Skip to content
Advertisements

ዩናይትድ ከ ሊቨርፑል: የሃገረ እንግሊዝ ታላቁ የደርቢ ትንቅንቅ

የታላቁ ጨዋታ ትንቅንቅ

በሚኪያስ በ. ወርዶፋ | እሁድ ጥር 7, 2009

1. ሁለቱ ክለቦች በሊጉ የምንግዜም ስኬታማ ቡድኖች መሆናቸው

ዩናይትድና ሊቨርፑል ፕሪምየር ሊጉ ላይ ላለፉት 41 አመት ነግሰውበታል። በእነዚህ ረጅም አመታት ከቢል ሻንክሌይ  የ 1973 ድል ጀምሮ እስከ ፈርጉሰን የ 2013 የመጨረሻው የሊግ ዋንጫ ድረስ 24 የሚሆኑት የሊጉ ዋንጫዎች ከሁለቱ ክለቦች ወደ አንዱ አምርተዋል። በነዚህ ጊዜያት የሁለቱ ክለብ ተቀናቃኝ የሆኑት አርሰናልና ቼልሲ በነዚህ ጊዜያት የሊጉን ዋንጫ ማንሳት የቻሉት ዘጠኝ ጊዜ ብቻ ነው። ከነሱ ውጪ ሊድስና ኤቨርተን ብቻ ከአንድ ጊዜ በላይ በሊጉ ላይ መንገስ የቻሉ ቡድኖች ናቸው።

ሁለቱ ቡድኖች ያለፉትን አራት አመታት ከሊጉ ዋንጫ ስኬት ቢርቁም አሁንም ግን የሁለቱም የሊግ ስኬት ግን መቀነስ አልቻለም። ምክንያቱም ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ አጨራረስ ላይ አሁንም ትልቅ ተፅዕኖ እያደረጉ ነው። በቀጣዮቹ አስርት አመታትም ይህ ተፅዕኖዋቸው እንደሚቀጥል እርግጥ ይመስላል።   

2. ሁለቱም የአውሮፓ ስኬታማ ክለቦች መሆናቸው 

በሊጉ ላይ እንዳላቸው የዋንጫ ልዩነት በአውሮፓ መድረክም በሁለት ዋንጫዎች ብቻ ይበላለጣሉ። በአገር ውስጥ ውድድር ዩናይትድ 20-18 በሆነ የዋንጫ ስኬት ሲመራ የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ላይ ሊቨርፑል ከተከታዩ ዩናይትድ ሶስት ዋንጫ በሁለት በልጦ የአምስት ዋንጫ ስኬትን አስመዝግቧል። 

ከዩናይትድ የዋንጫ ካዝና የተወሰኑት

ታላቁ የቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ለ 12 ጊዜያት ወደ እንግሊዝ ክለቦች አምርቷል። ከነዚህ ስምንት የሚሆኑት በሁለቱ የሰሜን ምዕራብ ታላላቅ ክለብ አምበሎች እጅ ላይ አርፏል። ከእንግሊዝ የሁለቱ ባላንጣዎች ቅርብ ተቀናቃኝ በ 1970ዎቹ ዋንጫውን ሁለት ጊዜ ያነሳውና አሁን በታችኛው ዲቪዚዮን የሚገኘው ኖቲንግሀም ፎረስት ብቻ ነው። &

ከሊቨርፑል የዋንጫ ካዝና የተወሰኑት

በሌላ መልኩ ስንገልፀውም ባለ ‘ትልቅ ጆሮው’ ዋንጫ ለስምንት ጊዜያት በሰሜን ምዕራብ ሲሽከረከር፣ ሶስት ጊዜያት ወደ ሚድላንድ ያመራ ሲሆን አንድ ጊዜ ብቻ በቼልሲ ጥረት ለንደን ላይ ተገኝቷል።

3. በትንቅንቁ የተሳተፉበት እንደሚያምኑት

የቀድሞና የአሁን ተጫዋቾች እንዲሁም አሰልጣኞች የሰሜን ምዕራቡን ትንቅንቅ ትልቅነት ለመግለፅ አፍረው አያውቁም። ከጥቂት አመታት በፊት ስቴቨን ጄራርድ በባርሴሎናና ማድሪድ መሀከል የሚደረገው የላሊጋው ደርቢ ጨዋታ የዚህን ያህል ትልቅ እንዳልሆነ ተናግሯል። ጄራርድ በወቅቱ “የባርሳና ማድሪድ ትንቅንቅ ላሊጋው ላይ ሊኖር ይችላል። ለኔ ትልቁ ጨዋታ የሊቨርፑል ከ ዩናይትድ ነው። ምክንያቱም ፕሪምየር ሊጉ የአለማችን ታላቁ ሊግ ነው። ሁለቱ ቡድኖችም በጣም ስኬታማ ክለቦች ናቸው።” ሲል ተናግሯል።

በተመሳሳይ በአንድ ወቅት አሌክስ ፈርጉሰንም የሁለቱን ቡድኖች ትንቅንቅ ለመግለፅ “አቻ የሌለው” የሚል ቃልን ተጠቅመዋል። ፈርጉሰን በወቅቱ “በእኛና በሊቨርፑል መካከል ያለው ትልቅ ባላንጣነት ነው። ባላንጣነቱም አቻ የሌለው ነው። ሁለቱም ቡድኖች በእንግሊዝ ምድር በስኬት አቻ የሚሆናቸው ክለብ የለም። ለዚህም ነው እርስ በርሳችን በትልቅ ባላንጣነት የምንፈላለገው።” ሲሉ የደርቢውን ትልቅነት ገልፀውታል። 

ከላይ ለመሰሉት በጨዋታው ዙሪያ ለተነገሩ ከባድ ንግግሮችም የጨዋታው ላይ ጥቂት ምስሎችን ማየት ሺህ የሚደርሱ ቃላትን የሚተካ ሲሆን የሁለቱ ቡድኖች ተጫዋቾች በደርቢው ላይ ግብ ሲያስቆጥሩ የሚያሳዩት የደስታ አገላለፅም እንደ ልቦለድ ታሪክ ያለውና እየተገለጠ መነበብ የሚችል ነው። 

የካራገርና ኔቭል ጠብ የደርቢው ትንቅንቅ አንዱ ማሳያ

እንደ ጋሪ ኔቭልና ጂሚ ካራገር ወይም ደግሞ ሪያን ጊግስና ስቴቨን ጄራርድ አይነቶች ደግሞ ይህ ጨዋታ ለእነሱ ምን ያክል ታላቅ እንደሆነ ለአለም ለማሳየት ብዙ ቃላትን ከመጠቀም ይልቅ እውነተኛውን ትንቅንቅ በሜዳ ላይ ማሳየት ይመርጣሉ።

4. ደጋፊዎቹና ሚዲያው እንደሚያምነው

የተለያዩ የእግር ኳስ አፍቃሪዎች የራሳቸውን ከተማ ደርቢዎች ከዚህኛው ደርቢ በላይ ሊያስቀምጡ ይችሉ ይሆናል። ነገር ግን በራሳቸው ከተማ ደርቢና በዚህ መሀከል የሚያስቀምጡት ልዩነቱ በጣም ጥቂት ነው። 

የውድድሩ አመቱ መርሀ ግብር ሲወጣም እነዚህ ወገንተኛ ደጋፊዎቹ ከሁለቱ ጨዋታ አንዱን ለመመልከት ምርጫቸው ሊያደርጉ ይችሉ ይሆናል።  በእርግጠኝነት ግን የሰሜን ምዕራብ ለንደኑ ደርቢ በሚዲያውና ወገንተኛ ባልሆኑ እግር ኳስ ተመልካቾች ዘንድ ተቀዳሚ ተመራጭ ነው። 

5. እርስ በርስ ባላቸው ትንቅንቅ ምክንያት 

የዛሬው ተጠባቂ ትንቅንቅ በምስል ሲገለፅ

ማንኛውም ሰው አንድን ክለብ ትልቅ በሚያስብለው መመዘኛ ዙሪያ የራሱ አስተሳሰብ አለው። ነገር ግን የነዚህ ሁለቱ ክለቦች ትልቅነት በማንም ሰው ሊካድ የማይችል ነው። ዩናይትድ በቅርቡ ከአዲዳስ ጋር ሪከርድ የሆነ የ 750 ሚሊዮን ፓውንድ የማሊያ ስምምነት ማድረግ የቻለ ነው። ሊቨርፑሎች ደግሞ ዳግም ወደ ቻምፒዮንስ ሊግ በተመለሱበት የ 2014/15 የውድድር ዘመን ትልቅ የማሊያ ስፓንሰርሺፕ ገቢ እድገት አስመዝግበዋል።

በእንግሊዝ ያለው የቴሌቪዥን ገቢም በሊጉ በየአመቱ በሚገኘው ውጤት ላይ የተመሰረተ ሳይሆን እንደ አንዳንድ የአውሮፓ ክለቦች የክፍፍል መንገድ በታሪክና በትልቅነት ላይ የሚመሰረት ቢሆን ኖሮ ሁለቱ ክለቦች ተቀዳሚ ተከፋዮች ነበሩ።

ድጋፍ ደግሞ ሌላውና ሁለቱ ክለቦች በአለም ዙሪያ የሚመኩበት ሀብታቸው ነው። ከአመታት በፊት ሁለቱ ክለቦች ለቅድመ ውድድር ዝግጅት የወዳጅነት ጨዋታ ወደ አውስትራሊያ ባመሩበትና ጨዋታ ባደረጉበት ወቅት 180,000 የሚደርሱ ደጋፊዎች በስታዲየሙ ዙሪያ ተገኝተው የነበረ ሲሆን አብዛኛዎቹም የስታዲየም ትኬት አጥተው ኮከቦቻቸውን ማየት ሳይችሉ በቅሬታ ወደ ቤታቸው ተመልሰዋል። ሁለቱ ክለቦች ይህን ተወዳጅነታቸውን የእግር ኳስ ባህል አነስተኛ በሆነበት አሜሪካን ሲሄዱም ሁሌ ያጋጥማቸዋል።

በአለም ላይ ያለውን አጠቃላይ የሁለቱ ደጋፊዎች የደጋፊ ብዛት ብንመለከት ደግሞ ዩናይትድ ከ 650 ሚሊዮን በላይ ደጋፊ በመያዝ ከአለም አንደኛ ሆኖ ከየትኛውም የአለም ክለቦች በላይ መቀመጥ የቻለ ነው። ሊቨርፑልም በተመሳሳይ በአለም ላይ በብዙ ሚሊየኖች የሚደገፍ ተወዳጅ ክለብ ነው። 

6. የፉክክሩ ግለት መጠን 

በኤቨርተንና ሊቨርፑል መሀከል የሚደረገው የደርቢ ጨዋታ ከዩናይትድና ሊሸርፑል አንፃር ሲታይ የወዳጅነት ሊባል ይችላል። ይህም ቀልድ ለመፍጠር የተባለ ሳይሆን መሬት ላይ ባለው ሀቅ ላይ የተመሰረተ ነው። ኤቨርተንና ሊቨርፑል ባይቀበሉትም ሁለቱ የመርሲሳይድ ክለቦች ከሚለያያቸው ነገር ይልቅ የሚያመሳስላቸው ነገር ይበዛል። 

የሚረር ጋዜጣ አምደኛው ብሪያን ሬዲ ሁለቱ የመርሲሳይድ ክለቦች ባደረጉት የ 1985 የኤፍኤ ዋንጫ ጨዋታ ምን ያህል ወዳጅ ክለቦች መሆናቸውን በገለፀበት ፅሁፋ “በየመንገዶቹ ላይ የመሀከለኛው ዘመንን የሚያሳዩ የደጋፊ ጩኸቶች ነበሩ። የስታንሊ ቢላዎች ኤግዚቢሽን በስታንሊን ስታዲየም አቅራቢያ ተካሂዶ ነበር። ከዛ ውጪ ግን በጋዛ ድንበር በመጥፎ ቀን የሚታየው አይነት የጎሰኝነት ስድድብ ነው በደጋፊዎች ላይ የሚታየው።” ሲል ቀለል አድርጎ ፅፏል። የዩናይትድና የሊቨርፑል ትንቅንቅ ግን ከዚህ በጣም የተለየና ብዙ ከባባድ ትዕይንቶችን ማሳየት ጀምሮ በከባባድ ሂደቶች የሚጠናቀቅ ነው።

7. ጨዋታዎቹ በራሳቸው 

የሰሜን ምዕራብ ደርቢ አወዛጋቢ ነገር ሁሌም የማያጣው ነው። የዳኞች ውሳኔ ምንም ቢሆን ከትችት አይፀዳም። በጨዋታው ላይ የሚመዘዝ እያንዳንዱ ትክክለኛ ቀይ ካርድ በደጋፌዎች ተቀባይነት የለውም። በጨዋታው ላይ መመዘዝ ያለበት አንዳንድ ቀይ ካርድ ደግሞ ሳይመዘዝ በዝምታ ይታለፋል። በሜዳው መስመር ላይ ደግሞ ትልቅ መዋከብ ይኖራል። 

በዚህ ሁሉ መሀከል ግን ሁለቱም ቡድኖች ደጋፊው የሚጠብቅባቸውን ያማረ አጨዋወት፣ የተዋቡ ቅብብሎችና ግሩም ግቦችን ለማስቆጠር ሲሰንፋ አይታይም። ለዚህም በዩናይትድ ደጋፊዎች በኩል የአይርዊንን የ 93/94፣ የስኮልስን 93/94 ወይም ደግሞ የቤካምን የ 96/97 ያማሩ የደርቢ ጎሎች ማስታወሱ በቂ ነው። በሊቨርፑላውያን ዘንድ ደግሞ የፎውለር የ 95/96 የጄራርድ 00/01 ወይም የመርፊ የ 01/02 ግሩም ጎሎች ከትውስታቸው የሚጠፋ አይነት አይደለም። 

በአጠቃላይ ከላይ ባሉትና በሌሎች በጣም ብዙ ምክንያቶች ዛሬ ምሽት ለ 198ኛ ጊዜ የሚደረገው የሰሜን ምዕራብ እንግሊዙ ደርቢ ከሌሎቹ በእንግሊዝ ምድር ከሚደረጉ የደርቢ ጨዋታዎች በላይ መቀመጥ ችሏል። በቀጣዮቹ አመታትም ከደረጃው ዝንፍ የሚያደርገው ሌላ የደርቢ ጨዋታ መከሰቱ የማይሆን ነገር ይመስላል። 

Advertisements

ሚኪያስ በቀለ View All

ይህን ዘገባ ያቀረብኩላችሁ የኢትዮአዲስ ስፓርት ኤዲተርና ፀሀፊ እኔ ሚኪያስ በቀለ ነኝ።

%d bloggers like this: