Skip to content
Advertisements

አሳሳቢ : በሌስተር ቤት የገባው በሽታ አድማሱን ማስፋቱን ቀጥሏል። 

​​


በሚኪያስ በ. ወርዶፋ | እሁድ ጥር 28, 2009

ሲቲን ገንዘብ ከጎረፈለትና በአረብ ባለሀብቶች ከመያዙ በፊት ስለነበረው አቋም ለምናቀው ለእኛ አዲሶቹና ሲቲን በስኬት ብቻ የሚያውቁት አዲሶቹ የእግር ኳስ ተከታታይ ትውልዶች “ሲቲቲስ” ስለተሰኘውና በጆ ሮይልስ የአሰልጣኝነት ዘመን ሲቲ ቤት በአንድ አመት ልዩነት ውስጥ በተከሰተ አስደንጋጭ የውጤት መቀያየር ምክንያት ስለተፈጠረው የእግር ኳስ በሽታ ስለማያውቁ ልንደናገጥ እንችል ይሆናል።

ኮሊን ሺንድለር “ሲቲ ራይንድ ማይላይፍ” ብሎ በሰየመው መፅሀፉ ጆ ሮይል የቃሉን ትርጓሜ እንዳልተረዱ “እሱ ሲቲቲስ በመድሀኒት የሚድን ክለብን በፕሮፌሽናል መንገድ መምራት ያለመቻል የባክቴሪያ በሽታ አድርጎ ነው የተረዳው። ነገርግን ሲቲቲስ ስንወለድ ይዘነው የምንፈጠረው የቪታሚን እጥረት ነው። የበሽታ መከላከል አቅማችንን ለመገንባት ተጨማሪ ነገሮችን መውሰድ እንችላለን ነገርግን ታኪን ሺንዋትራ ወይም ደግሞ ጄሚ ፓሎክን ከቦልተን የማስፈረም አይነት በሽታዎችን በሚገባ መፋለም አንችልም።” ሲል ነበር የበሽታውን አደገኛነት የገለፀው።

ሲቲ በ 1936/37 የሊጉን ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ማግኘት ቻለ። የወቅቱን የሲቲን ድል ይበልጥ ጣፋጭ ያደረገው ደግሞ የምንግዜውም ተቀናቃኛቸው ዩናይትድ ከ 42 ጨዋታዎች በኃላ መጨረሻ ከጨረሰው ቡድን በአንድ ደረጃ ከፍ ብሎ ከመጨረሻ ሁለተኛ ሆኖ በዛው አመት ወደታችኛው ዲቪዚዮን መውረዱ ነበር።

ነገርግን ቀጣዩ የውድድር አመት ለሲቲ ከባድ ፈተናን ይዞ መጣ። የኢትሀዱ ክለብ ከ 42 የሊግ ጨዋታዎች 20 የሚሆኑትን ተሸንፎ 21ኛ ሆኖ በመጨረስ ዋንጫ በበላ በቀጣዩ አመት ወደታችኛው ዲቪዚዮን ለመውረድ ተገደደ። በአስደናቂ ሁኔታ የሊጉን ብዙ ጎል ያስቆጠረው ቡድን መውረዱ ብዙዎችን አስደነቀ።

የዛሬ 79 አመት ለብቸኛ ጊዜ በእንግሊዝ እግር ኳስ የተከሰተው ዋንጫ በልቶ በቀጣይ አመት የመውረድ አደጋ አሁን አምና አስገራሚና የምንግዜውንም አስደናቂ ስኬት ባሳየው በሌስተር ቤት ተከስቶ ቀበሮዎቹ የሲቲቲስ በሽታ ምልክቶች በግልፅ እየታየባቸው ነው።

ከሁለት አመታት በፊት በወራጅ ቀጠና ውስጥ ለስድስት ወራት ቆይቶ በመጨረሻ ከመውረድ የተረፈው ቡድን ማንም ባልገመተው መልኩ በቀጣዩ አመት በ 10 ነጥብ ልዩነት የሊጉ አሸናፊ መሆን ችሏል። የሪያኔሪው ስብስብ ዘንድሮ የዛሬውን የዩናይትድ የ 3-0 ሽንፈት ጨምሮ ካለፋት 15 ጨዋታዎች ሁለቱን ብቻ ማሸነፍ ችሎ ከወራጅ ቀጠናው በአንድ ነጥብ ብቻ ርቆ ተቀምጧል። በቀጣይነት የሚጠብቁት ከባባድ ጨዋታዎች ደግሞ ይበልጥ ወደ ወራጅ ቀጠናው ደፍቆ እንዳይከተው ተሰግቷል።

ሌስተሮች ባሳለፍነው የውድድር ዘመን ያስመዘገቡት ስኬት ጠልፎ ጥሏቸዋል። የአምናውን አይነት ደስታ ዳግም እንደማያገኙ ለተረዱት ሌስተሮች ያሳለፍነው የውድድር ዘመን ድል አብዛኛው ኮከቦች የነበራቸው አስደናቂ ብቃት በእጅጉ እንዲወርድና ለውጤት ያላቸው ተነሳሽነት እንዲሞት ምክንያት ሆኗል። የአሰልጣኞች ቀንደኛ ጠላት የሆነው በቀደመ ውጤት የመርካት አባዜ በሌስተር ቤት ስሩን ሰዷል። በተጫዋቾች ዘንድ ተነሳሽነት ጠፍቷል።

የሌስተርን ያህል የከፋ ባይሆንም በዩናይትድ ቤትም የ 1999 የቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ካነሳ በኃላ ተመሳሳይ በሽታ ተከስቶ ነበር። “ከድሉ ወራት በኃላም የሶስትዮሽ ድሉ ጣጣ በየሄድንበት ይከተለን ነበር። ወደ ቀጣዩ አመት ውድድር ልንገባ ስንል ጀግኖች፣ ታሪክ ሰሪዎች፣ ከ 1968ቱ ቡድን የበለጣችሁ ተብለን ተወደስን በሶስቱ ዋንጫዎች ፎቶዎች ላይ ፊርማችንን አኖርን። ስለእዛ አስደናቂ ምሽት ሁሌም መነጋገርን ማቆም አቃተን።” ሲል ሮይ ኪን በአንድ ወቅት የስኬታቸውን ጣጣ አስታውሶ ተናግሯል።

በወቅቱ የፈርጉሰን ቡድን ከሶስትዮሽ ድሉ በኃላ በነበረው ቀጣይ አመት የሊጉን ዋንጫ ማንሳት ቢችልም በአውሮፓ መድረክ ዳግም ስኬት ለማስመዝገብ ተፈትኗል። በቻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ ዳግም ለመቅረብም ዘጠኝ አመታትን መጠበቅ ግድ ብሎታል። ከድሉ አመታት በኃላ የወቅቱ የቡድኑ አምበል ኪን ከኒውካምፑ ምሽት ድል በኃላ የተወሰኑ ተጫዋቾች ሌላ ዋንጫ ባያገኙ ምንም እንደማይመስላቸው የሰጡን አስተያየት አስታውሶ ተናግሯል። በወቅቱ በስኬቱ ከመጠን በላይ የረኩት ተጫዋቾች ድሉ በቀጣይ አመታት በአውሮፓ መድረክ ትልቅ ስኬት እንዳያስመዘግቡ ትልቅ የስንፈት በሽታ ሆኖባቸዋል።

በ 1998-99 የውድድር ዘመን ድዋይት ዮርክ በ 52 ጨዋታዎች 29 ጎሎችን በማስቆጠር የአጥቂ መስመሩን በሚባ መምራት ችሎ ነበር። ከእዛ በኃላ ግን ከእግር ኳስ ይልቅ ከሜዳ ውጪ ላሉ አልባሌ ነገሮች የሚንበረከክና እንደ ሌሎች አንዳንድ ተጫዋቾች ስኬቱ እንቅፋት ሆኖበት ታይቷል። የብላክበርን ተጫዋቾች የሊጉን ዋንጫ ካነሱ በኃላ ያሳዩት ባህሪ ወይም ደግሞ ሳሚር ናስሪ በሲቲ ቤት የመጀመሪያ የሊግ ዋንጫውን ካገኘ በኃላ የሄደበት መንገድ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል።

ጂሚ ቫርዲና ሪያድ ማህሬዝ ያለፈው አመት የኮከብ ተጫዋችነት ክብራቸውን ረስተው አሁን ያሉበት ደካማ እንቅስቃሴ ለዚህ ትልቅ ምሳሌ ነው። ይሄ ሲባል ግን የንጎሉ ካንቴ መውጣት ቡድኑን አልጎዳም ብሎ ለመከራከር አይደለም። ካንቴ በሳምንቱ አጋማሽ ከሊቨርፑል ጋር በነበረው ጨዋታ 14 ሸርተቴዎችን ሲወርድ የሌስተር ተጫዋቾች ከበርንሌይ ጋር የወረዱት አጠቃላይ ሸርተቴ ስምንት ብቻ ነው። ካንቴ ሶስት ተጫዋቾችን አልፎ አክርሮ የጎሉ አናት ላይ ኳስ በመምታት ጎል የሚያስቆጥር ወይም በተረከዙ በቄንጥ ኳስ የሚያቀብል አይነት ተጫዋች አይደለም። ነገርግን ባለፋት ሶስት አመታት በሊጉ ላይ አስደናቂ ኳስ ነጣቂና የሚበልጥ ተጫዋች መሆን የቻለ ነው። በአጠቃላይ በአንድ ተጫዋች መውጣት ላይ የሌስተርን ውድቀት ማመካኘት ሰበብ ይመስላል።

ለሪያኔሪ በመልበሻ ቤት መከፋፈል መኖሩን የሚገልፁ ሪፓርቶች መውጣታቸው መንፈስ ገዳይ ነው። ተቃራኒዎቻቸው ሌስተር የራስ ወዳድነትና የመጥፎ አስተሳሰብ ምልክት ያለበት ቦታ እንደሆነ መስማት ጀምረዋል። በደጉ ጊዜ ተጫዋቾቻቸውን እንደ አባት “ልጆች” እያሉ ይጠሩ የነበሩት ሰው ሪያኔሪን ዝቅ የሚያደርጉ መረጃዎች ከሌስተር ቤት መውጣት ጀምሯል።

እንደዚህ አይነት የመረጃ ማፈትለኮች ሙሉ ቁጥጥርና የተጫዋች አንድነት ባለባቸው ክለቦች የሚፈጠር አይደለም። የሊኦናርዶ ኡልአ የአደባባይ ውዝግብና እንዲሁም ተጫዋች አዲስ ኮንትራት ተፈራረመ ማለት ለክለቡ የመጫወት ፍላጎት አለው ማለት እንዳልሆነ ያሳየን የማህሬዝ ጉዳይ ከቀበሮዎቹ በስተጀርባ ጤና እንዳሌለ በሚገባ ይጠቁመናል።

የዛሬ አመት በዚህን ሰአት ሌስተር በወሳኝ ጨዋታ ወደ ኢትሀድ ተጉዞ  3-1 በማሸነፍ ጉዞውን ያሳመረበት ነበር። ዘንድሮ በተቃራኒው በዩናይትድ በትልቅ የጨዋታ ብልጫ ሜዳው ላይ 3-0 ተረቶ የወራጅ ቀጠናውን ለመቀላቀል አፋፉ ላይ ይገኛል። ስለዚህም ሪያኔሪም በክለባቸው የገባው በሽታ በቀላሉ የማይድንና ስር ነቀል ለውጥ እንደሚያስፈልገው ተረድተው ርምጃ መውሰድ መጀመር ይገባቸዋል።

 

Advertisements
%d bloggers like this: