Skip to content
Advertisements

ተስፋ: ከሪከርድ መጋራቱ በኃላስ መጪው ጊዜ ለሩኒ ምን ይዞ ይመጣ ይሆን?

በሚኪያስ በ. ወርዶፋ | ማክሰኞ ጥር 2, 2009

ከቅዳሜው ግጥሚያ በኃላ አሁን ጥያቄው ዋይኒ ሩኒ ከዚህ በኋላ ምን ያህል ጎል ለዩናይትድ ያስቆጥራል የሚለው ሆኗል። ይህ የሚወሰነው ግን በተጫዋቹ የክለቡ ቆይታ መሆኑ እርግጥ ነው።  የሩኒ የውል ስምምነት ስንመለከት ውሉን ለማራዘም የአንድ አካል ወይም የክለቡ ብቸኛ ፍላጎት እንደሚያስፈልገው ይገልፃል። በዚህም መሰረት ክለቡ ተጫዋቹ እንዲቀጥል ከፈለገ በየአመቱ የተጫዋቹን ኮንትራት ያራዝምለታል። 

አሁን ያለው የሩኒ የዩናይትድ ቤት ውል የሚጠናቀቀው በ 2019 ሲሆን ክለቡ ደስተኛ ሆኖ በውላቸው መሰረት ተጨማሪ አመታትን በክለቡ እንዲቆይ ከፈቀደለት 35 አመቱ ላይ ሆኖም ሩኒ በኦልትራፎርድ እንዲገኝ ያስችለዋል። 

ሩኒም ይህን ቆይታውን አበክሮ ይፈልጋል። ነገር ግን ክለቡስ የተጫዋቹን ቆይታ ይፈልግ ይሆን? ይህ አጥቂ ተጨማሪ ጎሎችን በዩናይትድ ቤት ቆይቶ ጎል ማስቆጠሩን እንዲቀጥል ተጨማሪ አመት ይሰጠው ይሆን? ይህ የሩኒ የመጨረሻ የእግር ኳስ አመታት ዙሪያ አስገራሚ የሚያደርግ ጉዳይ ነው። ግን እርግጥ ሩኒ ከዚህ በኃላ ምን ያክል ጊዜ በዩናይትድ ቤት አገልግሎት ሊሰጥ ይችላል?

የ 31 አመቱ አጥቂ ቅዳሜ ከሰአት የኤፍኤ ዋንጫ ቡድኑ የያም ስታሙን ሬዲንግ 4-0 እንዲያሸንፍ ትልቅ እገዛ አድርጓል። በጨዋታው ላይ ሩኒ በ 10 ቁጥር ሚናው ድንቅ የአጨራረስ ብቃትና ፈጠራን ማሳየት ችሏል።  

አስገራሚው ነገር ግን ሩኒ በደካማ እንቅስቃሴ ሙሉ አመቱን የጨረሰ መሆኑ ነው። ቅዳሜ ያስቆጠረው የሰባተኛው ደቂቃ የጨዋታው መክፈቻ ግብም በዘንድሮ የውድድር ዘመን ያስቆጠረው ገና አራተኛ ግቡ ነው። ከዚህ በኃላም በጆሴ ሞውሪንሆ ምርጥ 11 ውስጥ በቋሚነት እንደማይገባ እርግጥ ሆኗል። 

በወጣትነቱ እንደዛ ተከላካዮችን እየሰነጣጠቀ የሚያልፍ የነበረው ወጣት በ 31 አመቱ መቆም ግድ ብሎታል።  በአንድ ወቅት ለንዴት በጣም ፈጣን የነበረውና በከፍተኛ ጉልበት ሲጫወት የነበረው አጥቂ ዛሬ አድሜ አስክኖታል። 

ስለዚህ ለዩናይትድ ስንት ተጨማሪ ጎል ያስቆጥራል? ሩኒ የሰር ቦቢ ቻርልተንን ሪከርድ ከተጋራ በኃላ 250 ጎሎች ላይ መድረሱ እርግጥ  ሆኗል። በብሄራዊ ቡድን ደረጃም 119 ጨዋታዎችን አድርጎ 53 ጎሎችን ለማስቆጠር በቅቷል።

ለክለብና ለብሄራዊ ቡድን ኮከብ ጎል አስቆጣሪ መሆን መቻል የአንድን ተጫዋች ጥራት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። አስቸጋሪው ነገር የሪከርዱ ቀጣይነት ነው። ሩኒም 249 ጎሎች የደረሰበትን ጉዞ በቅኔ አሳምሮ “ያለኝን የእግር ኳስ ህይወት እያጣጣምኩት ነው” ሲል ገልፆታል።  

ይህ የሩኒ ንግግር የተሰነዘረውም የእግር ኳስ ህይወቱ እንዳበቃ ለሚሰጠው የጋዜጦች ወሬ እንደ መልስ እንዲሆን በማሰብ የተሰነዘረ ነው። ሩኒ በጋዜጦች የደረሰበትን ነገር “ክብር የሚነካ” ሲል በወቅቱ ገልፆታል። ሩኒ “ጋዜጦች እንደሞተ ሰው የዜና ዕረፍት ሊፅፉልኝ ሁሉ እንደሚፈልጉ አይነት ይሰማኛል። ይህ እንዲሆን አልፈቅድም። የእግር ኳስ ህይወቴ ገና አላበቃም።” ሲል ሁኔታውን በሀዘን ገልፆታል። 

የሩኒ የብቃት ውዝግብ ሊሰሙት ደስ የማይል የሚዲያ አፍ ሟማሻ ከሆነ ቆየት ብሏል። ሩኒ በተከታታይ የሚጠበቀውን ያህል ተጫዋች መሆን እንዳልቻለ የሚገልፁ ሀሜቶች ጆሮው ጥልቅ ይላሉ። አሁንም ከኮንትራቱ መጠናቀቅ በኃላ ለዩናይትድ ለመጫወት ያለው ፍላጎት ግን 15 አመታትን አሉታዊ ነገሮችን በሚገባ እየተጋፈጠ በትልቅ ደረጃ መጫወት ለቻለው ሩኒ ተቺዎች ቀልባቸውን መለስ እንዲያደርጉና ለገራገሩ አጥቂ ትልቅ ሀዘኔታ እንዲኖራቸው ያደርጋል።

ሩኒ እግር ኳስን ሲያቆም ይበልጥ የሰራው ስራ ከግንዛቤ ሊገባለትና በተቺዎቹ ሊሞገስ ይችላል። አስደሳቹ ነገር ግን የቡድን አጋሮቹ ከእሱ ጎን መሆናቸው ነው። በመጀመሪያ ከዚህ በኃላ ይሳካል ተብሎ በማይጠበቅ መልኩ ወደፊት የሰር ቦቢ ቻርልተንና ሩኒን ሪከርድ ሊሰብር እንደሚችል በሞውሪንሆ የተነገረለትና ቅዳሜ ሁለት ጎሎችን ያስቆጠረው የክለቡ የ 19 አመቱ ታዳጊ አጥቂ ረሽፎርድ የሩኒን ስኬት አሞግሶ ተናግሯል።

“የማይታመን ሪከርድ ነው። ወደኃላ ተመልሰህ ለክለቡ ያደረገውን ሁሉንም ጨዋታና ያስቆጠራቸውን ጎሎች ስትመለከት የሚያስደንቅና ለማንኛውም ወጣት ተጫዋችና አዳጊ አጥቂ ለመመልከት የሚያስደንቅ ነው። ሁላችንም ሪከርዱን በሚሰብርበት ወቅት አብረነው መደሰት አለብን።” ሲል ረሽፎርድ ለቡድን አጋሩ ያለውን አድናቆትና ድጋፍ አሳይቷል።

የሩኒ የመልበሻ ቤት ተፅዕኖ በሞውሪንሆ እንደ ቁልፍ ሀብት የሚታይ ሲሆን በቡድኑ አዋቂ ተጫዋቾችም እውቅና የተሰጠው ነው። በዩናይትድና በሆላንድ ብሄራዊ ቡድን በተቀያያሪ ሚና እየተጫወተ የሚገኘው ዴሊ ብሊንድ እንደተናገረው “ሩኒ ያስቆጠረው ጎል በጣም ከፍተኛ ነው። ትልቅ ስብዕና ያለውና በጣም ዝነኛ የክለባችን ተጫዋች ነው። ለእሱ እኔ ደስተኛ ነኝ።”  

በእዚህ ሰአት ዩናይትድ ከሩኒ ኮንትራት መጠናቀቅ በኃላ ለተጫዋቹ የ 12 ወር የውል ስምምነት ማቅረቡ የማይመስል ይመስላል። ነገር ግን ይሄ እግር ኳስ ነው። ማን ያውቃል? ሩኒ ዳግም ወደ ዩናይትድ ስብስብ መመለስና ወሳኝ ተጫዋች መሆን ከቻለ የእግር ኳስ አድናቂ ለሆነ ማንም ሰው አስደናቂ ትዕይንት ነው።   

ለአሁኑ ግን ወሳኙና በቂው ነገር ሩኒ 250 ጎል ላይ መድረሱ ነው። ሞውሪንሆ ዛሬ ቡድናቸው በካርሊንግ ካፕ ከሁል በሚያደርገው ጨዋታ ቅዳሜው ከነበረው የተለየ አሰላለፍ ይዘው እንደሚመጡ በመናገራቸው ሩኒ የመሰለፍ እድል ላያገኝና ሪከርዱ ዛሬ ምሽት ላይሰበር ይችላል። 

ነገር ግን ቀጣዩ የኦልትራፎርድ የዩናይትድ ተጋጣሚ የምንግዜውም ተቀናቃኙ ሊቨርፑል ነው። ሩኒም በልጅነት ክለቡ (ኤቨርተን) እና በዩናይትድ ቤት እንደ ታላቅ ተፎካካሪ አድርጎ በሚመለከተው ክለብ ላይ ጎል አስቆጥሮ ሪከርዱን ቢሰብር ከምንም በላይ ያስደስተዋል።

Advertisements

ሚኪያስ በቀለ View All

ይህን ዘገባ ያቀረብኩላችሁ የኢትዮአዲስ ስፓርት ኤዲተርና ፀሀፊ እኔ ሚኪያስ በቀለ ነኝ።

%d bloggers like this: