Skip to content
Advertisements

ድህረ ጨዋታ ዘገባ : ቼልሲ 3-1 አርሰናልበሚኪያስ በ. ወርዶፋ | ቅዳሜ ጥር 27, 2009

ቼልሲ መሪነቱን ለማጠናከር አርሰናል ደግሞ በዋንጫ የባቡር ጉዞ ላይ አሁንም መቀጠል እንደሚችል ለማሳየት ወሳኝ በሆነው የዛሬ ከሰአት ጨዋታ በስታምፎርድ ብሪጅ ተደርጎ ቼልሲ 3-0 በማሸነፍ የሊጉን መሪነት በ 12 ነጥቦች ማስፋት ችሏል።

በጨዋታው ላይ የኮንቴው ስብስብ ባሳለፍነው መስከረም በአርሰናል 3-0 በተሸነፈበት እለት የጨዋታው አጋማሽ ላይ መጠቀም የጀመረበትንና የተከታታይ 13 ጨዋታ ጉዞ ድልን ያስመዘገበበትን በሶስት ተከላካይ የመጠቀም አሰላለፍን ዛሬም ወደ ሜዳው ይዞ ገብቷል። 

በሌላ በኩል አርሰናል ከዚህ ቀደም ከሚከተለው አጨዋወት በተለየ በ 4-1-2-3 አሰላለፍ ዩዎቢን አማካኝ ላይ በማጫወት ኦዚልን ወደ ግራ አውጥቶ በማሰለፍ ወደ ሜዳ ገብቷል። በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎችም ዩዎቢ ለጎል የቀረበ ሙከራን ማድረግ ችሏል።

በጨዋታው የመጀመሪያ 12 ደቂቃዎችም መድፈኞቹ ኳስን በሚገባ ይዞ በመጫወት የጎል ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል። ነገርግን በ 12ኛው ደቂቃ ላይ ሞሰስ ለፔድሮ ያቀበለውን ኳስ ስፔናዊው በቀኝ ክንፍ ይዞ በመሄድ ያሻማውን ኳስ ዲያጎ ኮስታ ሞክሮት ቼክ በግሩም ሁኔታ መልሶበታል። 

ቢሆንም ግን ከቼክ የተመለሰውን ኳስ በጎሉ አቅራቢያ የነበረው ማርኮስ አሎንሶ መልሶ በጭንቅላት በመምታት የመድፈኞቹ መረብ ላይ ለማገናኘት ችሏል። 

የቤለሪን የጉዳት ሁኔታ ይህን ይመስላል።

ጎሉ በሚቆጠርበት ወቅት ግን ኳስ ለማግኘት በተፈጠረው ትንቅንቅ አሎንሶ የአርሰናልን መሀል ተከላካይ የሆነውን ቤለሪንን አገጩን በከባድ ሁኔታ በክርኑ ስለመታው ከጨዋታ ውጪ አድርጎታል። በእሱ ምትክም ጋብሪየል ፓሊስታ ተቀይሮ ወደ ሜዳ ለመግባት ተገዷል።   

ከዛም በጨዋታው 19ኛ ደቂቃ ሰማያዊዎቹ ቼልሲዎች በዲያጎ ኮስታ አማካኝነት የጨዋታውን መሪነት ወደ ሁለት የማሳደግ እድል ሳይጠቀሙበት ለትንሽ መክኖባቸዋል።  

በጨዋታው ላይ አርሰናል በጥሩ ሁኔታ መጀመር ቢችልም የባለ ሜዳዎቹ የዘንድሮ ስኬታማ የመልሶ ማጥቃት አጨዋወትን እንደ ከዚህ ቀደሞቹ የቼልሲ ተፋላሚ የሊጉ ቡድኖች መቋቋም ሳይችል ቀርቷል። 

ነገርግን በመጀመሪያው አጋማሽ የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች መድፈኞቹ ወደፊት መጓዝ ችለው አስደንጋጭ የጎል እድሎችን መፍጠር የቻሉ ሲሆን አቻ ለመሆንም ጥረት ቢያደርጉም ጨዋታው በ 1-0 የቼልሲ መሪነት ወደ እረፍት አምርቷል። 

ከእረፍት መልስ መድፈኞቹ ጨዋታውን የጀመሩበትን ያልተለመደ አሰላፍ ከዚህ ቀደም ወደሚታወቁበት የ 4-2-3-1 አሰላለፍ በመቀየር ኦዚልን ከሳንቼዝ ኃላ በማድረግና ዩዎቢን ወደ ግራ መስመር በማውጣት ጨዋታቸውን ጀምረዋል። 

ነገርግን የቼልሲን የውድድር ዘመን በእጅጉ እያሳመረ ያለው ቤልጄማዊው ሀዛርድ የቡድኑን መሪነት ማስፋት የቻለውን ሁለተኛ ግብ በ 52ኛ ደቂቃ አስቆጥሮ ከክለቡ ሩሲያዊ ባለሀብት ጀምሮ በስታዲየሙ የሚገኙ የቼልሲ ደጋፊዎችን ማስደሰት ችሎ ጨዋታው በባለ ሜዳው ቡድን 2-0 መሪነት ቀጠለ። 

ከጎሉ በኃላም አብዛኛዎቹ የአርሰናል ተጫዋቾች ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ገብተው የታዩ ሲሆን ሳንቼዝም የሚጠበቅበትን ብቃት ማሳየት ተስኖት ቆሞ ታይቷል። መድፈኞቹ የአማካኝ ክፍላቸውን እየቀያየሩ ለውጥ ለማምጣት ቢሞክሩም በጨዋታው ላይ ትርጉም ያለው ለመፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። 

የጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎችም ለአርሰናል መጥፎ ውጤትን ይዘው የመጡ ሲሆን ተቀይሮ የገባው የቀድሞው የአርሰናል ስፔናዊ አማካኝ ፋብሪጋዝ ገና እንደገባ በቼክ ስህተት ያገኛትን ስህተት ተጠቅሞ ሶስተኛውን ግብ ለቡድኑ ማስቆጠር ቻለ። 

በ 90ኛው ደቂቃም የመድፈኞቹ ፈረንሳዊ አጥቂ ከሞኒሪያል የተሻገረችውን ኳስ ተጠቅሞ የአርሰናልን ማስተዛዘኛ ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው በ 3-1 ውጤት ተጠናቋል። 

አሁን ቀጣዩ አነጋጋሪ ነገር የ 67 አመቱ አዛውንት አርሰን ቬንገር የኢምሬትስ ቀጣይ ቆይታ ዙሪያ  መሆኑ እርግጥ ሆኗል።

Advertisements
%d bloggers like this: