Skip to content
Advertisements

የፊፋ የዓመቱ ምርጥ እግርኳስ ተጫዋች ሽልማት ሙሉ ዘገባ

በ ወንድወሰን ጥበቡ | ሰኞ ጥር 1፣ 2009 ዓ.ም

1:30‘ የፊፋ የዓመቱ ምርጥ ወንድ ተጫዋች የመጨረሻ አላፊ 23 ዕጩዎች እነዚህ ነበሩ።(በደማቅ ፅሁፍ የሰፈሩር የመጨረሻ ሶስት የፍፃሜ አላፊዎች ናቸው።) ሰርጂዮ አግዌሮ፣ ጋርዝ ቤል፣ ጂያንሉጂ ቡፎን፣ ክርስቲኖ ሮናልዶ፣  ኬቨን ደብሩይኒ፣ አንቶኒ ግሪዝማን፣ ዝላታን ኢብራሂሞቪች፣ አንድሪየስ ኢንየስታ፣ ን’ጎሎ ካንቴ፣ ቶኒ ክሩዝ፣ ሮበርቲ ሊቫንዶውስኪ፣ ሪያድ ማህሬዝ፣ ሌዮኔል መሲ፣ ሉካ ሞድሪች፣ ማኑኤል ኖየር፣ ኔይማር፣ መሱት ኦዚል፣ ዲሚትሪ ፓየ፣ ፖል ፖግባ፣ ሰርጂዮ ራሞስ፣ አሌክሲ ሳንቼዝ፣ ልዊስ ስዋሬዝ፣ ጄሚ ቫርዲ  

የሽልማት ስነስርዓቱ ለመጀመር ከግማሽ ሰዓት ያነሱ ጊዜያት ይቀራሉ።

2:00′ የሽልማቱ እጩ ተጫዋቾች በቀዩ ምንጣፎች ላይ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ፎቶግራፎችን በሚከተለው መልኩ ተነስተዋል።

ሮናልዶ ከፍቅረኛውና ከልጁ ጋር

ዚነዲን ዚዳን ከባለቤቱ ጋር

ዳኒ አልቬስ ከባለቤቱ ጋር

ሉካ ሞድሪች ከባለቤቱና ከልጆቹ ጋር

አንቶኒ ግሪዝማን

ሰርጂዮ ራሞስና ባለቤቱ

ማርሴሎ ከባለቤቱና ከልጁ ጋር

ቶኒ ክሩዝና ባለቤቱ

2፡25′ የሽልማት ስነስርዓቱ ላይ እንዲታደሙ የተጋበዙ ሁሉ ቦታ ቦታቸውን ይዘው የዝግጅቱን በይፋ መጀመር በመጠበቅ ላይ ናቸው።

2፡30′ የየሽልማት ስነስርዓቱ ተጀምሯል። የስነስርዓቱ ቀዳሚ ዝግጅት የፑሽካሽ (የኣመቱ ምርጥ ግብ) ሽልማት ዕጩዎችና የተቆጠሩት ድንቅ ግቦች ለተመልካች ታይተዋል። አሸናፊውም በድምፅ ብልጫ እንደሚሰበሰብ ለተመልካች ተገልፃ የድምፅ አሰጣጡ በይፋ መጀመሩ ተበስሯል።

2:42′ የዓመቱ ፊፋ ምርጥ 11 (fifa pro 11) የጫዋቾች ተመርጠው ተለይተዋል። በዚሁ መሰረት ኑየር፣ ፒኬ፣ ማርሤሎ፣ ራሞስ፣ አልቬስ ክሩዝ፣ ሞድሪች፣ ኢንየስታ፣ ስዋሬዝ፣ ሮናልዶና መሲ ሆነው ተመርጠዋል። በሽልማቱ ላይም ኑየር፣ ሞድሪች፣ ራሞስ፣ ሮናልዶ፣ ክሩዝ፣ አልቬስ ተገኝተው ሽልማታቸውን ሲቀበሉ የባርሴሎና ተጫዋቾች ግን አልተገኙም። ኢንየስታ በቀጥታ የቪዲዮ ስርጭት ሽልማቱን አስመልክቶ ንግግር አድርጓል።

2:50′ ቀጣዩ ሽልማት የዓመቱ  ምርጥ ደጋፊዎች ሽልማት ሲሆን በዚሁም መሰረት እጩ ከነበሩት አዶ ደንሃግ (የሆላንዱ ክለብ) ሊቨርፑል-ዶርትሙንድ ደጋፊዎች በጋራ እና የአይስላንድ ደጋፊዎች ነበሩ ሽልማቱን የኦሎምፒክ ሜዳሊያ ባለቤቷ አትሌት ኢሊየና ኢዘምባየባ የሰጠች ሲሆን በዚሁ መሰረት አሸናፊው ባለፈው የውድድር ዘመን በዩሮፓ ሊግ ጨዋታ ላይ አስገራሚ የሆነ ድጋፍ በጋራ ማሳየት ሽለው የነበሩት  የቦሩሲያ ዶርትሙንድና የሊቨርፑል ደጋፊዎች የሽልማቱ አሸናፊ ሆነዋል።

3:06‘ ቀጣዩ ሽልማት የፊፋ የዓመቱ ምርጥ ሴት አሰልጣኝ  ሽልማት ሲሆን ሶስቱ እጩዎች  ጂል ኢሊስ፣ ሲልቫ ናይድ እና ፒያ ሱንድሃግ ለተመልካች ከተዋወቁ እና በየግላቸው ንግግር ካደረጉ በኋላ የፊፋ የዓመቱ ምርጥ ሴት አሰልጠኝ የጀርመን ሴት ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ የሆኑት ሲልቪያ ናይድ አሸናፊ ሆነው ሽልማታቸውን ከቀድሞው የሆላንድ ተጫዋችና የባርሴሎና አሰልጣኝ ፍራንክ ራይካርድ እጅ ተቀብለዋል።

3:15′ በሽልማቱ በጉጉት የሚጠበቀው የፊፋ የ2016 ዓመት ምርጥ ወንድ ተጫዋች ሽልማት እጩ የነበሩት መሲ፣ ሮናልዶ፣ እና ግሪዝማንን በተመለከተ ከተመልካች የተሰበሰቡ አስተያየቶችና ስለተጫዋቾቹ አጭር ገለፃ ለመድረኩ ከተሰጠ በኋላ እጩ ተወዳዳሪዎች ወደመድረክ እንዲወጡ ቢቀርቡም ከሶስቱ ዕጩዎች መካከል መሲ ወደሽልማት ስነስርዓቱ ባለመምጣቱ (በባርሴሎና የትናንት ምሽት ጨዋታ የተነሳ) ሮናልዶና ግሪዝማን በየግላቸው መድረክ ላይ ንግግር አድርገዋል። 

3:18′ ቀጣዩ ሽልማት የፊፋ ስፖርታዊ ጨዋነት (ፌር ፕሌይ) አዋርድ ሽልማት ሲሆን ይህንን ሽልማትም የቀድሞው የባርሴሎና ተከላካይ ካርሎስ ፑዮል በቅርቡ በአውሮፕላን አደጋ አብዛኛው ተጫዋቾቹንና የቡድን አባላቶቹን ላጣው የብራዚሉ ክለብ ቻፖክዌንሴ የፍፃሜ ዋንጫውን አሳልፎ የሰጠው ለአትሌቲኮ ናሲዮናል ተሰጥቷል።

 3:25′ ተከትሎ በመድረኩ ላይ የተዋወቀው ሽልማት የፊፋ የዓመቱ ምርጥ የወንዶች አሰልጣኝ እጩ የነበሩት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊጉ ድንገተኛ ክስተትና አሸነፊ የሌስተሩ ክላውዲዮ ራኒየሪ፣ የሻምፒዮንስ ሊጉ ባለድል የሪያል ማድሪዱ ዚነዲን ዚዳንና የዩሮ 2016ቱ አሸናፊ የፖርቱጋሉ አሰልጣኝ ፈርናንዶ ሳንቶስ ያለፈው አመት ስኬት ለመድረኩ በምስል የተደገፈ አጭር ማብራሪያ ከተሰጠ በኋላ የቀድሞው አርጄንቲናዊው ታሪካዊ ተጫዋች ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና የአምናው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ ጣሊያናዊው አሰልጣኝ ክላውዲዮ ራኒየሪ መሆናቸውን አብስሮ ሽልማቱን አበርክቶላቸዋል።

3:32′ ዩክሬናዊው ድንቅ ተጫዋች አንድሬ ሼቪቼንኮ ወደመድረክ በመውጣት ብራዚላዊው የፉትሳል ድንቅ ጥበበኛ ለሆነው ፋልካኦ የፊፋን የአድናቆት ልዩ የብቃት ሽልማት አበርክቶለታል።

3:35′ በሽልማት ስነስርዓቱ መክፈቻ ላይ ከተመልካች ድምፅ እንዲሰበሰብበት ተዋውቆ በይፋ የተከፈተው የፊፋ የዓመቱ ፑሽካሽ (ምርጥ ግብ) ሽልማት ድምፅ ተሰብስቦ ካበቃ በኋላ በተሰበሰበው የህዝብ ድምፅ መሰረት በብራዚላዊ ኮከብ ትልቁ ሮናልዶ ሽልማት ሰጪነት ማለዢያዊው ተጫዋች ሞህድ ፊያዝ ሱብሪህ ከቅጣት ምት በአስገራሚ ሁኔታ ጠምዝዞ ባስቆጥራት ግብ ለሽልማት በቅቷል።

9:45′  በዚህ ሽልማት ላይ በጉጉት ከሚጠበቁት ሽልማቶች መካከል አንዱ የሆነው የፊፋ የዓመቱ ምርጥ ሴት ተጫዋች ሽልማት ሲሆን፣ ለዚህ ሽልማት የታጩት ሶስት ተጫዋቾች ሜላኒ በህሪንገር፣ ካርሊ ሎይድ እና ማርታ ለተመልካች ተዋውቀው ለሽልማቱ አርጄንቲናዊው ምርጥ አጥቂ ጋብሬል ባቱስቱታ ሽልማቱን ለአሸናፊው እንዲያበረክት ወደመድረክ ተጠርቶ ለአሸናፊዋ አሜሪካዊቷ ተጫዋች ካርሊ ሎይድ የፊፋ የዓመቱ ምርጥ ሴት ተጫዋች በሚል ሽልማቱን አበርክቶላታል።

9:50′ በመጨረሻም በእግርኳስ ተመልካቹ ዘንድ በእጅጉ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የፊፋ የዓመቱ ምርጥ ወንድ ተጫዋች ሽልማት እጩ የሆኑት አርጄንቲናዊው ሊዮኖ መሲ፣ ፓርቱጋላዊው ክርስቲያኖ ሮናልዶ እንዲሁም ፈረንሳዊው አንቶኒ ግሪዝማን ብቃታቸው ከተዋወቀ በኋላ በፊፋው ፕሬዘዳንት ጂያንሊ ኢንፋንቲኖ አብሳሪነት መሰረት በእጅጉ የተጠበቀው ክርስቲያኖ ሮናልዶ የዓመቱ የፊፋ ምርጥ ወንድ ተጫዋች አሸናፊ መሆኑ ተበስሯል፤ ሽልማቱንም ከፕሬዝዳንቱ እጅ ተቀብሏል።

ሮናልዶ ከሽልማቱ በኋላ በመድረክ ላይ የሚከተለውን ተናግሯል።

“ይህ የመጀመሪያዬ አይደለም። ነገር ግን ለዚህ ሽልማት ስበቃ ግን የመጀመሪያዬ ነው። 2016 ዋው። የቡድን አጋሮቼን ማመስገን እወዳለሁ። ማድረግ የምችለውን ነገር ማሳካት ችያለሁ።

“ድምፃቸውን ለሰጡኝ ለደጋፊዎቼ፣ ለሚዲያው ሁሉ ምስጋና ላቀርብ እወዳለሁ። ሌላ ምንም የማክለው ነገር የለም። ሽልማቱ በራሱ ስለእነሱ ይናገራል።

“የባርሴሎና ተጫዋቾች እዚህ አብረውን ስላልተገኙ አዝናለሁ። ነገር ግን ሁኔታው ይገባናል።” 

9:55′ በዚሁ መሰረት በስዊዘርላንድ ዋና ከተማ ዙሪክ ሲከሄድ የቆየው የፊፋ የዓመቱ ምርጥ የእግርኳስ ሽልማት ስነስርዓት ተጠናቋል። ዘገባውን በቀጥታ የፅሁፍ ዘገባ ወደእናንተ ያደረስኩት ወንድወሰን ጥበቡ ነበርኩ መልካም የእንቅልፍ ጊዜ ይሁንላችሁ። ደህና እደሩ!

Advertisements
%d bloggers like this: