ስንብትና አቀባበል / ዌስትሀም ስላቪያን ቢሊችን ማሰናበቱን ማስታወቁን ተከትሎ ዴቪድ ሞየስን ለመቅጠር እንቅስቃሴ ላይ መሆኑ ተገለፀ


ዌስትሀም ስላቪያን ቢሊችን አሰናብቶ ዴቪድ ሞየስን በስድስት ወራት መነሻ የውል ስምምነት ለመቅጠር እንቅስቃሴ ላይ መሆኑ ተገልጿል። 

የዋና ከተማው ክለብ ቅዳሜ በሊቨርፑል የ 4-1 ሽንፈት ከደረሰበት በኋላ በወራጅ ቀጠና ውስጥ መዳከር የጀመረ ሲሆን አሰልጣኙን በማሰናበትም በሞየስ ለመተካት እንቅስቃሴ ላይ ነው። 

ከቢሊች መሰናበት ጋር በተያያዘ እየወጡ ያሉ መረጃዎች እያሳዩ እንዳሉት ከሆነ ለሞየስ እስከ ውድድር ዘመኑ መጨረሻ የሚቆይ ውል የቀረበላቸው ሲሆን የስኮትላንዳዊው ቀጣይ የመዶሻዎቹ ቤት ቆይታም ከመነሻ ውሉ መጠናቀቂያ ላይ እንደሚለይለት ተያይዞ ተነግሯል። 

ዌስትሀም ጉዳዩን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ “ዌስትሀም ዩናይትድ በዛሬው ዕለት ስላቪያን ቢሊች ከክለቡ መልቀቁን ለማረጋገጥ ይችላል።” ሲል አስታውቆ ቢሊች በክለቡ ለነበራቸው ቆይታ ያለውን ምስጋናና ክብር ገልጿል።  

ከቢሊች በተጨማሪም ምክትሎቻቸው የነበሩት ኒኮላስ ጁርሴቪክ፣ ኤዲን ቴርዚክ፣ ጁሊያን ዲክስ እና ሚሊጄንኮ ራክም ከክለቡ መሰናበታቸውን የለንደኑ ክለብ በመግለጫው ጨምሮ አስረድቷል።

ቢሊችን ለመተካት የታሰቡት ሞየስ አምና ሰርንደርላንድን በፕሪምየር ሊጉ የመጨረሻ ደረጃ አስይዘው ወደታችኛው ሊግ እንዲወርድ ከማድረጋቸው ጋር በተያያዘ ከስራ ውጪ ሆነው የሚገኙ ሲሆን በኤቨርተን ከነበራቸው ስኬታማ ቆይታ በኋላም በማንችስተር ዩናይትድን እና በስፔኑን ሪያል ሶሲዳድ ያልተሳካ ቆይታን ማድረጋቸው አይረሳም።  

ቢሊች በ 2015 ዌስትሀምን ከያዙ ወዲህ በመጀመሪያ የውድድር ዘመናቸው ክለቡ በሰባተኛነት እንዲያጠናቅቅ ሲያስችሉ ባሳለፍነው የውድድር ዘመን ደግሞ ለመዶሻዎቹ 11ኛ ደረጃን ለማስገኘት በቅተዋል። 

Advertisements