ዊዳድ ካዛብላንካ ከ 25 አመት በኋላ የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ዋንጫ አሸናፊ ሆነ

በካዛብላንካ መሀመድ አምስተኛ ሰታድየም የተደረገው የ 2017 የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የፍጻሜ የመልስ ጨዋታ የሞሮኮው ዊዳድ ካዛብላንካ ከእልህ አስጨራሽ ፍልሚያ በኋላ በደማቅ ደጋፊዎቹ ፊት የግብፁን አል አህሊን በመርታት የዋንጫ ባለቤት መሆኑን አረጋገጠ።

ከየካቲት ወር ጀምሮ በአዲስ ቅርፅ የተካሄደው 16 ቡድኖች በአራት ምድብ ተደልድለው ያደረጉት ውድድር ከብርቱ ፉክክር በኋላ በመጨረሻም የዋንጫ አሸናፊው ቡድን ተለይቷል።

የግብፁ አል አህሊ እና የሞሮኮው ዊዳድ ካዛብላንካ ለፍጻሜ ያደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ በአሌክሳንደሪያ ቡርጅ ኤል አረብ ስታድየም 1-1 በመለያየታቸው የምሽቱ የመልስ ጨዋታ በከፍተኛ ጉጉት ተጠብቋል።

ቤንቻርኪ ለዊዳዶች ስኬት ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል

ስምንት ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ የሆኑት አል አህሊዎች በሜዳቸው ያደረጉት ጨዋታ በአቻ ውጤት ቢያጠናቅቁም ከፍተኛ ልምድ ያላቸው በመሆኑ በ 2006 እና 2012 ላይ የሰሩትን ገድል ለመድገም ወደ ሞሮኮ አቅንተው ነበር።

ቡድኑ በሁለቱ አመታት በተመሳሳይ በፍጻሜ የመጀመሪያ የሜዳው ጨዋታ ላይ 1 ለ 1 ተለያይቶ ከሜዳው ውጪ በማሸነፉ የዋንጫ ባለቤት መሆን ችሎ ነበር።

በምሽቱ ጨዋታ ላይ ጎል የግድ ያስፈልጋቸው የነበሩት አል አህሊዎች ፈጣን አጀማመር በማድረግ በቀኝ መስመር በሞአሜን አማካኝነት ወደ ሳጥን አደገኛ ኳሶችን ሲያሻግሩ ታይተዋል።

ከዚሁ ከቀኝ መስመር የተሻገረው እና አዛሮ የጎል አጋጣሚ አግኝቶ እንግዳው ቡድን ቀድሞ ማስቆጠር የሚችልበትን ያልተጠቀመበት ይጠቀሳል።

በሁለተኛው ግማሽ የዊዳድ ደጋፊዎች የሚጨስ ተቀጣጣይ ነገር በማንደዳቸው ሜዳው በጭስ በመታፈኑ ዳኛው ለአንድ ደቂቃ የሚሆን ጨዋታውን አቋርጠው ነበር

ከ25ኛው ደቂቃ በኋላ የተረጋጋ እንቅስቃሴ ያደረጉት ዊዳዶች 29ኛው ደቂቃ ላይ ካድሩፍ ከርቀት የመታው የግቡ አንግል ሲመልስበት ሞአሜን በበኩሉ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ለ አል አህሊዎች ወርቃማ እድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

ከእረፍት መልስ የመጀመሪያው ደቂቃ ላይ ቤንቻርኪ ያሾለከውን ኳስ ኤልሀዳድ ሞክሮ ወደ ውጪ ወጥቶበታል።

አል አህሊዎች ወደ ጎል በመጠጋት የተሻሉ የነበሩ ቢሆኑም ጥብቅ የነበረውን የዊዳድ የተከላካይ ክፍል መፈተን ከብዷቸው ታይቷል።

የጨዋታው ብቸኛ ጎል በቤንቻርኪ የግል ጥረት ወደ ሳጥን ያሻማውን ኤል ካርቲ ከሁለት ተከላካዮች መሀል በጭንቅላቱ ገጭቶ በማስቆጠሩ ዊዳድ ካዛብላንካ በአጠቃላይ ድምር ውጤት 2 ለ 1 በማሸነፍ የዋንጫ ባለቤት ሆነዋል።

ይህም ከ 1992 በኋላ የካፍ ቻምፕየንስ ሊግ ዋንጫን ለመጀመሪያ ጊዜ አሸናፊ እንዲሆኑ ሲያስችላቸው በአጠቃላይ ለሁለተኛ ጊዜ የድሉ ባለቤት መሆን ችለዋል።

ካፍ ለውድድሩ አሸናፊ ለሽልማት ያዘጋጀውን 2.5 ሚሊየን ዶላር አሸናፊዎቹ የሚያገኙ ሲሆን በዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ በሚካሄደው የፊፋ የክለቦች የአለም ዋንጫ ላይም አፍሪካን ወክለው ተሳታፊ ይሆናሉ።

የቅዱስ ጊዮርጊሱ ሳልሀዲን ሰኢድ እና የኤስፔራንሱ ታሂር ኬኒሱ ደግሞ ሰባት ጎል በማስቆጠር የውድድሩ ኮከብ ጎል አስቆጣሪ ሆነው አጠናቀዋል።

Advertisements