Skip to content
Advertisements

​ሴኔጋል – የስብስቡ አባላት፣ የውድድሩ ተሳትፎ ታሪክ፣ በውድድሩ የሚጠበቅባት ስኬት እና ሌሎች መረጃዎች


በሚኪያስ በ. ወርዶፋ | ረቡዕ ጥር 3፣ 2009 ዓ.ም

ሴኔጋል በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ በሳዲዮ ማኔ፣ ቼኩ ኩዬቴ፣ ዲያፍራ ሳኮ እና ፓፓ ሶሬ አይነት ድንቅ ተጨዋቾች እየተመራች ዋንጫን ለማግኘት በማለም ወደ ጋቦን ታመራለች፡፡ ሴኔጋል ሁሌም አስደናቂ ውጤት ማምጣት ታውቅበታለች፡፡ ይህንን ለማወቅ በ2002 አለም ዋንጫ በዚዳን ትመራ የነበረችውን ፈረንሳይ የረታችበትን አጋጣሚ ማስታወሱ በቂ ነው፡፡ 
የሊቨርፑሉ አጥቂ ሳዲዮ ማኔ

የሴኔጋል ወሳኝ ተጫዋቾች እነማን ናቸው?

1. ሰይዱ ማኔ፣ የክንፍ ተጫዋች/አጥቂ፣ (ሊቨርፑል)

ማኔ ባሳለፍነው ክረምት ከሳውዝአምፕተን አንፊልድን ከተቀላቀለበት ጊዜ ጀምሮ በብቃቱ ብዙዎችን ማሳመን የቻለና በዚህ ውድድር ከሚጠበቁ ኮከቦች አንዱ ነው፡፡ በዚህ የውድድር ዘመንም ለመርሲሳይዱ ክለብ 9 የሊግ ጎሎችን ማስቆጠር ችሏል፡፡ 

2. ሄነሪ ሳቪየት፣ አማካኝ፣ ሴንት ኢትዬን (ከኒውካስትል በውሰት)

በእንግሊዝ ሊግ ተከታታዮች በኒውካስትል ቤት በነበረው ደካማ እንቅስቃሴ ሊታወስ ይችላል፡፡ ነገር ግን ሳቪየት በፈረንሳዩ ክለብ እንደገና መታደስ ችሏል፡፡ ዘንድሮ የፈረንሳዩ ቡድን በአውሮፓ ሊግ ለነበረው የምድብ ግጥሚያ ስኬትም ተጫዋቹ ትልቅ እርዳታ አድርጓል፡፡ 

3. ቼኩ ኩዬቴ፣ የመሀል አማካኝ፣ ዌስትሀም

ኩዬቴ በዌስትሀም ቤት ስሙን ማፃፍ የቻለው በአዲሱ የለንደን ስታዲየም ግብ በማስቆጠር ነው፡፡ ምንም እንኳን መዶሻዎቹ ዘንድሮ በሜዳቸው እየተፈተኑ ቢሆንም ኩዬቴ ተፅዕኖ አሳዳሪና ባለ ጥሩ ብቃት ተጫዋች መሆን ችሏል፡፡ 

የዌስትሃሙ አማካኝ ቺኩ ኩዬቴ

የሴኔጋል የአፍሪካ ዋንጫ ተጫዋቾች ስብስብ

በረኞች፡ አብዱላዪ ዲያሎ (ሳይኮር ሬዚስፑር/ቱርክ)፣ ካዲም ኒዲያዬ (ሆሮያ ኤሲ/ጊኒ)፣ ፓፔ ሴዱ ንዲያዬ (ኤንጂቢ ታሊ/ሴኔጋል)

ተከላካዮች፡ ላሚን ጋሳማ (አልናዝቡር/ቱርክ)፣ ካራ ምቦድጂ (አንደርሌክት/ቤልጄም)፣ ዛርጎ ቱሬ (ሎርየንት/ፈረንሳይ)፣ ካሊዱ ኩሊባሊ (ናፖሊ/ጣሊያን)፣ ሳሊዪ ሲስ (ቫሌንሲነስ/ፈረንሳይ)፣ ቼክ ምቤንጉ (ሴንት ኢቴን/ፈረንሳይ)

አማካኞች፡ ኢድሪሳ ጉዬ (ኤቨርተን/እንግሊዝ)፣ ቼኩ ኩዬቴ (ዌስትሀም/እንግሊዝ)፣ ሼኪ ንዱዬ (አንገርስ/ፈረንሳይ)፣ ፓፔ ኩሊ ዲዮፕ (ኤስፓኞል/ስፔን)፣ ፓፔ አልዌን ንዳዬ (ኦስማንልስፑር/ቱርክ)፣ ሙመድ ድያሜ (ኒውካስትል/እንግሊዝ)፣ ሄነሪ ሳቪዬት (ሴንትኢቴን/ፈረንሳይ)

አጥቂዎች፡ ሙሳ ኮንቴ (ኤፍሴ ሲዮን/ስዊዘርላንድ)፣ ፋማራ ዴዲሁ (አንገርስ/ፈረንሳይ)፣ ሙሳ ሶው (ፈነርባቼ/ቱርክ)፣ ማሜ ቢራም ዲዩፍ (ስቶክ ሲቲ/እንግሊዝ)፣ ሳዲዮ ማኔ (ሊቨርፑል/እንግሊዝ)፣ ኬይታ ባልዴ (ላዚዮ/ጣሊየን)፣ ኢስማዬላ ሳራ (ሜትዝ/ፈረንሳይ)

የዌስትሃሙ አጥቂ ዲያፍራ ሳኮ

ሴኔጋል እንዴት ለውድድሩ ለማለፍ በቃች?

ሴኔጋሎች ምስጋና ለሳዲዮ ማኔና ማሜ ዲዩፍ ጎሎች ይግባና ብሩንዲን ከሜዳቸው ውጪ 2-0 በማሸነፍ የጋቦን ተሳታፊነታቸውን አረጋግጠዋል፡፡ በእርግጥም ሴኔጋሎች ስድስቱንም የምድብ ጨዋታ በማሸነፍና በሙሉ 18 ነጥብ ነበር ለውድድሩ የበቁት፡፡
የሴኔጋል አሰልጣኝ ማን ናቸው?

የቀድሞው አማካኝ አሊዩ ሲሴ በ2015 በአራት አመት ኮንትራት የሴኔጋልን ቡድን እያሰለጠ የሚገኝ ሲሆን የአሰልጣኝነት ቆይታው ግን በዚህ ውድድር ላይ በሚያስመዘግበው ስኬት የሚወሰን እንደሆነ ታውቋል፡፡ 
የሴኔጋል የአፍሪካ ዋንጫ ታሪክ ምን ይመስላል?

ሴኔጋል ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ ዋንጫ መሳተፍ የቻለችው አራተኛ ሆና ባጠናቀቀችበት የ1965 የአፍሪካ ዋንጫ ነው፡፡ የሴኔጋል የውድድሩ ምርጥ ውጤት በ2002 ለፍፃሜ ደርሳ በካሜሮን በፍፁም ቅጣት ምት ተረታ ዋንጫውን የተነጠቀችበት ጊዜ ነው፡፡ 
በውድድሩ ላይ ከሴኔጋል ምን ይጠበቃል? 

ከአይቮሪኮስት በመቀጠል ሴኔጋል የውድድሩ ተገማች ሀገር ስትሆን በቡድኑ ውስጥ ያለው ስሜትና ልምድ ምንም ነጥብ ሳይጥሉ እስከ ፍፃሜ እንደሚደርሱ ተስፋ እንዲጣልባቸው ምክንያት ሆኗል፡፡ አብዛኛው ነገር ግን የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ኮከቦቻቸው በሚያሳዩት ብቃት ላይ የሚወሰን ይሆናል፡፡

Advertisements
%d bloggers like this: