Skip to content
Advertisements

አንድ ጥያቄ አለኝ: የአፍሪካ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድኖች የቅፅል ስሞቻቸው መሰረት ምንድን ናቸው? 

በሚኪያስ በ. ወርዶፋ | ሰኞ ጥር 8, 2009 


በአፍሪካ እግር ኳስ ቅፅል ስም አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ ጥቅም ላይ ይውላል። ​ቅፅል ስም ለደጋፊዎች ቡድኖችን በቀላሉ ለመለየት ብቻ ሳይሆን ተጨዋቾችን ለማነሳሳትና ከተቃራኒው ቡድን እንደሚበልጡ እንዲሰማቸው ለማድረግም ጭምር ነው። 

በአውሮፓ ግን ሁኔታው ከአፍሪካ በእጅጉ የተለየ ነው። ቡድኖች ቅፅል ስም ሲያወጡ ቀላል እንዲሆን አድርገው ነው። ለምሳሌ የጣሊያን ብሄራዊ ቡድን ‘አዙሪ’ በሚል ቅፅል ስም ይጠራሉ። ትርጉሙም ሰማያዊዎቹ ማለት ነው። ጀርመኖች ደግሞ ‘ዳይ ሜንሻፍት’ በሚባለውና ቡድኑ የሚል ትርጓሜ ባለው ቀላል ቅፅል ስም ይታወቃሉ። 

አፍሪካ ግን የቅፅል ስም መብቀያ ለምለም መሬት ናት። አህጉሪቷ ውስጥ ትልቅ የእግር ኳስ ባህል ተፈጥሯል። ይህንንም የአህጉሪቱ ትልቅ የእግር ኳስ መድረክ በሆነው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ቅፅል ስሞችን የየሀገራቱ ተጫዋቾችና ደጋፊዎችና እራሳቸውን ከመግለፅ ባሻገር ክብራቸውን ሀያልነታቸውን ለመግለፅ ሲጠቀሙበት በማየት ማረጋገጥ ይቻላል።  

የአፍሪካ ቡድኖችን ቅፅል ስም ይበልጥ ለየት የሚያደርገው ደሞ በሀገራቸው በሚገኙ የገንዘብ ኖት ስያሜዎችና እንስሳቶች እንዲሁም ሌሎች መሰል መግለጫዎች መታጀቡ ነው። 

            የገንዘብ ኖቶችና እንስሳት 

የ 1976 አፍሪካ ዋንጫ የፍፃሜ ተፋላሚ የነበረችው ጊኒ ‘ሲሊ ናሽናሌ’ በሚል ቅፅል ስም ትታወቃለች። ‘ሲሊ’ የሚለው ቃል ሱሱ ከሚሰኝ የጊኒ ቋንቋ የመጣ ሲሆን ትርጉሙም ዝሆን ማለት ነው። 

የጊኒ ቅፅል ስምም በምዕራብ አፍሪካ ሰሜን ምስራቅ ክልል ከሚገኙ ዝሆኖች ጋር በተያያዘ የተሰጠ ስያሜ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ስያሜው ትልቅ ትርጉም አለው። ምክንያቱም ደግሞ ሀገሪቱ ከ 1971 – 1985 ትጠቀምበት የነበረው የገንዘብ መጠሪያ ኖት በዚህ ስያሜ ይጠራ ስለነበር ነው። 

ነገር ግን ጊኒ የግዙፉን እንስሳ ስያሜ ብትይዝም እስካሁን ድረስ የአህጉሪቱ ትልቁ ዋንጫ የሆነውን አፍሪካ ዋንጫ ለማግኘት አለመታደሏ ስያሜው የከበዳት አስመስሏታል። 

የዛምቢያን ቅፅል ስም ስንመለከት ደግሞ ‘ቺፓሎፓሎ’ ወይም  የመዳብ ጥይቶች ይሰኛል። የቃሉ መነሻም ኪትዌ ከሚገኘው የመዳብ ማውጫ የተወሰደ ነው። ከዚህ ቀደም በሀገሪቱ መስራች ፕሬዝዳንት ኬኔት ካውንዳ ስም ‘ኬኬ11’ ተብሎ ይጠራ የነበረው የዛምቢያ ብሄራዊ ቡድን በ 1993 የሀገሪቱን ታላቅ የንግድ ስፍራ ለማስተዋወቅ ሲባል አስፈሪ የሆነውን የጥይት ቅፅል ስም እንዲይዝ ተደርጓል።

የባለ መዳብ ጥይቱ ዛምቢያ ብሄራዊ ቡድንም ከፊቱ ያገኛቸውን ደረት ደረታቸውን ብሎ እያጋደመ የ 2012 አፍሪካ ዋንጫ የበላይነትን በማረጋገጥ የስያሜውን ትርጉም ጥንካሬ አሳይቷል። 

                       መነሳሻ

ደቡብ አፍሪካዎች በ 1992 ወደ አለም አቀፍ ጨዋታዎች ዳግም ከተመለሱ በኃላ በጋዜጠኛ ሲቡሲሶ መሴልኩ ‘ባፋና ባፋና’ የሚል ተቀፅላ ስም አገኙ። ትርጉሙም ‘ልጆቹ ልጆቹ’ የሚል ነበር። 

በወቅቱ ከአፓርታይድ በ 1994 ነፃ ወጥተው የነበሩት ደቡብ አፍሪካውያን የወቅቱ የእግር ኳስ ብሄራዊ ቡድናቸውን ‘ሂዱ ልጆች፣ ሂዱ ልጆች’ እያሉ እያበረታቱና ድጋፍ እየሰጡ በሜዳቸው ላይ የ 1996 አፍሪካ ዋንጫን ማንሳት ቻሉ። 

በወቅቱ ስያሜው ከአፓርታይድ ወጥታ እንደ አዲስ እየተመሰረተች ለነበረችው ሀገር ግንባታ ጥሩ ቢሆንም የስያሜው ትርጓሜ ግን ከታችኛው ከአዲሲቷ ሀገር የመጡ ልጆች በወቅቱ ከነበሩት ታላላቅ የአፍሪካ ቡድኖች ጋር ያለ አቅማቸው የሚፎካከሩበት ያልተመጣጠነ ፍልሚያ አስመስሎት ነበር።   

በሌላ በኩል ‘የማይበገሩት አንበሶች’ የሚለው የካሜሮን ተቀፅላ ስም ሁሌም ጠንካራ፣ ግዙፍና በአካል ብቃት ላይ ያተኮረ ቡድን ይዛ በየውድድሩ ለምትቀርበው ካሜሮን ትክክለኛ ስያሜ ነበር። በወቅቱ ካሜሮን ይህን በጫካው ንጉስ የተሰየመ ተገቢ ስያሜ ልታገኝ የቻለችው ሀገሪቱ በወቅቱ በነበራት ከፍተኛ የአንበሳ ጥብቃና እንክብካቤ ስራዎች ምክንያት ነበር። 

የካሜሮን ብሄራዊ ቡድን እስከ 1972 የአፍሪካ ዋንጫ ድረስ የሚጠራው አንበሶቹ በሚል ተቀፅላ ብቻ ነበር። ነገር ግን በሜዳው በተደረገው ውድድር ሶስተኛ መውጣቱ የከነከናቸው የወቅቱ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት አህመዱ አሂዲጆ ብሄራዊ ቡድኑን ለቀጣይ ውድድሮች በስነልቦና በኩል ለማነሳሳት በማሰብ የማይበገሩት አንበሶች የሚል የተሻሻለ ስያሜ ሰጡት።

ከዛ ወዲህም ካሜሮኖች አዲሱ ስያሜ የአትላስ አንበሶች ወይም የታራንጋ አንበሶች የተሰኙትን የሞሮኮና የሴኔጋል ብሄራዊ ቡድኖችንና ሌሎች መሰል ባለ ጠንካራ ስም ቡድኖችን ለመቋቋም ብርታት ሆኗቸዋል። የማይበገሩት አንበሶችም በ 1984፣ 1988፣ 2000 እና 2002 የአፍሪካ ዋንጫን ለአራት ጊዜያት ከፍ አድርገው ማንሳት ችለዋል።

                     የነብር ቆብ

በቀድሞው አጠራሯ ዛየር የምትሰኘው የዛሬዋ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ጎንጎ ነብሮቹ በሚለው ተቀፅላ ስያሜ እየተጠራች የ 1968 እና የ 1974 አፍሪካ ዋንጫን ማንሳት ችላለች። በወቅቱ የብሄራዊ ቡድኑ ቀንደኛ ደጋፌ የነበሩት የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሞቦቱ ሴሴኮ በሀገራቸው የሚገኘውን ነብር ለማስታወስ ሲሉ ታዋቂ የሆኑበትን በነብር ቆዳ የተሰራ ቆብ (ኮፍያ) ያደርጉ ነበር።  

ሞቦቱ ሴሴኮ ከስልጣን ከወረዱ በኃላ በ 1997 የብሄራዊ ቡድኑ ስያሜ ወደ ‘ሲምባስ’ ወይም ደግሞ አንበሶቹ ወደሚል ስያሜ ተቀየረ። ነገር ግን በ 2006 ሀገሪቱ ባፀደቀችው ህገ-መንግስት የቡድኑ የቀድሞ ስያሜ የሆነው ነብሮቹ እንዲመለስ ተደረገ።    

በ 1974 አለም ዋንጫ በመካፈል የመጀመሪያው የአፍሪካ ቡድን የሆነው የደቡብ ሰሀራው ብሄራዊ ቡድንም በነዚህ አመታት ለአራት ጊዜያት ያህል የቅፅል ስም መቀያየር አጋጥሞታል።  

ከ 1960 እስከ 1965 አንበሶቹ በመባል ሲጠሩ ቆዩና በ 1965 ነብሮቹ የሚለውን ስያሜ አግኝተው እስከ 1997 በዛው እየተጠሩ ዘለቁ። ይህ ስያሜም ይለብሱት በነበረው ማሊያ እጅጌ ላይ ጭምር ሰፍሮ ነበር። ከዚህ በኃላም ለሁለት ጊዜያት የብሄራዊ ቡድኑ መጠሪያዎች ተቀያይረዋል። 

ጥቋቁሮቹ ኮከቦች ደግሞ በጋና ባንዲራ ላይ የሚገኘውን ብቸኛው ኮከብ የሚያመለክትና ለቡድኑ ደጋፊዎች ብቸኛ ኮከብ ለሆኑት የጋና ብሄራዊ ቡድን አባላት መታሰቢያ የተሰጠ ስያሜ ነው። የምዕራብ አፍሪካዎቹ ጋናዎችም ከዚህ ቀደም ለአራት ጊዜያት የአፍሪካ ዋንጫን ማሸነፍ ችለው ለአምስተኛው ስኬት በአምበላቸው አሳማዋ ጂያን እየተመሩ አምስተኛ ስኬት ለማስመዝገብ በማሰብ ጋቦን ደርሰዋል።

ስለ ቅፅል ስማቸው በአንድ ወቅት በአልጀዚራ ስፓርት የተጠየቀው አሳማዋ ጂያን “ጥቋቁሩ ኮከብ የብቃታችን መለያ ነው። በእግር ኳስ እንደ አንፀባራቂ ኮከብ የምንቆጠርና የጨዋታዎች የበላይ ነን። ልክ ኮከብ ያለውን ማሊያ ስታጠልቅ ለሀገርህ መሞት ትመኛለህ። ይሄ ከቅፅል ስማችን ጋር አብሮ የመጣ ኩራትና መነሳሻ ነው።” ሲል በስሜት ተውጦ የጥቋቁሮቹ ኮከቦችን ትርጉም አስረድቷል።

የውድድሩ ተገማች ሀገር አይቮሪኮስቶች በበኩላቸው ‘ዝሆኖቹ’ የሚለውን ተቀፅላ በ 19ኛው ክፍለ ዘመን ያካሂዱት ከነበረው የዝሆን ቀንድ ንግድ ወርሰዋል። አንዳንዶች ግን በ 1992 እና 2015 ለሁለት ጊዜያት ብቻ ዋንጫ ላነሱት አይቮሪኮስቶች ከእንስሳት ግዙፍ የሆነውንና የሚፈራውን ‘ዝሆን’ ስያሜው ማግኘታቸው እንደሚበዛባቸው በመናገር ወቀሳ ያቀርቡባቸዋል።

                ያንቀላፋት ትላልቆች 
የአፍሪካ ዋንጫው ላይ ለሰባት ጊዜያት መንገስ የቻሉት የሰሜን አፍሪካዎቹ ግብፆች የበላይነት፣ ስልጣኔን፣ ማንነትንና ትልቅ ታሪክን በጉልህ በሚያንፀባርቀው ‘ፈርኦኖቹ’ በሚለው አንድ ነጠላ ቃል ይጠራሉ።  

በዚሁ ሁሉ መሀከል ግን በተቀናቃኞቿ ላይ ፈሪያ እግዚያብሄርን የሚያሳድር ከባድ ቅፅል ስም የያዘችው የአፍሪካ ዋንጫው ባለ ታሪክ ሀገር ከ 2010 ድል በኃላ ላለፋት ሶስት ውድድሮች ማለፍ ሳትችል ቀርታ ከሰባት አመት ማንቀላፋት በኃላ ዳግም ዘንድሮ ወደ ውድድሩ ለመጀመሪያ ጊዜ ተመልሳለች።

ሌላዋ ባለ ታሪክ ሀገር ናይጄሪያዎች ደግሞ በሚለብሱት ማሊያ እጅጌ ላይ ባለው ንስር ቅፅል ስም ይጠራሉ። ናይጄሪያዎች ከ 1988 በፊት አረንጓዴዎቹ ንስሮች እየተባሉ ይጠሩ የነበረ ሲሆን በ 1988 የአፍሪካ ዋንጫ ፍፃሜ በካሜሮን የደረሰባቸው ሽንፈት ግን ለውጤታቸው ማማር መነሳሻ በሆናቸው ‘ልዕለ ንስሮች’ በሚል አዲስ ስያሜ እንዲቀይሩ አስገድዷቸዋል። 

ከስም ቅያሬው በኃላም ደካማ አጀማመራቸውን ቀልብሰው ለአምስት አለም ዋንጫዎች ማለፍ ሲችሉ ለሶስት ጊዜያትም ለውድድሩ የጥሎ ማለፍ ደረጃ መብቃት ችለዋል። በአፍሪካ ዋንጫ ውድድርም ሶስት ዋንጫዎችን ለማንሳት በቅተዋል። 

እስካሁን ካየነው እንደምንረዳውም ቅፅል ስም በአፍሪካ እግር ኳስ ውስጥ መዝናኛና ቡድኖችን በቀላሉ መለያ ብቻ ሳይሆን በጨዋታዎች ላይ ከማይጠፋትና የጨዋታው ዋና መሰረቶች ከሆኑት ደጋፊዎች እና ከእጃቸው ከማይለዩት የጨዋታው ማድመቂያ ከበሮዎች ቀጥሎ ወሳኝ ነገር መሆኑን ነው።  

Advertisements

ሚኪያስ በቀለ View All

ይህን ዘገባ ያቀረብኩላችሁ የኢትዮአዲስ ስፓርት ኤዲተርና ፀሀፊ እኔ ሚኪያስ በቀለ ነኝ።

%d bloggers like this: