Skip to content
Advertisements

ከውሳኔው በስተጀርባ: ገንዘብና ፓለቲካ የአለም ዋንጫን ማሽከርከሩን አሁንም ቀጥሏል

በሚኪያስ በ. ወርዶፋ| ረቡዕ ታህሳስ 3, 2009


ጂያኒ ኢንፋንቲኖ በፊፋ ምክር ቤት ፊት ቆመው ታላቁን የስፓርት ተቋም እንዲመሩ በአባላቱ መመረጣቸውን ባለማመን በግርምት ቆዝመው ከታዩ አመትም አልሞላቸው። ራሰ በርሀው ሰው ግን ታሪካዊ የሆነ ውሳኔን በፊፋ ምክር ቤት ለማስወሰን ብዙ ጊዜ ስልጣን ላይ መቆየት አላስፈለጋቸውም። ብዙዎችን ያስደነቀው ግን በሙስና ቅሌት በእገዳ ላይ የሚገኙትን የቀድሞውን የፊፋ አስተዳዳሪ ሴፕ ብላተርን የአለም ዋንጫ ተሳታፊ ሀገሮችን ቁጥር የማሳደግ ሀሳብ ወደ ተግባር መለወጥ መጀመራቸው ነው።

ይህ ውሳኔም ከዚህ ቀደም በፊፋ ውስጥ በነበረው የምርጫ ፓለቲካ መሰረት ኢንፋንቲኖ ተጨማሪ ሀገሮችን በማካተትና ውለታ በመስራት የአዳዲስ ተሳታፊ ሀገሮችን ድጋፍ በቀጣዩ ምርጫ የሚያገኙበት ይሆናል። ፊፋ እንደ ተቋም ደግሞ በውድድሩ ላይ 16 አዳዲስ ሀገር በቀል ገበያዎችን በመጨመር ከቴሌቭዥን ድርጅቶችና ከስፓንሰሮች ወደ 1 ቢሊየን ዶላር ተጨማሪ ገቢ በመፍጠር 640 ሚሊየን ዶላር የተጣራ ትርፍ ወደ ኪሱ ለመክተት አቅዷል።

ይህ የአዲሱ ገቢ መምጣት ደስታም ያለምንም ተቃውሞ ውሳኔው በሙሉ ድምፅ ባፀደቁት የፊፋ ምክር ቤት አባላት አይን ላይ ገና ከውሳኔው አሰጣጥ ስነስርአቱ በፊት በግልፅ ይነበብ ነበር። ኢንፋንቲኖም ባሳለፍነው የካቲት ሲመረጡ ወደ ፊፋ የሚገባው ብር የእያንዳንዱ አባል ሀገር መሆኑን ገልፀው አባል ሀገራቱን በመሸንገል ከ209 ድምፅ የአብዛኛውን ድጋፍ ለማግኘት ተጠቅመውበታል። በወቅቱ ከፊፋ እድገት እያንዳንዱ አባል ሀገር 5 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያገኝ ሲናገሩም ሁሉም ብሩ ከሆነ ቦታ በሆነ መንገድ እንደሚመጣ ያውቅ ነበር።

ስለዚህም የስዊዙ የእግር ኳስ ፓለቲከኛ ኢንፋንቲኖ ከሳቸው ቀደም ብለው የነበሩ የፊፋ ባለስልጣናት ይጠቀሙበት የነበረውን ‘የእከክልኝ ልከክልህ’ መንገድን በደንብ ለራሳቸው እንዲመች አድርገው እየተገበሩት ይገኛል።   

በ1974 የአለም ዋንጫ ተሳታፊዎችን ቁጥር አሳድጋለሁ ብለው ቃል በመግባት ጆ ሀቫላንጅ ፊፋን እንዲመሩ ተመረጡ። ሌላኛው የቀድሞ የፊፋ ፕሬዝዳንት ሴፕ ብላተር ደግሞ በ 1988 ለሚመርጧቸው የፊፋ አባል ሀገራት የእግር ኳስ ልማት ማስተግበሪያ የገንዘብ ፈሰስ እንደሚያደርጉ በማሳመን በአለም የእግር ኳስ አስተዳዳሪው አካል ሀላፊነት ላይ የነበራቸውን የስልጣን ዘመን ለተጨማሪ 17 አመታት ማስቀጠል ቻሉ።

ዢን-ማሪ ፋውስቲን ጎዴፍሮይድ “ጆኣ” ደ ሃቨላንጅ  ከ1974-1998 ድረስ የቆዩ ሰበተኛው የፊፋ ፕሬዝዳንትነት ናቸው

ስለ አዲሱ ውሳኔ ተቃውሟቸውን የገለፁት የአውሮፓ ክለቦች ማህበር ሊቀመንበር ካርል ሄንዝ ሩሚንጌ ” ስለ ስፓርት አሁንም ትኩረት መስጠት መጀመር አለብን። ፓለቲካና ንግድ የእግር ኳስ ብቸኛ ተቀዳሚ ነገሮች መሆን የለባቸውም።” በማለት ነው።
የአውሮፓ እግር ኳስ ግን ይህን አዲስ ውሳኔ በጠነከረ ሁኔታ ሲቃወምና በሁኔታው ሲያፌዝ ማየት ትርጉም የለሽ ይሆናል። ለአውሮፓ ሀብታም ክለቦች ፍላጎት መሳካት የቆመውና የማህበሩን ሊቀመንበር የሚመሩት ክለብ (ባየርሙኒክ) እንኳን በ2015-16 የውድድር ዘመን 627 ሚሊዮን ዩሮ ያፈሰበት የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር የፊፋ ውሳኔ በዋነኛነት ‘ንግድ’ ላይ ያተኮረ ነው ብሎ ሲቃወም ማየት ደስ አይልም።  

የቀድሞው የፊፋ ፕሬዘደንት ጆሴፍ ሴፕ ብላተር (1998-2015)

አውሮፓውያን እየተቃወሙት ያለው ውሳኔም የራሳቸው የአውሮፓ ክለቦችም በተመሳሳይ የሚፈፅሙትና መቆሚያ የሌለውን የቴሌቪዥን ስፓንሰርሺፕ ቅኝ ግዛታቸውን ለማስቀጠልና የክለቦቻቸው ውድ ተጫዋቾች በጨዋታ ብዛት እንዳይጎዱ በሚል በክረምት ወቅት ብዙ ጨዋታ እንዳይኖራቸው ለማድረግ ከሚከላከሉበት ጥቅመኛ አሰራራቸው ተለይቶ አይታይም። 

አለም ዋንጫ የእግር ኳስ ታላቁና ታሪካዊ ውድድር ለመሆን የራሱን ሚና ቢጫወትም ከሚያሳትፋቸው ቡድኖች ቁጥር ጋር በተያያዘ ሁሌም ፓለቲካ ነክ አጀንዳ አይጠፋውም። ለምሳሌ አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት ነፃ መውጣት በቻሉበትና እግር ኳሳቸውን ለማሳደግ ደፋ ቀና ባሉበት የመጀመሪያዎቹ አመታት አለም ዋንጫው የአውሮፓውያን የተሳትፎ መድረክ ብቻ እንዲሆን መደረጉ ትልቅ ቅሬታ አሳደረባቸው። 

ለ1966 የእንግሊዝ አለም ዋንጫም ከተሳታፊ 16 ሀገሮች የአፍሪካና እስያ ኮታ አንድ (የሁለቱ አህጉራት ቡድኖች በእርስ በርስ ጨዋታ ተጋጥመው የሚያልፋበት) ብቻ እንዲሆን በመደረጉ የአፍሪካ ሀገራት ራሳቸውን ከማጣሪያ ውድድሩ አገለሉ።    

የሀቫላንጅ ቃልኪዳን የተፈፀመው የውድድሩ ተሳታፊ ሀገሮች ቁጥር በ 1982 ወደ 24 እንዲያድግ በተደረገበት ወቅት ሲሆን ለእግር ኳስ ልማት ለአባል ሀገራት የሚሰጠው ገንዘብም እድገት ያሳየው እግር ኳስን በአለም አቀፍ ደረጃ ለማስፋፋትና ተጨማሪ ገንዘብ ለመሰብሰብ በፊፋ አዲስ እቅድ በመነደፉ ነበር።

በ1998 የተሳታፊ ሀገሮች ቁጥር በድጋሚ በስምንት ጨምሮ 32 መሆን ቻለ። የዚህ እድገት መነሻውም ተመሳሳይ የሆነና የምርጫ ፓለቲካውና የገንዘቡ ቃልኪዳን ያመጣው ነው። በወቅቱ አሁን በስራ ላይ ያለው የ32 ተሳታፊ ሀገሮች የአለም ዋንጫ ቅርፅ ሲመጣ ውድድሩን የሚያረዝምና የተበላሸ የምድብ አጨዋወት ያለው ነው በሚል የተቃወሙት ነበሩ።  

አሁን ደግሞ የአውሮፓ የውድድሩ ተሳታፊ አገሮች አሁንም በበላይነት በሚቀጥሉበት ሁኔታ ወደ ከ 2026 ጀምሮ የተሳታፊዎች ቁጥር ወደ 48 እንዲያድግ በፊፋ ምክር ቤት ተወስኗል። የፊፋን አላማ በጥልቀት በማያውቁ በተለያዩ የአለም ክፍሎች ውሳኔው ለአዳዲስ ሀገሮች እድል ይሰጣል በሚል ሲወደስ ከአውሮፓ አባል ሀገራት ግን ትልቅ ውግዘት ገጥሞታል። 

የእንግሊዝ እግር ኳስ ማህበር (FA) ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆኑት ማርቲን ግሌን ውድድሩን በትንሽ ተሳታፊ ሀገሮች ማስቀጠል እንደሚገባ ገልፀዋል። የአፍሪካዊቷ ሀገር ናይጄሪያ የእግር ኳስ ማህበር (FA) ፕሬዝዳንት አማጁ ፒኒክ በበኩላቸው ሰዎች በአዲሱ ውሳኔ መደነቃቸውን ገልፀው የተሳታፊ ቁጥር ሲጨምር የውድድሩ ውበት ይበልጥ እንደሚጨምር ያላቸውን ተስፋ ገልፀዋል። 

የእንግሊዝ እግርኳስ ማህበር ዋና ስራአስፈፃሚ ማርቲን ግሌን

በመጨረሻም አሁን አራት ቢሊየን የተመልካች ቁጥር ያለውና ኮካኮላ፣ አዲዳስና ሌሎች ግዙፍ አጋሮችን ከጎኑ የያዘው አለም ዋንጫ ተጨማሪ 16 ሀገሮችን አካቶ ሌላ ተጨማሪ አዙሪት ይዞ ይመጣል። ምክንያቱም ዘመናዊ አለም ሁሉም ነገር የንግድና ፓለቲካ ውጤት በመሆኑ ነው። አዲሱ የፊፋ ፕሬዝዳንትም ሁኔታው እስከ አጥንታቸው ዘልቆ ታውቋቸዋል።   

Advertisements

ሚኪያስ በቀለ View All

ይህን ዘገባ ያቀረብኩላችሁ የኢትዮአዲስ ስፓርት ኤዲተርና ፀሀፊ እኔ ሚኪያስ በቀለ ነኝ።

%d bloggers like this: