Skip to content
Advertisements

​አልጄሪያ – የስብስቡ አባላት፣ የውድድሩ ተሳትፎ ታሪክ፣ በውድድሩ የሚጠበቅባት ስኬት እና ሌሎች መረጃዎች


በሚኪያስ በ. ወርዶፋ | ረቡዕ ጥር 3፣ 2009 ዓ.ም

የሌስተር ሲቲ ተጫዋች በሆኑት ሪያድ ማህሬዝና ኢስላም ስሊማኒ የምትመራው የበረሀዋ ቀበሮ አልጄሪያ ዋንጫውን በ 27 አመት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ሀገሯ መውሰዷ ቢያጠራጥርም የውድድሩ ድንገቴ ክስተት ልትሆን ትችላለች፡፡ 

የዌስትሃሙ አማካኝ ሶፊያን ፌጉሊ

የአልጄሪያ ወሳኝ ተጫዋቾች እነማን ናቸው?

1. ሪያድ ማህሬዝ፣ አማካኝ፣ ሌስተር

ማህሬዝ ለሀገሩ ከ2014 ጀምሮ መሰለፍ የቻለ ሲሆን ሀገሩንም በ2014 በአለም ዋንጫና በ2015 አፍሪካ ዋንጫ መወከል ችሏል፡፡ ከሊሀርቬይ በ400,000 ፓውንድ ብቻ የእንግሊዙን ክለብ የተቀላቀለው ተጫዋች በ2015-16 የሊጉ የውድድር ዘመን ኮከብ ተጫዋች መሆን ችሏል፡፡ በተመሳሳይ አመትም የአልጄሪያ የአመቱ ምርጥ ተጫዋች ተሸላሚ መሆን ችሏል፡፡

ሪያድ ማህሬዝና ያሲን ብራሂሚ

2. ኢስላም ስሊማኒ፣ አጥቂ፣ ሌስተር

ስሊማኒ ባሳለፍነው ክረምት ወደ ሌስተር ሲቀላቀል የእንግሊዙን ክለብ 28 ሚሊዮን ፓውንድ ወጪ ያስወጣ ሲሆን ከበርንሌይ ጋር በነበረው ግጥሚያም ሁለት ጎሎችን ለማስቆጠር ችሏል፡፡ ለሀገሩ በተሰለፈበት 46 ጨዋታ 23 ግቦችን ማስቆጠር የቻለ ሲሆን በ 2014 የብራዚሉ አለም ዋንጫ ደቡብ ኮሪያና ሩሲያ ላይ ጎል አስቆጥሯል፡፡ 

የሌስተሩ አጥቂ ኢስላም ሲሊማኒ

3. ሶፊያን ፌጉሊ፣ አማካኝ፣ ዌስትሀም

ፌጉሊ ለመጀመሪያ ጊዜ አልጄሪያን ወክሎ መጫወት የቻለው በየካቲት 2012 ነው፡፡ ሀገሩንም በ2013 እና በ2015 የአፍሪካ ዋንጫ እንዲሁም በ2014 አለም ዋንጫ መወከል ችሏል፡፡ የዌስትሀሙ አማካኝ እስካሁን አልጄሪያን በመወከል 42 ጨዋታዎችን አድርጎ 11 ጎሎችን አስቆጥሯል፡፡ 

የአልጄሪያ የአፍሪካ ዋንጫ ተጫዋቾች ስብስብ

በረኞች፡ አሴላህ ማሊክ (ጄኤስ/ካባይሊ)፣ ምቦሊህ ራይስ (አንታላስፑር/ቱርክ)፣ ራህማኒ ቼምሴዲን (ኤምኦ/ቤጃያ)

አማካኞች፡ ሞክታር ቤልክሂተር (ክለብ አፍሪካ/ቱኒዚያ)፣ ሞሀመድ ራቢ ሚፍታህ  (ዩኤስም አልጀር/አልጄሪያ)፣ አይሳ ማንዲ (ሪያል ቤትስ/ስፔን)፣ ኪክሀም ቤልካሩሂ (ኤስፔራንሴ/ቱኒዚያ)፣ ሊያሲን ካዳሙሮ (ሴርቬት ጄኔቫ/ ስዊዘርላንድ)፣ ሞሀመድ ቤንያሂ (ዩኤስም አልጀር/አልጄሪያ)፣ ራሚ ቤንስባኒ (ስታዴ ሬንስ/ፈረንሳይ)፣ ፎውዚ ጎህላም (ናፖሊ/ጣሊያን)፣ ጃሜል ኤዲን ሚስባህ (ኤፍሲ ክሮተን/ጣሊያን)

አማካኞች፡ አድሌን ጉድዮራ (ዋትፎርድ/እንግሊዝ)፣ ሳፊር ታይደር (ቦሎኛ/ጣሊያን)፣ ናቢ ቤንታሌብ (ሻልክ 04/ጀርመን)፣ መሀዲ አቤይድ (ዲጆን/ፈረንሳይ)፣ ያሲን ብራሂሚ (ኤፍሲ ፖርቶ/ፖርቹጋል)፣ ራሺድ ጌዛል (ኦሎምፒክ ሊዮን/ፈረንሳይ)

አጥቂዎች፡ ኢስላም ስሊማኒ (ሌስተር/እንግሊዝ)፣ ሪያድ ማህሬዝ (ሌስተር/እንግሊዝ)፣ ሂላል ሳውዳኒ ኤል አረቢያ (ዲያናሞ ዛግሬብ/ክሮሺያ)፣ ባግዳድ ቦንድጃህ (አልሳድ/ኳታር)፣ ሶፊያን ሀኒ (አንደርሌክት/ቤልጄም)

አልጄሪያ እንዴት ለውድድሩ ለማለፍ በቃች?

አልጄሪያ ለውድድሩ የበቃችው የመጨረሻ የማጣሪያ የምድብ ጨዋታዋን ሲሸልስን 2-0 በሆነ ውጤት በመርታት ነበር፡፡ አሁን በአፍሪካ ዋንጫው ላይ በምድብ ‘ለ’ ከዚምቧቤ፣ ቱኒዚያና ሴኔጋል ጋር ተደልድላለች፡፡ 

የአልጄሪያ አሰልጣኝ ማን ናቸው?

የ62 አመቱ የቡድኑ አሰልጣኝ ሚሎቫን ራጄቪክ በ2010 የአፍሪካ ዋንጫ የጋና ብሄራዊ ቡድንን ለአፍሪካ ዋንጫ ፍፃሜ ማብቃት የቻሉ ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ጥቋቁሮቹ ንስሮችን ለ2010 የአለም ዋንጫ የሩብ ፍፃሜ ደረጃ ማብቃት ችለዋል፡፡ በሳውዲ አረቢያው ክለብ አልአህሊ የነበራቸው ቆይታ ግን ስኬታማ አልነበረም፡፡ 

ሚሎቫን ራጄቪች

የአልጄሪያ የአፍሪካ ዋንጫ ታሪክ ምን ይመስላል?

አልጄሪያ ውድድሩን ባዘጋጀችበት የ1990 የአፍሪካ ዋንጫ ባለ ድል ነበረች፡፡ ከዛ በመለስ በነበሩት ውድድሮች ግን ከሩብ ፍፃሜ መሻገር አልቻለችም፡፡ በ1996፣ 2000፣ 2004፣ እና 2015 የመጨረሻ ስምንት ቡድኖች ውስጥ መግባት ችላለች፡፡ 

በውድድሩ ላይ ከአልጄሪያ ምን ይጠበቃል? 

አይቮሪኮስትና ሴኔጋልን የመሳሰሉ ጠንካራ ሀገሮች ባሉበት በዚህ ውድድር አልጄሪያ ለዋንጫ ባትገመትም እንደ ከዚህ ቀደሙ የሩብ ፍፃሜ ቦታን እንደማታጣ ተስፋ ተጥሎባታል፡፡

በ2015 ለሩብ ፍፃሜ መድረስ የቻለው የአልጄሪያ ቡድን

Advertisements
%d bloggers like this: