የ2017 የአፍሪካ ቻምፕየንስ ሊግ ዛሬ በካዛብላንካ ፍጻሜውን ያገኛል

ሁለቱ የሰሜን አፍሪካ ፈርጦች የሞሮኮው ዋይዳድ ካዛብላንካ እና የግብፁ አል አህሊ በካዛብላንካ ሞሀመድ አምስተኛ ስታድየም በሚያደርጉት የዛሬው የፍጻሜ የመልስ ፍጥጫ የ2017 የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ አሸናፊ ቡድን ይሞሸራል።

ሰሜን አፍሪካዎች የበላይነታቸውን በያዙበት የ2017 የካፍ ቻምፕየንስ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታ ዛሬ ማምሻውን ሲጠናቀቅ ዋይዳድ እና አል አህሊ የመጨረሻውን የሞት ሽረት ፍልሚያቸውን እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

የውድድሩ የዋንጫ ልማደኛ የሆኑት “ቀያይ ሰይጣኖቹ” አል አህሊዎች ለዘጠነኛ ጊዜ አሸናፊ በመሆን ቁጥር ስፍር ለሌለው ደጋፊያቸው ዋንጫውን በማበርከት ዳግም የአፍሪካ ቁንጮ ሆነው በአለም የክለቦች ውድድር ላይ ለመሳተፍ ቋምጠዋል።

ከጎረቤታቸው ዛማሌክ ትችት ለማምለጥ እንዲሁም በነሱ ሽንፈት የዛማሌክ ደጋፊዎችን ደስታ ከማየት ሞታቸውን የሚመርጡት ቀያይ ሰይጣኖች በ 2006 እና 2012 ላይ የሰሩት ገድል ዛሬም መድገም ይጠበቅባቸዋል።

ከአውሮፓ ቻምፕየንስ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታ በተለየ በደርሶ መልስ የሚደረገው የአፍሪካ ቻምፕየንስ ሊግ የ 2017 የፍጻሜ የመጀመሪያ ጨዋታ ባለፈው ቅዳሜ በአሌክሳንድሪያ ቦርጅ ኤል አረብ ስታድየም ተካሂዶ እንግዳዎቹ ዋይዳድ ካዛብላንካን የሚጠቅም ውጤት ተመዝግቧል።

ኢትዮጵያዊው በአምላክ ተሰማ የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ 1 ለ 1 መጠናቀቁን የሚገልፀውን የመጨረሻውን ፊሽካ ሲያሰሙ ውጤቱ ባለሜዳዎቹን አል አህሊዎችን በቁጭት አንገት ያስደፋ እንግዳዎቹን ዋይዳዶችን ደግሞ በበጎ መልኩ ፈገግ ያደረገ ነበር።

አህሊዎች 2006 የፍጻሜ የመጀመሪያ ጨዋታ በተመሳሳይ በሜዳቸው ካይሮ ስታድየም ላይ ከቱኒዚያው ሴፋክሲያን ጋር 1 ለ 1 ቢለያዩም በመልሱ ጨዋታ በሞሀመድ አቡትሪካ የግራ እግር ድንቅ ጎል አሸናፊ ሆነው ዋንጫውን አንስተዋል።

በተመሳሳይ 2012 የፍጻሜ  የመጀመሪያ ጨዋታ አል አህሊ ሌላውን የቱኒዚያ ክለብ የሆነውን ኤስፔራንስን በሜዳው አስተናግዶ 1 ለ 1 ተለያይቶ በመልሱ 2 ለ 1 አሸንፎ ዋንጫ አንስተው የፈነጠዙበት ታላቅ ገድል ዛሬም መድገም እንደሚችሉ ተስፋ አድርገዋል።

በልምምድ ቦታ ላይ የተገኙት የአል አህሊ ደጋፊዎች

ወደ ሞሮኮ ከማቅናታቸው ቀደም ብሎ ያደረጉት ልምምድ ላይ ደጋፊዎቻቸው እንዲገኙ የስታድየሙን በር ክፍት ያደረጉት አል አህሊዎች ከ 10ሺ በላይ ደጋፊዎች በልምምድ ላይ ተገኝተው ተጨዋቾቹን በማበረታታት ከአደራ ጋር ሸኝቷቸዋል።

የክለቡ አሰልጣኝ የሆኑት ሆሳም ኤል ባድሪ “ተጫዋቾቼ ልምድ ያላቸው በመሆኑ ከአል አህሊ ጋርም ይሁን ከብሔራዊ ቡድን ጋር በእንደዚህ አይነት ወቅት እንዴት አድርገው ጨዋታውን መምራት እንደሚችሉ ያውቁበታል።ሚዛናዊ የሆነ ዳኝነት እንደሚኖር አስባለው።ሁሉም ሰው በመጀመሪየ ጨዋታ የነበረውን ዳኝነት ተመልክቷል።ዋንጫውንም ለማንሳት እንታገላለን።” ሲሉ ተናግረዋል።

ባለሜዳዎቹ ዋይዳዶች በውድድሩ አንድ ጊዜ ብቻ ዋንጫ ማንሳት ቢችሉም ጠንካራ ተፎካካሪነታቸው ግን የሚካድ አይደለም።

የ2016 የካፍ ቻምፕየንስ ሊግ ውድድር ላይ በግማሽ ፍጻሜው በግብፁ ዛማሌክ በአጠቃላይ ውጤት ቢሸነፉም ከሜዳቸው ውጪ ይዘውት የመጡት የ 4 ለ 0 ሽንፈት ለመቀልበስ በሜዳቸው ያደረጉት ጥረት አስደናቂ ነበር።

በወቅቱ በመልሱ ጨዋታ በሜዳቸው በድንቅ ተነሳሽነት እና ፍልሚያ ዛማሌክን 4 ለ 1 በማሸነፍ ለፍጻሜ ለመቅረብ ተቃርበው ነገርግን ያልቻሉበትን ወኔ ዛሬም ይፈልጉታል።

ዘንድሮም በምድብ ማጣሪያው ከዛሬው ተፋላሚው አል አህሊ ጋር አንድ ላይ ተደልድለው የነበረ በመሆኑ ሁለቱ ቡድኖች በደንብ አድርገው እንደሚተዋወቁ መረዳት ይቻላል።

ቤንቻርኪ የዋይዳዶች ቁልፍ ተጫዋች ሆኗል

በምድብ ማጣሪያው ያደረጓቸው የእርስበርስ ጨዋታዎች ሁለቱም በሜዳቸው የ 2 ለ 0 አሸናፊዎች መሆን ችለው እንደነበር ይታወሳል።

ዋይዳዶች በምሽቱ ጨዋታ ላይም ባለሜዳዎቹ በደጋፊያቸው ታግዘው አሸናፊ የመሆን እድል እንዳላቸው ቢነገርም ደጋፊያቸው ጫና ውስጥ ሊከቷቸው እንደሚችሉ የአል አህሊ አሰልጣኝ የሆኑት ሆሳም ኤል ባድሪ ገልፀዋል።

ሆሳም ኤል ባድሪ በመግለጫቸው “ዋይዳዶች ብዙ ደጋፊዎች ያላቸው ናቸው ነገርግን አፍሪካ እና በአረብ ኤሚሬትስ ብዙ ደጋፊ ያለው አል አህሊ ነው። እነሱ በሜዳቸው ስለሚጫወቱ ጫናው የሚኖረው እነሱ ላይ እንጂ እኛ ላይ አይደለም።” ሲሉ ተናግረዋል።

የዋይዳዱ አሰልጣኝ ሁሲን አሞታ በበኩላቸው የ 1 ለ 1 ውጤቱን ለማስጠበቅ እስከ ሞት እንደሚታገሉ ነገርግን አውቶቢስ አቁመው ተከላክለው እንደማይወጡ አሳውቀዋል።

የዋንጫ አሸናፊው የ 2.5 ሚሊየን ዶላር ሲሸለም በዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ በሚካሄደው የፊፋ የአለም የክለቦች ዋንጫ ላይም አፍሪካን ወክሎ ይሳተፋል።

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s