አርጄንቲና ገብታበት ከነበረው አስቸጋሪ ያለማለፍ አደጋ ኢኳዶርን ከሜዳዋ ውጪ በሊዮኔል መሲ ሃትሪክ 3ለ1 በማሸነፍ የዓለም ዋንጫውን መቀላቀል የምትችልበትን ሶስት ነጥብ ማግኘት ችላለች።
አርጄንቲና የእኩለ ለሊቱን ጨዋታ ያደረገችው በደቡብ አሜሪካው የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የደረጃ ሰንጠረዥ ስድስተኛ በመሆን ነበር።
ነገር ግን ያደረገችውን ጨዋታ ማሸነፍ በመቻሏ ቀደም ብላ ማለፏን ካረጋገጠችው ብራዚል፣ ኡራጓይና ኮሎምቢያ ጋር በቀጥታ የዓለም ዋንጫውን መቀላቀል ችላለች። በአምስተኛ ደረጃ ማጠናቀቅ የቻለችው ፔሩ ደግሞ በሚቀጥለው ወር በሚደረገው የደርሶ መልስ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ የዓለም ዋንጫ ተሳትፏውን የምትወስን ይሆናል።
አርጄንቲናውያኑ ወደቀጣዩ ዙር ለማለፍ ሽንፈትን ማስወገድ የግድ አድርገው ጨዋታቸውን ያደረጉ ቢሆንም የውድድሩ ሁለተኛው ፈጣን ጎል በሆነውና ጨዋታው በተጀመረ ገና በ38ኛው ደቂቃ በኢኳዶሩ ሮማሪዮ ኤብራ በተቆጠረባቸው ግብ ድንጋጤ ውስጥ ገብተው ነበር።
ይሁን እንጂ ሊዮኔል መሲ ከመረብ ላይ ማሳረፍ በቻላቸው ሶስት ግቦች የአርጄንቲናን የሩሲያ 2018 ዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ትኬት መቁረጥ እርግጥ ማድረግ ችሏል።
በሌላ የአህጉሪቱ ጨዋታ በኻመስ ሮድሪጌዝ ግብ ከፔሩ ጋር 1ለ1 በሆነ ውጤት ነጥብ የተጋራችው ኮሎምቢያ የዓለም ዋንጫውን መቀላቀል ስትችል፣ ፔሩም በዚህ ውጤት የቺሊን በብራዚል 3ለ0 መሸነፍ ምክኒያት በአምስተኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ የዓለም ዋንጫውን ለመቀላቀል የደርሶ መልስ ጨዋታን የማግኘት ዕድል ያገኘች የደቡብ አሜሪካ ሃገር መሆን ችላለች።
ማለፏን ከመጨረሻው ጨዋታ በፊት ያረጋገጠችው ብራዚል በሁለተኛው አጋማሽ በተቆጠሩ የፓውሊንሆ አንድ ግብና የማንችስተር ሲቲው አጥቂ ጋብሬል ኻሱስ ሁለት ግቦች የቺሊን የዓለም ዋንጫ የማለፍ ዕድል አምክነውታል።
ልዊስ ስዋሬዝ ባስቆጠራችው ሁለት ግቦች ታግዛ ቦሊቪያን 4ለ2 በሆነ ውጤት ማሸነፍ የቻለችው ኡራጓይ በደረጃ ሰንጠረዡ ላይ በሁለተኛነት በመቀመጥ የፊታችን ክረምት የሚደረገውን የሩሲያ የዓለም ዋንጫ ውድድር መቀላቀል የቻለች ሃገር ሆናለች።
የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ማድረግ ከሚያስገድደው አምስተኛ ደረጃ በአንድ ነጥቦች ብቻ ከፍ ብላ የምሽቱን ጨዋታ ያደረገችው ፓራጓይ በ84ኛው ደቂቃ በተቆጠረባት ግብ በቬንዙዌላ በገዛ ሜዳዋ 1ለ0 ተሸንፋ የዓለም ዋንጫ ተሳትፎን ያጣች ዕድለቢስ ሃገር ሆናለች።