Skip to content
Advertisements

“ፓግባ እየተጓዘበት ያለው መንገድ ከዲፔይ የቁልቁለት መንገድ ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ ሊጠነቀቅ ይገባዋል።” – ሩድ ጉሌት

ከሜዳ ውጪ ተግባራት በፊት ለስራው ትኩረት እንዲሰጥ እየተመከረ ያለው ፓግባ

በሚኪያስ በ. ወርዶፋ | እሁድ ጥር 14, 2009

የሆላንዱ ዝነኛ ተጫዋች ሩድ ጉሌት ፓል ፓግባ የጀመረው መንገድ ከሜንፈስ ዲፔይን የቁልቁለት ጉዞ ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ተናገረ። ጉሌት ፍራቻውን በገለፀበት ንግግሩ በ 89 ሚሊዮን ፓውንድ ዩናይትድን የተቀላቀለው ፈረንሳዊው ኮከብ ከአስፈላጊ ነገሮች ይልቅ የታይታ ስራዎችን እያስቀደመ መሆኑንና ይህም ከትልቅ ተጫዋች የማይጠበቅ መሆኑን ተናግሯል።

የዜናው ምንጭ ሚረር እንደገለፀው ከሰሞኑ ቅንጦት በማብዛቱና ብቃቱ እንደተጠበቀው መሆን ስለተሳነው በ 25 ሚሊዮን ፓውንድ የዩናይትድን ቤት የተሰናበተው ሜምፈስ ዲፔይን በማስታወስ ፋሽን መከተልን አቁሞ እግር ኳስ ላይ እንዲያተኩር ጉሌት ለተጨዋቹ ያስተላለፈውን መልዕክት ፅፏል።

ፓግባ የራሱን የአዲዳስ አልባሳት በዲዛይን አሰርቶ መልበስ የጀመረ ሲሆን ከሰሞኑ ደግሞ በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ተጫዋቾች ዘንድ የመጀመሪያ የሆነውን በራሱ ስም ፊደል የተወከለ የቲውተር ምልክት ይፋ አድርጓል ። ጉሌት ስለ ሁኔታው ለጋዜጣው ሲናገርም “ፓግባ ሜምፈስ ዲፔይ በዩናይትድ ቤት በተጓዘበት ተመሳሳይ መንገድ እየሄደ ነው።

“የአለም ውዱ ተጫዋች ሊሆን ይችላል። ነገር ግን አብዛኛውን ጊዜውን በአለባበሱ፣ በፀጉሩ ቀለምና በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚያጠፋ ከሆነ ትልቅ ተጫዋችነቱ ዋጋ አይኖረውም። ፓግባ ሜምፈስን ቢጠይቀው በእንግሊዝ እግር ኳስ ስኬታማና ትልቅ ተጫዋች መሆን የሚቻለው በየሳምንቱ ጠንክሮ መጫወትና ሁሉንም ትኩረት ለስራው በመስጠት መሆኑን ይረዳል።

ገፅታ ግንባታ የዩናይትድ ቤት እድሜውን እንደሚያሳጥረው ቢወራም ፓግባ የቲውተር ምልክት በስሙ ተቀርፃለት የሜዳ ውጪ ተፅዕኖው እያየለ ሄዷል።

“ሜምፈስ በትልቅ ደረጃ ወቀሳ ውስጥ የገባው የእግር ኳስ ችሎታውን ከማሻሻል ይልቅ ለራሱ ገፅታ በመጨነቁ ነው። በሜዳ ላይ የሚኖረው ነገር ከሁሉ ነገር ቀዳሚ መሆኑን ማወቅ ነበረበት። ፓግባ በዚህ ሁኔታ የሚቀጥል ከሆነ የደጋፊዎችን ወቀሳ ማግኘቱ አይቀርም። ክለቡን ለቆ እንዲሄድም መጮህ ይጀምራሉ።

“የአለም ትልልቅ የእግር ኳስ ኮከቦች እራሱ ለክለባቸው ጥሩ ብቃት ማሳየት ከሁሉም ነገር በላይ ቀዳሚ መሆኑን እንዲረዱ የሚያዝ ትልቅ ያልተፃፈ ህግ አለ። ይሄ የኔ ምክር ነው።” ብሏል።

ጉሌት የቀድሞው ፌይኖርድ፣ ፒኤስቪ አይንዶቨን፣ ኤሲ ሚላን፣ ሳምፕዶሪያና ቼልሲ ኮከብ ሲሆን የኒውካስትል ክለብንም ማሰልጠን ችሏል። ይህ ሆላንዳዊ እንደሚያምነው ዛላታን ኢብራሂሞቪችን ለፓግባ ትክክለኛ ምሳሌ መሆን የሚችል ተጫዋች ነው። በእርግጥም ጉሌት ጆሴ ሞውሪንሆን ከእሳቸው ቀደም ከነበሩት ዴቪድ ሞይስና ሊውስ ቫንሀል እጣ የታደጋቸው የዛላታን ጎሎች መሆናቸውን ያምናል።

ጉሌት ስለ ሁኔታው የሚሰማውን ሲናገርም “የአሌክስ ፈርጉሰን ራዕይ በጣም ጉልህ ነው። ከእሳቸው በኃላ ለመጡት ዴቪድ ሞይስና ቫንሀል በጣም ትልቅ ነበር። ሁለቱም በፈርጉሰን ራዕይ ተጠልፈው ወድቀዋል። ጆሴ ሞውሪንሆም የናይትድን ወደ ቀደመ የፈርጉሰን ታላቅ ቦታው ለመመለስ ተቸግረው ታይተዋል።

“ነገር ግን ባለፋት ሳምንታት የቡድኑ ውጤት ተሻሽሏል። ለዚህ መሻሻልም ትልቁን ሀላፊነት የተወጣው ኢብራሂሞቪች ነው። እሱ ትልቅ ስራን ሰርቷል። ሀላፊነቱን ተቀብሎም ብቻውን መሸከም ችሏል። ከዛ በላይ ደግሞ በሚያገባቸው ጎሎችና በላቀ የጨዋታ የበላይነቱ ጠቃሚ ተጫዋች መሆኑን አሳይቷል” ሲል ሆላንዳዊው ንግግሩን ቋጭቷል።

Advertisements

ሚኪያስ በቀለ View All

ይህን ዘገባ ያቀረብኩላችሁ የኢትዮአዲስ ስፓርት ኤዲተርና ፀሀፊ እኔ ሚኪያስ በቀለ ነኝ።

%d bloggers like this: