Skip to content
Advertisements

ውዝግብ: የዲያጎ ኮስታ የዛሬው የልምምድ ውሎና ቀጣዩ የቼልሲ ቆይታው

በሚኪያስ በ. ወርዶፋ | ማክሰኞ ጥር 9, 2009
ከሰሞኑ ውዝግብ ላይ የነበረውና ከቡድኑ ተቀንሶ የነበረው ዲያጎ ኮስታ ዛሬ ወደ ቡድኑ ተመልሶ ከዋናው ቡድኑ ጋር ልምምድ ሲሰራ የሚያሳዩ ምስሎች ይፋ ሆነዋል። የተለያዩ የእንግሊዝ ሚዲያዎችም ዛሬ አመሻሹ ላይ የአንባቢን ቀልብ ይስብልናል የሚሉትን ርዕሶች ተጠቅመውና በፎቶ አጅበው የተጫዋቹን መመለስ በከፍተኛ ደረጃ እየዘገቡት ይገኛል። 

የእንግሊዙ ዘ ሰን ጋዜጣ ከዋነኞቹ አንዱ ነው። ይህ ተነባቢ ጋዜጣ ተጫዋቹ ወደ ቡድኑ መመለሱንና ባሳለፍነው ሳምንት ከኮንቴ በፊት ግጭት ውስጥ ገብቶባቸው ከነበሩት የአካል ብቃት አሰልጣኝ ጋር መታረቁን የሚገልፅ ፅሁፍ ከምስሎች ጋር አያይዞ ይዞ ወጥቷል። 

እንደ ጋዜጣው ዘገባ የሊጉ ኮከብ ግብ አግቢ ወደ ልምምድ ዳግም በመመለሱ መደሰቱንና የክለቡን የአካል ብቃት አሰልጣኝ የሆኑትን ጁሊዮ ቶውስን ከልቡ ባይሆንም እንኳ ለሚዲያ ፍጆታና ውዝግቡን ለማርገብ ሲል ሲያቅፍና ሲስማቸው እንደነበር ታይቷል። ከዚህ በተጨማሪ የክለቡ አለቃ አንቶኒዮ ኮንቴም የእንኳን ደህና መጣህ አቀባበል አድርገውለታል። 

ቶውስ ያለፈውን ጊዜ በመርሳት ስፔናዊውን አጥቂ ወደ ራሳቸው ሳብ በማድረግ ሲያቅፉት ታይተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ጋዜጣው ለእሱ ብቻ የደረሰ ምስል መሆኑን በገለፀበት አንድ ምስል ኮስታ በኮብሀም የልምምድ ማዕከል ከቼልሲ የቡድን አባላት ጋር ለማውራት ከልምምድ ሜዳው ወደ ዳር ወጣ ባለበት ወቅት ቶውስ ልዩነታቸውን ወደ ጎን ትተው ኮስታን ወደራሳቸው ስበው ሲያቅፉት ታይተዋል። 

የክለቡ ምክትል አሰልጣኝ ካርሎ ኩዲቺኒ፣ የአካል ብቃት አሰልጣኝ የሆኑት ጋሪ ጆንስና የቡድኑ ተከላካይ ጋሪ ካሂል በፎቶው ላይ ከሚታዩ የሰማያዊዎቹ ስብስቦች የተወሰኑት ናቸው። ኮስታ ከእርቅ ማውረዱ በኃላ ከጆን ቴሪ፣ ከኤደን ሀዛርድ፣ ከኒጎሉ ካንቴ፣ ከዊሊያምና ከሌሎች የቡድን አጋሮቹ ጋር ጠንካራ ልምምድ ሲሰራ ታይቷል።

በመጨረሻ ግን ዘ ሰን ለለንደኑ ክለብ አስደንጋጭ የሆነ መረጃ ይፋ አድርጓል። እንደ ጋዜጣው ዘገባ ከሆነ የቻይናው ሱፐር ሊግ ክለብ ቲያንጂን ኳንጂን የተጫዋቹ ወኪል ከሆነው ጆርጌ ሜንዴዝ ጋር መነጋገሩንና ተጫዋቹን ለማዘዋወር አማላይ የሆነ ሳምንታዊ 570,000 ፓውንድ ደሞዝ እንዳቀረበለት ፅፏል።

ጋዜጣው ከክለቡ ሰማሁ ብሎ ጨምሮ እንደፃፈው ሜንዴዝ የቻይናው ክለብ ሊቀመንበር የሆኑት ዩሂ ቤት ማምራቱንና ክለቡ በመጀመሪያ የፒኤስጂውን አጥቂ ኤዲሰን ካቫኒን ለማስፈረም ፈልጎ የነበረ ቢሆንም የፈረንሳዩ ክለብ ተጫዋቹ ከሀምሌ በፊት ከክለቡ እንደማይለቅ ለክለቡ ባለስልጣናት ስለነገራቸው ፊታቸውን ወደ ኮስታ ማዞራቸውንና ነገር ግን እሱም በተመሳሳይ ከሀምሌ በፊት እንደማይለቅ በማመናቸው ስፔናዊውን አጥቂ ለማስፈረም የመጨረሻ ሙከራ ለማድረግ ማሰባቸውንና የእሱ ዝውውር ካልተሳካማ ቤንዜማን ጨምሮ ሌላ አጥቂ ለማስፈረም መጣራቸው እንደማይቀር ታውቋል። 

በሌላ በኩል በትናንትናው እለት ዘገባው አንቶኒዮ ኮንቴ ከኮስታ ጋር ዛሬ ማክሰኞ ችግሩን ለመፍታት ይነጋገራል ከሚለው መረጃ በተቃራኒ ጣሊያናዊው አሰልጣኝ ከአጥቂው ጋር እንደማይነጋገርና የኮስታ ችግር ተጫዋቹ እራሱ በመጪው ጊዜያት በሚያሳየው ባህሪ እንደሚወሰን የፃፈው የእንግሊዙ ዘ ጋርዲያን ጋዜጣ ግምቱ ሰምሮለታል። 

በዚህም መሰረት ኮንቴ ስፔናዊውን ተጫዋች ለብቻው ማናገር ሳያስፈልገው ተጫዋቹን ወደ ቡድኑ በመቀላቀል የተጫዋቹን ባህሪ መሰረት አድርጎ ችግሩን ለመፍታት ማሰቡ ዛሬ ታይቷል። እንደ ጋዜጣው መረጃ ከሆነም የኮስታ ሰሞነኛ ፍላጎት ማጣትና ግጭት ውስጥ መግባት የተፈጠረው ከጀርባ ጉዳቱ ጋር በተያያዘ ሳይሆን ዋናው መሰረቱ ከቻይናው ክለብ የቀረበው የዝውውር ጥያቄ መሆኑንም ክለቡ መረዳቱ ታውቋል።

ኮስታ ወደ ልምምድ በዚህ መልክ ነበር የመጣው።

ኮስታ በዛሬው እለት ወደ ልምምድ ሊመለስ የቻለውም  ከጉዳቱ ማገገሙን በማረጋገጡና በተደረገለት ምርመራ ሲሆን ኮስታም የተጫዋቹ ባህሪ መሻሻልን ካመነበት በሚቀጥለው እሁድ በሌስተሩ ጨዋታ ግሩም ጥምረት መፍጠር ከቻሉት ዊሊያምና ፔድሮ አንዱን አሳርፎ ዳግም ወደ ጨዋታ እንደሚመልሰው ተገልጿል። 

በሌላ በኩል ግን ተጫዋቹ ከመጪው ክረምት በኃላ በክለቡ የመቆየት እድሉ አነስተኛ ሲሆን ከቻይናው ክለብ በተጨማሪም የኮስታ የቀድሞው ክለብ የሆነው አትሌቲኮ ማድሪድ ፈላጊው መሆኑ ታውቋል። ይህንን የተገነዘቡት ቼልሲዎቹም ኮስታን በጥሩ ድርድር በመሸጥ በምትኩ የሪያል ማድሪዱን አጥቂ አልቫሮ ሞራታን የረጅም ጊዜ ተተኪ ለማድረግ ማሰባቸው ተነግሯል። ከሞራታ በተጨማሪም የኤቨርተኑ ሮሚዮ ሉካኩና የክሪስታል ፓላሱ ክርስቲያን ቤንቴኬም ስፔናዊውን አጥቂ ለመተካት ትልቅ ግምት የሚሰጣቸው ናቸው።

ዘ ጋርዲያን በመጨረሻም ከዘ ሰን ጋር በተቀራረበ መልኩ የቻይናው ቲያንጂን የቼልሲውን አጥቂ ለማስፈረም የሄደበትን መንገድ አብራርቶ በመጨረሻም ክለቡ በቅርቡ የቻይና ክለቦች ከውጪ የሚያመጧቸውን ተጫዋቾች እንዲቀንሱ የሚያስገድድ ደንብ ከወጣው ወዲህ ውድ ዝውውሮችን ለመቀነስ ማሰባቸውን ፅፏል።

ነገር ግን ከተለያዩ የዜና ምንጮች እንደሚሰማው ኮስታ በመጪው ክረምት ወደ ቻይና ማምራቱ የማይቀር ይመስላል።  

Advertisements

ሚኪያስ በቀለ View All

ይህን ዘገባ ያቀረብኩላችሁ የኢትዮአዲስ ስፓርት ኤዲተርና ፀሀፊ እኔ ሚኪያስ በቀለ ነኝ።

%d bloggers like this: