የቀድሞ የአርሰናል ተጫዋች የነበረው እንዲሁም አሁን የስካይ ስፖርት ተንታኝ እና የሳምንቱ እንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ግምቶችን በመስጠት የሚታወቀው ፖል ሜርሰን በ49 አመቱ ወደ እግርኳስ ሊመለስ ነው፡፡
ሜርሰን ሊጫወትለት የተስማማው ለዌልሱ የአራተኛ ዲቪዝዮን ተሳታፊው ኬራው ለሚባል ቡድን ሲሆን የቡድኑ ጸሀፊ ለሜርሰን ለቡድኑ እንዲጫወት ያቀረቡለትን ጥያቄ ሜርሰን በሳምንቱ መጨረሻ ከስካይ ስፖርት ጋር በገባው ውል መሰረት ፕሪምየርሊግ ጨዋታዎች ላይ ትንታኔ ስለሚሰጥ እንደማይመቸው መናገር ችሎ ነበር፡፡
ነገርግን የቀድሞ ተጫዋቹን አጥብቆ የፈለገው የዌልሱ ቡድን በድጋሚ ወደ ሜርሰን በመቅረብ በሳምንቱ አጋማሽ ብቻ ለሚደረጉ ጨዋታዎች ለቡድናቸው እንዲጫወትላቸው ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተሰምቷል፡፡
በዚህም መሰረት ፖል ሜርሰን መጀመሪያውን ጨዋታ እሮብ ጥቅምት 18 ከኬሪው የከተማ ባላንጣ ከሆነው ፖንቲክሉን ጋር ይጫወታል፡፡
ለስካይ ስፖርት ሀሳቡን የሰጠው ፖል ሜርሰን “ለነሱ መጫወት እችል እንደሆነ መጥተው ጠየቁኝ ነገርግን በሳምንቱ አጋማሽ ከሆነ መጫወት እንደምችል ነግሬያቸዋለው፡፡ ስለዚህ እሮብ በደርቢው ጨዋታ ላይ እሰለፋለው፡፡” ሲል ተናግሯል፡፡
የሜርሰን አዲሱ ቡድን ኬራው በሚጫወትበት ሊግ ላይ 16 ቡድኖች የሚሳተፉ ሲሆን ቡድኑ 13ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡