ክላውድ ማኬሌሌ ከስዋንሲ ሲቲ ረዳት አሰልጣኝነት በመልቀቅ ወደ ቤልጄም አቀና

የቀድሞ የሪያል ማድሪድ እና የቼልሲ ተጫዋች የነበረው ክላውድ ማኬሌሌ ከስዋንሲ ረዳት አሰልጣኝነት ሀላፊነቱ በመልቀቅ የቤልጄሙን ቡድን ለማሰልጠን ተስማምቷል።

2002 ላይ ከሪያል ማድሪድ ጋር የቻምፕየንስ ሊግ ዋንጫን ማንሳት የቻለው የ44 አመቱ ማኬሌሌ ከ 2011 እስከ 2014 በፓሪስ ሴንት ጄርሜይን የካርሎ አንቼሎቲ እና የሎረ ብላ ረዳት አሰልጣኝ ሆኖ በመስራት ጥሩ ልምድ መቅሰም ችሏል።

ፓል ክሌመንት የስዋንሲ አሰልጣኝ ሆነው ከተሾሙ በኋላም በፒ ኤስጂ አብሯቸው የሰራው ወዳጃቸውን ባለፈው ጥር ወር ላይ ረዳት አሰልጣኛቸው አድርገው ወደ ዌልስ እንዲመጣ አድርገውታል።

ማካሌሌ በስዋንሲ የነበረው ቆይታም ከዋና አሰልጣኙ ፓል ክሌመንት ጋር በመሆን የዌልሱን ቡድን በፕሪምየርሊጉ እንዲሰነብት መርዳት ችሏል።በተለይም በሁለተኛው ዙር ላይ ቡድኑ ካደረጓቸው 19 ጨዋታዎች 28 ነጥቦችን በማሳካት 15 ኛ ደረጃን አግኝቶ እንዲያጠናቅቅ አድርገዋል።

ነገርግን እራሱን ችሎ የዋና ቡድን አሰልጣኝ ለመሆን ካለው ፍላጎት የተነሳ ወደ ቤልጄም በማቅማት የውድድር ዘመኑ በውጤት ማጣት እየዳከረ የሚገኘው ካስ ኡውፐን የሚባለውን ቡድን ለማሰልጠን  እንደተስማማ ታውቋል።

አዲሱ ክለቡ በቤልጄም ሊግ ላይ ሁለት ጨዋታዎችን ብቻ በማሸነፍ የመጨረሻ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን የቡድኑን አሰልጣኝ ጆርዲ ኮንዶምን ካሰናበቱ በኋላ ተተኪ አሰልጣኝ ሲፈልጉ ቆይተዋል።

ማካሌሌ በአዲሱ ስራው የቤልጄሙን ቡድን ከገጠመው የውጤት እጦት ማላቀቅ የመጀመሪያ የቤት ስራው ሲሆን ይህም በክለቡ አስተዳዳሪዎች በጥብቅ እንደተነገረው ታውቋል።

ክለቡ በመግለጫው”ስዋንሲ ያሉ ሁሉም ሰዎች ማካሌሌ ለክለቡ ላበረከተው አስተዋፅኦ እያመሰገንን በቀጣይ ስራው መልካም እድል እንዲገጥመው እንመኛለን።” ሲሉ መልካም ምኞታቸውን ገልፀውለታል።

Advertisements