በካታሎናውያን ውሳኔ የባርሴሎና ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል?


ካታሎናውያኑ እጅግ ውዝግብ ባልተለየው እና በስፔን መንግስት ከፍተኛ ተቃውሞ በደረሰበት የራስን ዕድል በራስ የመወሰን የድምፅ አሰጣጥ ተካሄዷል። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከሆነም 90 በመቶ ካታሎናውያን የ”ነፃነት” ድጋፍ ድምፃቸውን ሰጥተዋል። ለመሆኑ ባርሴሎናን ጨምሮ ስፓኛልና ጂሮና ክለቦች የወደፊት የዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል? ኢትዮአዲስ ስፖርትም ይህንና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በሚከተለው ፅሁፍ ሰፋ አድርጋ ተመልክታቸዋለች። 

ካታሎኒያ ምንድን ነው?

ካታሎኒያ በስሜን ምስራቅ ስፔን የምትገኝ የስፔን አምስት በመቶ የሚጠጋ ኢኮኖሚ የሚመነጭባት ባልትልቅ ኃይል ግዛት ናት። 7.5 ሚሊዮን ህዝቦች ያሏትና የራሷ የሆነ ቋንቋና ባህል ያላት በስፔን ለአራት መቶ ዓመታት የዘለቀው የጀነራል ፍራንኮ አምባገነናዊ መንግስት አገዛዝ ኃይል ስር ወድቃ የቆየች ግዛት ናት። 

የግዛቲቱ መንግስት በአሁኑ ጊዜ የራሱ የሆነ ፖሊስ እና አብዛኛውን የጤናና የትምህርት ጉዳዮቹን በአንፃራዊ ነፃነት በራሱ ማስተዳደር ቢችልም፣ አሁንም ድረስ ግን ግብር፣ የውጭ ጉዳይ፣ የመከላከያ፣ የወደብ፣ አውሮፕላን ማረፊያና የባቡር ትራንስፖርትን የሚያስተዳድረው ዋና መቀመጫውን በማድሪድ ያደረገው የስፔን መንግስት ነው።

ካታሎናውያን የግዛት ነፃነት እውቅናን ለማግኘት ለበርካታ ምዕተ ዓመታት ጥያቄ ሲያነሱ የቆዩ ቢሆንም፣ ጠንከር ያለ የነፃነት ጥያቄን ማንሳት የጀመሩት ግን በ2010 ቢሆንም የስፔን የህገመንግስታዊ ጉዳዮች ፍርድ ቤት የስፔን ግዛት እንደሆነች ትልቅ የራስ ገዝ እውቅናን የሚሰጥ ውሳኔ አስተላልፏል።

ውሳኔው ከተላለፈበት ጊዜ አንስቶም በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ካታሎናውያን መስከረም 11 በየዓመቱ በሚከበረው ካታሎናውያን በዓል ወቅት የነፃነት ጥያቄያቸውን በአደባባይ ሲያስተጋቡ ቆይተዋል።

እሁድ ዕለት በካታላን የሆነው ምንድን ነው?

አብዛኞቹ የግዛቲቱ በፃነት አጥብቆ ፈላጊዎች በገቡት ቃል መሰረት በስፔን መንግስት ድጋፍ ሳያገኝ የአንድ ወገን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን የህዝባዊ ውሳኔ ድምፅ አሰጣጥ ሂደት አከናውነዋል። ይህን በማድረጋቸው ደግሞ የስፔን መንግስት የህገመንግስታዊ ጉዳዮች ፍርድ ቤቱን ውሳኔ ጥሰዋል በሚል የኃይል እርምጃ እስከመውሰድ ደርሶ 800 ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል።

የድምፅ አሰጣጡ ውጤት ምን ይመስል ነበር?

የስፔን የህገመንግስታዊ ጉዳዮች ፍርድ ቤቱ ባለፈው ወር የመገንጠል ምርጫው እንዳይሄድ ውሳኔ ቢያስተላልፍም በዚህ ሁሉ ውጥረት በተካሄደው የድምፅ አሰጣጥ የካታሎን አገዛዝ አመራሮች እንደገለፁት ከሆነ መምረጥ ከሚችሉ ካታሎናውያን መራጮ 90 በመቶ የሚሆኑት የግዛቲቱን ነፃነት ደግፈው ድምፅ ሰጥተዋል።

የስፔን ህገመንግስት መገንጠልን አስመልክቶ ምን ይላል?

የስፔን ህገመንግስት የስፔን ጋዛቶች የራስ ገዝ መንግስት መመስረት ስለመቻላቸው “እውቅና” እና “ማረጋገጫ” እንደሚሰጥ የሚገልፅ አንቀፅ አስፍሯል። 

ቀጥሎ ምን ይፈጠራል?

የካታላን ግዛት አመራር በነጠላ የተካሄደው ከስፔን ነፃ የመውጣት የህዝብ ውሳኔ የድጋፍ ድምፁ በ48 ሰዓታት ውስጥ ይፋ እንደሚሆን ገልፅዋል። የነፃነት ውሳኔውም በዚህ ሳምንት ሙሉ በሙሉ ይፋ እንደሚሆን ይጠበቃል።

የስፔን መንግስትስ ምን ሊያደረግ ይችላል?

የማድሪዱ መንግስት የመገንጠል ጥያቄውን ውድቅ እንዳደረገው ሁሉ ለድምፅ አሰጣጥ ውጤቱንም ህገወጥ በማለት እውቅና አልሰጠውም። ስለዚህ ለግዛቲቱ ነፃነት ይፋ መሆንም እውቅና እንደማይሰጥ እርግጥ ነው። ይህንን ለማረጋገጥም የስፔኑ ጠቅላይ ሚኒስቴር ከዚህ ቀደም ጥቅም ላይ ውሎ የማያውቀውንና የስፔንን ህገመንግስትን እና ህግን ተግባራዊ የማያደርግ በተናጥል የሚንቀሳቀስን ግዛት ለስፔን የጋራ ጥቅም ሲባል ጠቅሎ እንደሚይዝ የሚያስችለውን የስፔን ህገመንግስት አንቀፅ 155 እንደአማራጭ ይጠቀማሉ ተብሎም ይጠበቃል።

የግዛቲቱ መገንጠል እውን ከሆነ የባርሴሎና የወደፊት ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል?

ካታሎናውያኑ ከስፔን አገዛዝ ስርዓት ነፃ የሚሆኑ ከሆነ የኑ ካምፑ ኃያል ክለብ ከስፓኞል እና ጂሮና ጋር ከላ ሊጋው ውድድር ውጪ መሆን የሚችሉባቸው አማራጮች አሏቸው።

እንደካታሎን ግዛት የስፖርት ሚኒስቴር ገለፃ ከሆነ ካታሎናውያኑ ከስፔን አገዛዝ ስርዓት ነፃነት ወጥተው ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር የሚችሉበት ሁኔታ አለ። ይኸውም ባርሴሎና የእንግሊዙን ፕሪሚየር ሊግ፣ የፈረንሳዩን ሊግ 1 ወይም የጣሊያኑን ሴሪ ኣ ሊጠቃለል ይችላል።

ትውልደ ካታሎናውያኑም ከወዲሁ የግዛቲቱን የወደፊት ዕጣ ፈንታዎች አስመልክተው የራሳቸውን የወደፊት ዕቅዶች እያቀረቡ ይገኛሉ። እያቀረቧቸው ከሚገኙት ዕቅዶች መካከልም በነፃ አገዛዝ በምትመሰረተው አዲሲቱ ሃገር የሚገኙ ክለቦችን የሚመለከቱ የትግበራ ዕቅዶች ይጠቀሳሉ።

ባርሴሎና፣ ስፓኞል እና ጂሮና የግዛቷን ነፃናት ተከትሎ የወደፊት ዕጣ ፈንታቸው ምን እንደሚሆን የተረጋገጠ ነገር የለም። ነገር ግን እንደሚኒስቴሩ ጄራርድ ፊጉራስ እምነት ከሆነ ወደፊት በርካታ አመርቂ አማራጮች ይኖራሉ።

እንደሚኒስቴሩ ንግግሩ ከሆነም “ነፃነቱ በተመለከተ በላ ሊጋው ውስጥ የሚገኙ የካታላን ቡድኖች በስፔን ሊግ ወይም እንደጣሊያን ፈረንሳይ ያሉ ጎረቤት ሃገሮች ወይም በፕሪሚየር ሊጉ መጫወት የሚፈልጉ ስለመሆን አለመሆናቸው ራሳቸው ይወስናሉ። 

“አሁን በስፔን ከሌላ ሃገር የሆኑ፣ እንደኦንዱራ በእግርኳስና በቅርጫት ኳስ ብሄራዊ ሊጎች ውስጥ የሚጫወቱ ቡድኖች አሉ። ሞናኮ በፈረንሳይ ይጫወታል። በእንግሊዝ የዌልስ ክለቦች ይጫወታሉ። የአውሮፓ ህብረት እግርኳስ ማህበርም ቡድኖች ከሃገራቸው ውጪ በሌላ ሃገራት የተለያዩ ሊጎች ውስጥ መጫወታቸውን የሚፃረር ነገር አለው ብዬ አላስብም።” ብለዋል ሚኒስቴሩ።

በሚኒስቴሩ ሃሳብ መሰረት ከሆነም ባርሳ በላ ሊጋው ውድድር ላይ እየተጫወተ ሊቀር ቢችልም የስፔን የሊግ አመራሮች ግን ማንኛውም የመገንጠል ሁኔታ ከስፔኑ ውድድር ውጪ እንደሚያደርጋቸው ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።

የስፔን ሊግ ፕሬዝዳንት የሆኑት ሃቪየር ቴባስ ይህን አስመልክተው ሲናገሩ “በስፖርት ላይ ድንበር የሚባል ነገር የለም። እናም ነገሮች ተፍታተው በግልፅ መቅረብ አለባቸው። ስምምነት ላይ መድረስና የስፔንን የህግ ስርዓት መመርመር  ቀላል ነገር አይደለም። ነገር ግን እነሱ [የካታላን ክለቦች] ያን የሚያደርጉ ከሆነ በስፔን ላ ሊጋ ላይ መጫወት አይችሉም። ነገር ግን እነሱ በዚያ ላይ ይደርሳሉ ብዬ ተስፋ አላደርግም።”በማለት ገልፀዋል።

በነፃነት ውሳኔው ላይ የባርሴሎና አቋም ምንድን ነው?
የባርሴሎና እግርኳስ ክለብ ነፃነቱን አስመልክቶ እስካሁን በይፋ የመጨረሻ ውሳኔ አቋም ላይ ባይደርስም ነገር ግን ማንኛውንም እቅድ ተግባራዊ ከማድርጉ በፊት የህዝቡን መልካም ፈቃድ እየጠበቀ ይገኛል።

ወቅታዊውን የግዛቱን ጉዳይ አስመልክቶ ክለቡ በሰጠው መግለጫ “ባርሴሎና እግርኳስ ክለብ የአባላቱን የተለያዩ አካላት ፍላጎቶችን ያከብራል። የአብዛኛውን የካታላን ህዝብ ፍላጎትም መደገፉንም ይቀጥላል። ይህንንም በሲቪል፣ በሰላም ምሳሌ በሚሆን መንገድ ተግባራዊ ያደርጋል።” ሲል ገልፅዋል።

በመሆኑም ክለቡ የሁለቱን አካላት ውሳኔ በመጠበቅ ቀጣይ እጣ ፈንታውን የመወሰን ተግዳሮት ከፊት ለፊቱ ተጋርጦበታል። ውሳኔው ምን ይሆናል? ያን ጊዜ የሚፈታው ጉዳይ ይሆናል።

የሆነ ሆኖ ግን የኤርነስቶ ቫልቬርዴው ቡድንም በላ ሊጋውና በሻምፒዮንስ ሊጉ ውድድሮች ላይ እንዲሁም የእሁድ አመሻሹን የዝግ ስታዲየም ጨዋታን ጨምሮ ምንም አይነት መንገራገጭ እና መረበሽ ሳይታይበት በዚህ የውድድር ዘመን በሁሉም ውድድሮች ላይ ያደረጋቸውን ጨዋታዎች በሙሉ በማሸነፍ ጉዞውን መቶ በመቶ የተደላደለ አድርጎ በመጓዝ ላይ ይገኛል። 

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s