በክረምቱ የዝውውር መስኮት ባርሴሎናን በመልቀቅ የፈረንሳዩን ሀብታም ክለብ ፒኤስጂን የአለም ሪከረድ በሆነ ሂሳብ የተቀላቀለው ኔይማር ጉዳይ አሁንም መነጋገሪያነቱን ቀጥሏል፡፡
በተለይም ከወደ ፈረንሳይ የተሰማው ዜና እንደሚያመለክተው ከሆነ ደግሞ የፒኤስጂ ተጫዋቾች ለእርሱ በክለቡ እየተደረገለት የሚገኘው የተለየ እንክብካቤ እንዳላስደሰታቸው ነው፡፡
የታመኑ ዘገባዎችን በመስራት አንቱታን ያተረፈው ለ ፓሪያሰያን ታማኝ ምንጮቼ ነገሩኝ እንደዘገበው ከሆነ ደግሞ ተጫዋቹ በክለቡ ሀላፊዎች የሚደረግለት ቅጥ ያጣ አይዞክ ባይነት በክለቡ ኮከቦች አልተወደደም ገና ከወዲሁ ለፈረንሳዩ ክለብ 10 ግቦችን ማስቆጠር የቻለው ብራዚላዊው ጥበበኛ በልምምድ ማዕክል ጭምር የተለያዩ ድጋፎች የሚደረጉለት ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ በልምምድ ወቅት በእርሱ ላይ ፋውል የሰራ ተጫዋች ከበድ ያለ ተግሳፅ ከቡድኑ የበላዪች እንደሚደርስበት ነው፡፡
ይህም ገና ከወዲሁ የፔይዤን ተጫዋቾች እያስከፋ እና ሞቾት እየነሳ ይገኛል፡፡ በዚህም ምክንያት የመልበሻ ክፍሉ ሰላም እንዳይደፈርስ ያሰጋልም ተብሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አርጀንቲናዊው አማካይ ሀቪየር ፓስቶሬ ከዚህ ቀደም ይለብሰው የነበረውን የ10 ቁጥር ማሊያውን ካለ እርሱ ፍቃድ ለኔይማር መሰጠቱ እንዳስከፋው የሚታወስ ሲሆን ከኡራጋዊው የክለቡ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ኤዲሰን ካቫኒ ጋር በፍጹም ቅጣት ምት ጉዳይ ዙሪያ ገብተውት የነበረው እሰጣ ገባም የሚረሳ አይደለም፡፡
የፈረንሳዪ ክለብ ክዋክብት በኔይማር ቅጥ ያጣ እንክብካቤ ደስተኛ ባይሆኑም የቀድሞ የባርሴሎና ኮከብ ግን ከፓርክ ደፕሪንስ እስደናቂ ብቃቱን በማሳየት ላይ የሚገኝ ሲሆን ከወዲሁም 10 ግቦችን ከመረብ ማገናኘት ችሏል፡፡