስ የማቀበል ችሎታ ያለው ሲሆን ኳስ ሲይዝም ምቾት ያለው አጨዋወት አለው” ሲል ክለቡን ለመልቀቅ ስንዝር ስለቀረው ተጫዋች ያለውን አድናቆት ገልጿል።

Advertisements