አቤቱታ / ሶስቱ ክልሎች የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ላይ ያላቸውን ቅሬታ አቀረቡ

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባኤ ከፊታችን ሀሙስ ጀምሮ በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል እንደሚደረግ ይጠበቃል፡፡ከዚህ ጠቅላላ ጉባኤ መካሄድ ቀናት በፊት ግን ጠቅላላ ጉባኤው ይካሄድበታል ተብሎ የነበረው የአፋር ክልልን ጨምሮ የጋምቤላ እና ሀረሪ ክልሎች  የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን  ላይ ያላቸውን ተቃውሞ በማስመለከት በዛሬው እለት በኢትዮጵያ ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

የአፋር ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት የሆኑት አቶ መሀመድ በእለቱ ጋዜጣዊ መግለጫውን ያስጀመሩ ሲሆን በመጀመሪያም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን  ለአፋር ክልል የዘንድሮውን ጠቅላላ ጉባኤ እንደምታሰናዳ አሳውቆ በመጨረሻም ውሳኔውን መሻሩ  እርሳቸውን ጨምሮ መላውን የክልሉን ነዋሪ እንዳሳዘነ ገልጸው የፊታችን ሀሙስ በሚጀመረው ጠቅላላ ጉባኤም ፌዴሬሽኑ ለአፋር እግር ኳስ ፌዴሬሽን  አሳማኝ ምክንያት እንዲያቀርብ የጠየቁ ሲሆን ያ የማይሆን ከሆነ ግን አሁንም ተቃውሞቻውን እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል፡፡

በተጨማሪም ፊፋ ለኢትዮጵያ ምርጫው ለጊዜው ይቆይ ማለቱን ተከትሎ የመጣውን ጥያቄ እንቀበላለን ያሉት የአፋር እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንቱ ጉባኤው ህግን የተከተለ ስላልነበረ የፊፋን ውሳኔ እንደግፋለን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም የፊፋን ውሳኔን መተግበር አለበት ሲሉ አሳውቀዋል፡፡

የጋምቤላ ክልልን በመወከል በዚህ ስብሰባ ላይ የተገኙት ጃንቻ ንኮት በበኩላቸው ይህ የህዝብ ጥያቄ ነው የእኛ ብቻ አይደለም ነገ እንዲህ አይነቱ ጉዳይ በእኛም ላይ ሊደርስ ይችላል በማለት ከአፋር ክልል ጎን መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም ከፊፋ የመጣውን ጥያቄ ክልላቸው እንደሚደግፈው እና በጠቅላላ ጉባኤው ላይም ይህንን ሀሳብ ለጉባኤተኛው ለማንሳት እንደተሰናዱ አሳውቀዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለም የፊታችን ሀሙስ በሚጀመረው ጠቅላላ ጉባኤም ለቀጣዮቹ 4 አመታት የኢትዮጵያን እግር ኳስ የሚመሩት ሀላፊዎች እንደሚመረጡ ሲነገር  ቢሰንብትም ፊፋ ምርጫው ደንብን ያሟላ አይደለም እና  ምርጫውን አዘግዩልኝ ማለቱን ተከትሎ ምርጫው ለሌላ ጊዜ እንደሚተላለፍ የሚጠበቅ ሲሆን ጠቅላላ ጉባኤው ግን ለሁለት ቀናት የሚካሄድ ይሆናል፡፡

 

Advertisements