Skip to content
Advertisements

የገንዘብ ቀውስ : አተርፍ ባይ አጉዳይ የሆነው አትሌቲኮ ማድሪድና እድል የቀናው ማንችስተር ዩናይትድ 

ግሪዝማንና ሳውል የክለቡን የገንዘብ ቀዳዳ ለመድፈን ሲባል በመጪው ክረምት ሊሸጡ ይችላሉ።

በሚኪያስ በ. ወርዶፋ | ሰኞ ጥር 15, 2009የስፔኑ ክለብ ከሶስት አስርት አመታት በፊት ቪሴንቴ ካልዴሮንን ለቆ በከተማው ሌላኛ አቅጣጫ ወደሚገኘው የቀድሞው ስታዲየሙ ላ ፒየንታ እንደሚያመራ ይፋ አድርጎ ነበር። ነገር ግን ከገንዘብ፣ ከህጋዊነትና ከአቅርቦት ጋር በተያያዙ ችግሮች ምክንያት ተጓቶ ቆይቷል። ነገር ግን በቅርቡ የክለቡ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሚጉዌል አንጌል ጂል ማሪንና ፕሬዝዳንቱ ኤነሪክ ሴሬዞ የቻይና ኢንቨስተሮችንና ሜክሲኳዊውን ቢሊየነር ካርሎስ ስሊምን በእቅዱ ውስጥ በማካተት በ2017/18 የውድድር ዘመን በቶሎ ወደ አዲሱ ስታዲየም ለመዘዋወር የሚያስፈልገውን የግንባታ ብር ማግኘት ችለዋል።

የዚህ ለስታዲየሙ ወጪ የተገኘው ገንዘብ ጉዳይ ለህዝቡ ሙሉ ለሙሉ ግልፅ አልተደረገም። ነገር ግን ውስጥ ለውስጥ በተደረገ ድብቅ ምርመራ ከስሊም ባንክ የተገኘው 160 ሚሊዮን ዩሮ በቶሎ መከፈል ካልቻለ ሜክሲኳዊው ባለሀብት በክለቡ ድርሻ እንደሚኖራቸው ታውቋል።

ሴናሌስ ደ ሁሞ የተሰኘው የደጋፊዎች ቡድን መሪ የሆነው ጆሴ ሊውዝ ሳንቼዝ እንደሚገልፀው ከሆነ የአትሌቲኮ የገንዘብ ቀውስ ክለቡ ያለበትን እዳ እንዲከፍል ሲባል በሚደረገው ህጋዊ የድርሻ ጣልቃ ገብነት ለሽያጭ የሚቀርቡት የክለቡ ብርቅዬ ንብረቶች አንቶኒ ግሪዝማን፣ ኮኬና ውል ንጉዌዝ ጉዳይ አሳስቦታል።

ሳንቼዝ ስለጉዳዩ ሲናገርም “ማንም ከስታዲዮ ካልዴሮን ጋር ችግር የለበትም። የሚገኝበት ቦታም በጣም ምቹ ነው። ከፕላዛ ሜየር አደባባይ የ 20 ደቂቃ የእግር መንገድ ነው። ቦታው በጣም በሰዎች የተጨናነቁና የአካባቢውን ህዝብ በሚገባ ምግብ ቤቶች የተሞላ ደማቅ ስፍራ ነው። ምንም አይነት ችግር የለበትም። አላማው ግን ሌላ ነው። ከአዲሱ ስታዲየም ትልቅ ገንዘብ መሰብሰብ ከዛም የክለቡ አስተዳደር ቀዳዳውን በእሱ እየደፈነ ከዚህ ቀደም ያለበትን የተበላሸ እና ትኩረት ያጣ አስተዳደራዊ መንገዱን በተጠናከረ መልኩ ማስቀጠል ነው።” ብሏል።

የአትሌቲኮ ስታዲየም ቪሴንት ካልዴሮ

የካልዴሮን ስታዲየም ሽያጭ በክለቡ ይፋዊ ሂሳብ አካውንት ላይ የተገለፀ ሲሆን ከ 2003 ጀምሮ ጂሊ ማሪንና ሴሬዞ በክለቡ ድርሻ ላይ እጃቸውን ከከተቱ ወዲህ የታየ ነው። ይህ የስታዲየም ባለቤትነትም ዝውውርም በ 2014 በስፔን ሰበር ሰሚ ፍርድ ቤት “የተጭበረበረ” ተብሎ ውድቅ ተደርጓል። ነገር ግን ከፍርድ ቤቱ ውሳኔ በተቃራኒ አሁንም የክለቡ ቦርድ በስልጣን ላይ ቀጥሏል።

በዚህ ሁሉ መሀከልም አትሌቲኮ አገም ጠቀም በሆነ መልኩ ከከተማው ምክር ቤት ጋር እየሰራ ይገኛል። ካልዴሮን ስታዲየም በ 2012፣ 2016 እና በ 2020 ኦሎምፒኮች መስተንግዶ ፋክክር ታስቦ የከተማው አስተዳደር ለሶስት ጊዜያት እድሳት ቢያረግለትም ሶስቱም ግዜያት የኦሎምፒክ መስተንግዶ ጥያቄው ውድቅ ተደርጓል።


በአካባቢው የሚገኙ የተለያዩ የፓለቲካና የንግድ ሰዎችም ከስታዲየም ሽግግሩ ጋር በተያያዘ ከክለቡ ጋር በነበረው እንቅስቃሴ በሙስና ይታማሉ። ይህ ቅሌትም የከተማው ፕሬዝደንት ኢግናሲዮ ጎንዛሌዝንና የከተማውን ከንቲባ አልቤርቶ ሩይዝ ጋላርዶን ድረስ የሚዘልቅ ነው።

በሌላ በኩል ደሞ ስታዲየሙ ከአትሌቲክስ ውጪ ለእግር ኳስም የተመቸ እንዲሆን ያደረገውና በካልዴሮን ስፍራ የመኖሪያ አፓርታማዎች የገነባው የካታላኑ የግንባታ ቡድን የሆነው ኤፍሲሲ በስፔን የንብረት ነክ ኢኮኖሚ ቀውስ ኪሳራ ውስጥ ገብቶ ለመዘጋት በቅቷል።

በህዳር 2014 የአለም ሀብታሙ ሰው የሆኑትና በሀገራቸው እንዲሁም በስፔን እግር ኳስ ላይ እንቅስቃሴ የሚያደርጉት ካርሎስ ስሊም የስፓርት ተቋማት ግንባታ ተቀዳሚ መታወቂያው የሆነው የኤፍሲሲ ቡድን ባለ ትልቅ ድርሻ ሆኑ። በ 2015 የስሊም ኢምቡርስ ባንክ የ 160 ሚሊዮን ዩሮ ብድር በመፈቀዱና አትሌቲኮም በላ ፔይንታ የጀመረውን ግንባታ ሊቀጥል ስለነበር ድርጅቱ ራሱን ከካልዴሮንን ፕሮጀክት አገለለ።


ከጥቂት ወራት ወደዚህ አትሌቲኮና የክለቡ ወዳጅ የሆኑ የአካባቢው ሪፓርተሮች በአዲሱ ስታዲየም ግንባታ ለውጥ ዙሪያ በተከታታይ ዘገባ አቀረቡ። ከሁሉም በላይ ባሳለፍነው ታህሳስ የስታዲየሙ ስያሜ “ዋንዳ ሜትሮፓሊቲያን” ተብሎ ሲሰየም ዘገባው ከሁሉም ደማቅ ነበር። ይህ የስያሜ መብት ሽያጭ ገዢ ድርጅት የቻይና የመዝናኛ ተቋም ሲሆን በጥር 2015 የክለቡን 20 በመቶ ድርሻ በ 45 ሚሊዮን ዩሮ መግዛቱ ይታወሳል።


የዚህ የስም ቅያሬ ይፋ መሆን የተበሰረውም በኬሮግራፊ በደመቀ ስነስርአት በኮምፒውተር የተሰሩ በአዲሱ ስታዲየም በደስታ የክለቡ ጨዋታ የሚከታተሉ ደጋፊዎችን አጉልቶ በማሳየት ነበር። ነገር ግን ሳንቼዝ እንደሚናገረው ከኮምፒውተር ጨዋታው መሬት ላይ ወዳለው እውነታ ሲመጣ ነገሩ ሙሉ ለሙሉ የተገላቢጦሽ ነው።


“ኤፍሲሲ በ 40 ሜትር ክልል ውስጥ እና በስታዲየሙ ላይ ነው ግንባታ እያካሄደ ያለው። ከዛ ውጪ ሁሉ ነገር ግልጥ ያለ ባዶ ሜዳ ነው። በስርአቱ የታቀደ ስራ አልተሰራም። በመሰረት ልማት ላይ ምንም አይነት ስራ አልተጀመረም። ምንም አይነት የታቀደ ነገርም የለም። የሚቀጥለው የውድድር ዘመን ሊጀምር ስምንት ወራት ብቻ ቢቀሩትም አሁን ያለው እውነታ ይህ ነው።” ሲል ሳንቼዝ ምን ያህል የክለቡ መግለጫና በመሬት ላይ ያለው እውነታ እንደሚጣረስ አሳይቷል።

የአለም አቀፍ ኮሚቴ ተቆጣጣሪዎች ለኦሎምፒኩ አዘጋጅነት ብቁነቱን ለማረጋገጥ ወደ ላ ፒየንታ ስታዲየም መጥተው የነበረ ቢሆንም የማዘጋጀት ጥያቄው ዳግም ውድቅ ተደርጓል


በማድሪድ ከንቲባ ማኑዌላ ካርሜና እና በማዕከላዊ መንግስቱ መሀከል ያለው ፓለቲካዊ ቁርሾም ነገሩን ይበልጥ አወሳስቦታል። አትሌቲኮ ለፒዬኔታ የስታዲየም መገንቢያ ስፍራ በሚከፍለው ገንዘብ ዙሪያ አለመግባባት አለ። ይህ 45 ሚሊዮን ዮሮ የተገመተ ስፍራ እስካሁን የቀላልና የምድር ውስጥ ለውስጥ ባቡር እና አገናኝ መንገዶች ግንባታ አልተጀመረለትም።


በመስከረም ወር በነበረው ክርክር የተቃዋሚው የሶሻሊስት ፓርቲ ተወካይ የሆኑት የከተማው ምክር ቤት አባል ሜርሴዲስ ጎንዛሌዝ 70,000 ደጋፊዎችን ወደ አዲሱ ስታዲየሙ ለማጉዋጉዋዝ ‘ሄሊኮፍተር’ እንደሚያስፈልግ በመናገር ኮስታራ ቀልድ በመቀለድ የነገሩን አሳሳቢነት ገልፀዋል።


የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር (UEFA) ከሚቀጥለው አመት ጀምሮ ከምሸቱ አንድ ሰአት (በስፔን ሰአት አቆጣጠር) ጀምሮ ጨዋታ እንደሚኖር አሳውቋል። ስለዚህ ይሄ ማለት ሌሎች ከስራ ወጥተው ወደ ቤታቸው በሚሄዱበት ሰአት የአትሌቲኮ ደጋፊዎች ወደ ስታዲየም ያመራሉ እንደ ማለት ነው።


ባለስልጣናቱ የትራንስፓርት ችግር ትርምስ ማድሪድን እንደሚያዳክማት ያውቃሉ። ከችሎታ አንፃር ከተመለከትነው መሰረተ ልማቶቹን መገንባት አስቸጋሪ ነገር አይደለም። ነገር ግን በተለያዩ ፍላጎቶች የታጨቀ የፓለቲካ ግጭት በባለስልጣናቱ መሀከል አለ። ከዚህ ሌላም ለግንባታው በጣም ብዙ የህዝብ መዋጮ ስለሚያስፈልግ የገንዘብ ችግርም አለ።

የማድሪድ ከተማ ከንቲባ ማኑዌላ ክራሜና የቡድኑ አንደኛው እንቅፋት ናቸው።


ነገር ግን ክለቡ ሁሉ ነገር ወደ ጥሩ ሁኔታ ይቀየራል እያለ በአዲሱ ስታዲየም ይደረጋል ተብሎ ለሚጠበቀው የ 2017/18 የውድድር ዘመን ትኬቶችን የሸጠ ሲሆን በማህበራዊ ሚዲያም የስታዲየሙን ግንባታ ሂደት ለውጦች በየጊዜው ይፋ እያደረገ ነው። ሴሬዞ የስታዲየሙ የመብራት ዝርጋታ ይፋ በሆነበት ያለፈው ጥቅምት “አዲስ አገልግሎቶች፣ የመኪና ማቆሚያዎች፣ ምግብ ቤቶች፣ የምድር ውስጥ ባቡር፣ ሁሉም ነገር” በጊዜው እንደሚጠናቀቅ ለሪፓርተሮች ተናግረዋል።


ከዛሬ አስር አመት በፊት የስፔን የንብረት ገበያ አዋጭ በነበረበት ወቅት የከተማው እምብርት የሆነውን የካልዴሮንን ስፍራና ከዛ ቀደም ፈርሶ የነበረውን የቀድሞውን ማሁ ቢራ ፋብሪካ እንደ አዲስ መገንባት በጣም አዋጭ መስሎ ነበር። አሁን ባለው የገበያና የእቅድ ሁኔታዎች የአትሌቲኮ ባለስልጣናት እንኳን አፓርታማ ቤቶችን ለመገንባት ከስሊም ባንክ የተበደሩትን እዳ ለመክፈል ገንዘብ ማግኘት ተቸግረዋል።


“ከነዚህ እቅዶች ጀርባ ግላዊ የገንዘብ ፍላጎቶች አሉ። ነገር ግን እነማን እንደሆኑ አናውቅም። ነገር ግን አሁን ካለው ችግር መላቀቅ ካልቻሉ የክለቡ የሂሳብ አካውንት ትክክለኛውን የክለቡን የገንዘብ ሁኔታ ማሳየት አይችልም። ከዚህ በተጨማሪም ቦታውን መሸጥ ከቻሉም የክለቡን ሂሳብ በማስተካከል አቅም ያላቸውን ገዢዎች መሳብ ይችላሉ። ስለዚህ በማጭበርበር ያገኙትን ድርሻ ለዋንዳ፣ ስሊም ወይም ለሌሎች ገዢዎች በመሸጥ ከዚህ ችግር ክለቡን ሊያወጡት ይገባል።” ሲል ሳንቼዝ ያለውን ብቸኛ መፍትሄ በዝርዝር ተናግሯል።


በሌላ በኩል ግን የጊዜ መጣበቡን የተረዱት የአትሌቲኮ ክለብ ሀላፊዎች የ 2017/18 ውድድር የመክፍቻ ጨዋታዎቻቸውን በሌሎች ክለቦች ሜዳ ለማድረግ እንዲችሉ ለላሊጋው ባለስልጣናት ጥያቄ አቅርበዋል። ሳንቼዝም ክለቡ በቀጣዩ አመት በካልዴሮን መጫወት እንደማይችል መረዳቱን ጠርጥሯል። ምንም እንኳን ክለቡ በዚህ ዙሪያ አስተያየት ለመስጠት ባይፈልግም።

ሜክሲኳዊው ቱጃር ካርሎስ ስሊም

ከዚህ ውጪ ደግሞ የዲያጎ ሲሞኔው ቡድን በሜዳ ላይ መቸገሩም ሌላኛው የክለቡ ፈተና ነው። ሳንቼዝ ሲናገርም “ጂል ማሪንና ሴሬዞ አሰልጣኙን እንደ ጥላ የሚመለከቱት ሲሆን ከሱ ጀርባ በጣም ደስተኛ ናቸው። ነገር ግን በካልዴሮን ትርፍ ማግኘት ካልቻሉ ለባንኩ እዳቸውን መክፈል ስለሚገባቸው በእርግጠኝነት ተጫዋቾችን ይሸጣሉ።” ብሏል።


በዚህ ሁሉ መካከል ግን የእንግሊዙ ዩናይትድ አጥብቆ የሚፈልገውን ፈረንሳዊ ኮከብ አንቶኒ ግሪዝማንን በእጁ ለማስገባት ይበልጥ ይቀለዋል። የስፔኑ ክለብም ከዩናይትድ የሚቀበለው 100 ሚሊዮን ዩሮ እዳውን ከግማሽ በላይ በመሸፈን እዳውን ያቀልለታል።

በጣም ከባሰው ችግርም ቀላሉን ችግር በመምረጥ አትሌቲኮ ሊለቀው የማይፈልገውን ተጫዋች ወደ ኦልትራፎርድ ይሸኛል። ሙሉ ለሙሉ እዳውን ለመክፈል ደግሞ በክለቡ ያሳደጋቸውንና በደጋፊው እንደ ቤተሰብ የሚታዩትን ኮኬንና ሳውልን የመሳሰሉትን ተጫዋቾች በመጪው ክረምት ለሌሎች ክለቦች ለመልቀቅ ይገደዳል።

Advertisements

ሚኪያስ በቀለ View All

ይህን ዘገባ ያቀረብኩላችሁ የኢትዮአዲስ ስፓርት ኤዲተርና ፀሀፊ እኔ ሚኪያስ በቀለ ነኝ።

%d bloggers like this: