በስታዲዪ ሞንትቪሊ በተደረገው 10ኛው ሳምንት የላሊጋ ጨዋታ ሪያል ማድሪድ ያልተጠበቀ ሽንፈት አስተናገደ፡፡ ሎስ ብላንኮዎቹ በቀላሉ 3 ነጥቦች እንደሚያገኙ ቅደመ ግምት አግኝተውበት በነበረው ጨዋታም በአዲስ አዳጊው ጂሮና አስደንጋጭ የተባለ የ2-1 ሽንፈት ደርሶባቸዋል፡፡
ሪያል ማድሪዶች ስመ ጥሮቹን ክርስትያኖ ሮናልዶ ሰርጂዮ ራሞስ ካሪም ቤንዜማን በዚህ ጨዋታ ቅድምያ በማሰለፍ ቢጀምሩም በጂሮና ያልጠተበቀ ሽንፈት ደርሶባቸዋል፡፡ ሎስ ብላንኮዎቹ በኢስኮ ግብ ቀዳሚ መሆን ቢችሉም ጂሮናዎች በክርስትያን ስቱዋኒ አማካኝነት ባስቆጠሩት ግብ አቻ ከሆኑ በኋላ በእለቱ ኮከብ ሆኖ ባመሸው ፓብሎ ማፍዮ አማካኝነት በተገኘች 2ኛ ግብ ድል ማድረግ ችለዋል፡፡
የሪያል ማድሪዶቹ ኮከቦች ፖርቱጋላዊው ክርስትያኖ ሮናልዶ እና ካሪም ቤንዜማ በምሽቱ ለጎል የቀረቡ ኳሶችን ቢሞክሩም ኳስና መረብን ሳያገናኙ ወጥተዋል፡፡ ይህንን ተከትሎም ሪያል ማድሪዶች ገና ከወዲሁ ከሊጉ መሪ ባርሴሎና በ8 ነጥቦች ርቀው በ20 ነጥብ እና በ10 ንጹህ ግቦች በላሊጋው 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡
ሎስ ብላንኮዎቹ የዛሬ ምሽቱን ሽንፈት ተከትሎም ከዚህ ቀደም በላሊጋው አዲስ ካደጉ ክለቦች ጋር ካደረጉት 59 ጨዋታዎች በኋላ ሽንፈት ያስተናገዱ ሲሆን ከዚህ ቀደም ለመጨረሻ ጊዜ ሊጉን በተቀላቀለ አዲስ ክለብ ሽንፈት አስተናግደው የነበረው በ2008 ከአልሜሪያ ጋር አድርገውት በነበረው ጨዋታ ነው፡፡