Skip to content
Advertisements

ተስፈኛ ታዳጊ : የዘር ሀረጉ ከኤርትራ የሚመዘዘው አዲሱ ዛላታን ኢብራሂሞቪች ማነው? 

የዘር ምንጩ ምስራቅ አፍሪካ የሆነው አዲሱ ተስፈኛ ታዳጊ
 

በሚኪያስ በ. ወርዶፋ | ሰኞ ጥር 15, 2009ለአንድ በአውሮፓ ለሚኖር ወጣት የ 17ኛ አመት ልደት በአሉን ማክበሪያ ብዙ አይነት መንገድ አለ። ከቤተሰቡ ወይም ከእጮኛው ጋር በእራት ግብዣ ወይም ደግሞ ከጓደኞቹ ጋር ዘና በማለት ሊያሳልፈው ይችላል።

ለአሌክሳንደር ይሳቅ ግን የልደት አከባበሩ ከዚህ የተለየ ነበር። ለክለቡ ኤአይኬ ሶላን አዋቂ ቡድን መሰለፍ ከጀመረ ስድስት ወራትን ብቻ ያስቆጠረው ታዳጊ በልደቱ ቀን በስዊድን ለሚገኝ አንድ የደርቢ ትንቅንቅ ክለቡን እየመራ ነበር።

ብዙዎች በ 17 አመታቸው ሊሞክሩት ከሚችለው በላይ አሌክሳንደር 33,000 ደጋፊ በያዘውና አብዛኛው ደግሞ ከእሱ በተቃራኒው የነበረው ዲጁርግራንድ ክለብ በሚደግፍበት ስታዲየም ያለምንም ፍርሀት በሚገባ ተጫውቶና ሁለት ጎሎችን አስቆጥሮ ከቡድን አጋሩ ቺኒዱ ኦባሲ “አዲሱ ዛላታን ኢብራሂሞቪች” የሚል ቅፅል ስምን ለመጀመሪያ ጊዜ አገኘ።

ከስዊድኑ ኮከብ ዝላታን ጋር እየተነፃፀረ የሚገኘው የስዊድን የወደፊት ተስፋ

በጨዋታው ላይ የጎል ሙከራ ለመፍጠር 100 ሰከንዶች ብቻ ያስፈለገው 1.90 የሚረዝመው አጥቂ በ 1891 በሶስት ሳምንታት ልዩነት ብቻ በተቋቋሙትና የምንግዜም ተቀናቃኞቹ ጨዋታ ቡድኑ 3-0 እንዲያሸንፍ ትልቅ እገዛ ማድረግ ቻለ። በዚህም የዛላታን ተተኪ እንደተገኘ በስዊድን ምድር በስፋት ተነገረ።

በስዊድኗ ሶላን ከኤርትራ ወላጆች የተገኘው አሌክሳንደር በአካባቢው በሚገኘው ክለብ በስድስት አመቱ በመቀላቀል የእግር ኳስ ህይወቱን ጀምሯል። ዛላታንን እንደ ጀግናው እያየ ያደገው ተጫዋች በስብዕና እንዲሁም በአስተዳደግ ከዩናይትዱ አጥቂ ጋር ባይመሳሰልም በአጨዋወቱ ግን ብዙ ነገራቸው ተመሳሳይ ይመስላል።

አሌክሳንደር ከስዊድናዊው ኮከብ በተጨማሪም የዘር ሀረጉ እንደሱ ከኤርትራ የሆነውን ተጫዋች ሄኖክ ጎይቶምን አርአያ አድርጎ ነው የተነሳው። ሄኖክ ለስዊድን ከ 21 አመት በታች መጫወት የቻለ ሲሆን በ 2012 ወደ ኤአይኬ ክለብ ከመመለሱ በፊትም የአውሮፓ ክለቦች በሆኑት ዩዲኒዜ፣ ሙርሲያ፣ ቫላዶሊድና አልሜርያ አይነት ክለቦች መጫወት ችሏል።

በስዊድኑ ክለብ ለአራት አመታት የነበረው ቆይታም በ 2015 ወደ ስፔኑ ጌታፌ በማምራቱ ሊያበቃ ችሏል። ይህም ከ 15 አመቱ ጀምሮ ከዋና ቡድኑ ጋር ልምምድ ሲሰራ ለነበረው ለአሌክሳንደር ወደ ዋናው ቡድን እንዲቀላቀል መንገድ ከፍቶለታል።

የሄኖክ ክለቡን መልቀቅም የሲኤስኬ ሞስኮውን ተጫዋች ካርሎስ ስትራንድበርግን ወደ ስዊድኑ ክለብ እንዲመጣ አደረገው። ካርሎስም የሄኖክን ቀዳዳ እንዲደፍን ታስቦ የመጣ ሲሆን አሌክሳንደር ግን እድገቱን ጠብቆ እንዲያድግ በክለቡ በጣም ይፈለግ ነበር። ነገር ግን ያሳየው አስደናቂ ብቃት የወቅቱን አሰልጣኝ አንድሬስ አልምን ተጫዋቹን ወደ ቡድናቸው አሰላለፍ እንዲቀላቅሉ አስገደዳቸው። አልምስ ተሰናብተው ሪካርድ ኖርሊንግ ሲቀጠሩም ታዳጊው ተስፈኛ በብቃቱ አሳምኖ መቀጠል ቻለ።

በስዊድኑ አልስቬንስካን ክለብም በ 24 ጨዋታዎች ላይ 10 ጎሎችን ማስቆጠር ቻለ። ብዙዎችን በእንቅስቃሴውና በአካላዊው ጥንካሬ ብቻ ሳይሆን በብሩህ አይምሮውና ከእድሜው በላይ ባለው ብልሀት ማስደመም ቻለ። በባህሪው የኢብራሂሞቪችን ቁጡነት ባይዝም የአጨዋወት ሁኔታው የዝነኛውን ስዊድናዊ የወጣትነት ጊዜ በሚገባ ቁልጭ አድርጎ ያስታወሰ ሆነ።

ኤአይኬ ክለብም በስዊድን ሊግ ከታላቁና ለ 22 ጊዜ የሊጉን ዋንጫ ካነሳው ማልሞ ቀጥሎ በሁለተኛነት መጨረስ ቻለ። ይህም ምስጋና ለአዲሱ ታዳጊ ይሁንና ትልቅ ስኬት ሆናቸው በሌላ በኩልም ተጫዋቹ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ክለቡን ለቆ ወደ ሌሎች የአውሮፓ ሀያላን ክለቦች እንደሚያመራ ምልክት የሰጠ ሆነ። ከአውሮፓ ታላላቆች ለተጫዋቹ ዝውውር ተብሎ የክለቡን አመታዊ ባጀት ያህል ሲቀርብ ክለቡ ጥያቄውን ውድቅ ለማድረግ ተቸገረ።

አሌክሳንደር እስካሁን ድረስ ለእኛ ብቻ ተጫውቶልናል። ይህም በጣም ያኮራናል።” ሲሉ የክለቡ ስፓርት ዳይሬክተር ቢጆርን ዌስትሮም የተጫዋቹን መሸጥ ይፋ አደረጉ። ነገር ግን ክለቡ ገና ተጫዋቹ 17ኛ አመቱን ባከበረበት ወቅት በስዊድን የመቆየቱ ነገር እንዳበቃለት ተረድቶ ነበር። በወቅቱ ጥያቄ የነበረው “ይለቅ ይሆን?” የሚለው ሳይሆን “ወዴት ያመራ ይሆን?” የሚለው ነበር።

ከተለያየ ቦታም ማሳሰቢያዎች መደመጥ ጀመሩ። “ጥሩውንና ትክክለኛውን ምርጫ ምረጥ።” የሚሉ ምክሮች ለታዳጊው ተሰነዘሩ። ኤአይኬ ክለብም ኢብራሂሞቪች ከማልሞ ወደ አያክስ ሲያመራ ካስወጣው 7 ሚሊዮን ፓውንድ በላይ ላገኘበት ተጫዋች ገንዘቡን ብቻ አይደለም ዝም ብሎ የተቀበለው። ተጫዋቹ ወደ ፈረንሳዩ ፒኤስጂ እንዲያመራ ፈልጎ ነበር።

ነገር ግን ተጫዋቹን ለመውሰድ የቀረበው ሪያል ማድሪድ በመሆኑ ከክለቡ ተወካዮች ጋር ድርድር ተደርጎ ከመስማማት ተደረሰ። ሁሉ ነገር ተጠናቆም ለተጫዋቹም የአምስት አመት ስምምነት ከስፔኑ ክለብ ቀርቦለት ፊርማውን ማኖር ብቻ ቀረ።

ነገር ግን ተጫዋቹ “ቀጣዩ ጉዞ ወዴት ነው?” ሲል መልሶ አሰበና የዋና ቡድን እግር ኳስን ለምዶ የደጋፊን ፍቅር አይቶ ወደ ማድሪድ በመሄድ የ ‘ቢ’ ቡድን ተጫዋች መሆንን ጠላ። ከዚህ በተጨማሪም ከዚህ ቀደም ወደ ማድሪድ አምርቶ አንድ ጨዋታ ብቻ አድርጎ ከወር በፊት ወደ ሆላንድ በውሰት ያመራው ኖርዌያዊ ማርቲን ኦድጋር ትውስ ሲለው ሀሳቡን ሙሉ ለሙሉ ቀየረ።

የ 17 አመቱ ታዳጊ በስዊድን የሰራውን ገድል በጀርመን ሊደግም የቦርሲያ ዶርትሙንድን ማሊያ ለማጥለቅ ፊርማውን አኑሯል።

ከአስር አመት በፊት ከኪሳራ አገግሞ ታላቅ መሆን ለቻለውና እነ ኑሪ ሳሂን፣ ማት ሀምልስ፣ ኢልካይ ጉንዶጋን፣ ማሪዮ ጎሜዝ፣ ሮበርት ሎንዶልስኪ እና ሌሎች ብዙ ኮከቦች ለተጫወቱለት ቦርሲያ ዶርትሙንድ ልቡ ከጀለ። በጀርመኑ ክለብ አዲስ ታሪክ ለመስራት በማሰብም በ 8.65 ሚሊዮን ፓውንድ (10 ሚሊየን ዩሮ) የዝውውር ሂሳብ ፊርማውን አኖረ።

“አሌክሳንደር ይሳቅ ባለ ትልቅ ተሰጥኦ የሆነ በብዙ የአውሮፓ ክለቦች የተፈለገ ተጫዋች ነው። ክለባችን ቦርሲያ ዶርትሙንድን ለመቀላቀል በመወሰኑም ተደስተናል።” ሲሉ የክለቡ ስፓርቲንግ ዳይሬክተር ማካኤል ዞርክ ተናግረዋል።

አሌክሳንደር እነ ኦስማን ዴምቤሌ፣ ክርስቲያን ፑልሲች፣ ኤምሪ ሞር፣ ፌሊክስ ፓስላክና ጁሊያን ዊግል ያሉ ተጫዋቾችን በታዳጊነታቸው አምጥቶ የዋና ቡድን እድል በመስጠት የእግር ኳስ ህይወታቸውን ባሳደገው ክለብ መገኘት ቻለ።

በዶርትሙንድ ግልፅ መንገድ አለ። ቱሼል ወጣቶችን በማመን በኩል በኩል ምንም ችግር እንደሌለበት ማሳየት ችሏል። የአድሪያን ራሞስ መልቀቅ አሌክሳንደርን ለማስፈረም ምክንያት ሆኗል።

በጋቦን ሀገሩን ወክሎ እየጫወተ ያለው ኤምሪክ ኦቦምያንግ ከዚህ የውድድር ዘመን በኃላ የክለቡ ቀጣይ ቆይታ አለመታወቁ አሌክሳንደር የጋቦናዊው ተቀያሪ በመሆን እንዴት ብቃቱን ማሳየት እንደሚችል ይበልጥ እየተማረ እንዲቆይ ያስችለዋል። ከዛም በቅርቡ በዶርትሙንድ ቤት ዋናው ፊት አውራሪ ሆኖ ሊመጣ ይችላል። እኛም ምስራቅ አፍሪካን ለሚያስጠራው ኮከብ ከወዲሁ ይቅናህ ብለናል።

Advertisements

ሚኪያስ በቀለ View All

ይህን ዘገባ ያቀረብኩላችሁ የኢትዮአዲስ ስፓርት ኤዲተርና ፀሀፊ እኔ ሚኪያስ በቀለ ነኝ።

%d bloggers like this: