ፔፕ ጓርዲዮላ ከሲቲ ጋር በአሰልጣኝነት ዘመኑ ምርጥ አጀማመር ማድረግ ቻለ

የማንቸስተር ሲቲው አሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ ትናንት አርሰናልን ካሸነፈ በኋላ በባርሴሎና እና በባየርሙኒክ በቆየበት ወቅት በተሻለ ምርጥ አጀማመርን ከእንግሊዙ ቡድን ጋር ማድረግ ችሏል፡፡

ማንቸስተር ሲቲ በእንግሊዝ ፕሪምየርሊግ ከተከታዩ የከተማው ባላንጣው ዩናይትድ በስምንት ነጥብ ከወዲሁ መምራት ችሏል። 

ቡድኑ ካለፉት 11 የ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ሁለት ነጥብ ብቻ የጣለ ሲሆን 38 ጎሎችን በማስቆጠር ድንቅ ጅማሮ ማድረግ ችሏል፡፡

ቡድኑ የተቆጠረበት ሰባት ጎሎች ብቻ በመሆኑ በማጥቃት ብቻ ሳይሆን በመከላከልም የሚታማ እንዳልሆነ በተጨባጭ ማስመስከር ችሏል፡፡

ለዚህ ደግሞ ትልቁን ድርሻ ሊይዝ የሚችለው የቡድኑ አሰልጣኝ ፔፕ ጓርድዮላ ሲሆን የቡድኑን የጨዋታ ውበት ጭምር ማሻሻል ችሏል።

አሰልጣኙ በክረምቱ በርከት ያሉ ተጫዋቾችን አሰናብቶ በምትካቸው ሌሎች ተጫዋቾችን ሲያዘዋውር ቡድኑን በአንዴ ለማዋሀድ እንደሚቸግረው ሲነገር ቢቆይም በተቃራኒው በፕሪምየርሊጉም ይሁን በቻምፕየንስ ሊጉ ውጤታማ ጉዞ እያደረገ ይገኛል፡፡

ፔፕ በሲቲ በ11 ጨዋታዎች መሰብሰብ የቻለው ከዚህ ቀደም ውጤታማ የሆነባቸው ባርሴሎና እና ባየርሙኒክ እያለ በመጀመሪያዎቹ 11 ጨዋታዎች መሰብሰብ ከቻለው የተሻለ እንደሆነ ትናንት አርሰናልን ማሸነፍ ከቻለ በኋላ አረጋግጧል፡፡

በተለይ ስሙን የተከለበት ባርሴሎና ከ 11 ጨዋታዎች ትልቁን ውጤት ማሳካት የቻለው በ 2008/2009 ላይ ሲሆን በወቅቱ መሰብሰብ የቻለው 28 ነጥቦችን ነበር፡፡ ይህ ደግሞ አሁን በሲቲ መሰብሰብ ከቻለው በአራት ነጥብ ያንሳል፡፡

በባየርሙኒክ ደግሞ 2015/2016 ላይ ድንቅ አጀማመር መጀመር የቻለበት አመት ሲሆን በወቅቱ የሰበሰበው 31 ነጥብ አሁን ከሲቲ ጋር ከሰበሰበው ቢስተካከልም ንጹህ ጎል ግን 29 ብቻ የነበረው በመሆኑ አሁን ሲቲዎች ማሳካት ከቻሉት በጎል ያነሰ ሆኗል፡፡

ይህ ቁጥራዊ መረጃ ደግሞ አሰልጣኙ እስካሁን በአሰልጣኝነት ዘመኑ በ11 ጨዋታ ያስመዘገው ትልቁን ውጤት ማሳካት የቻለው አሁን ባለበት ማንችስተር ሲቲ ውስጥ እንደሆነ ማስረጃ ሆኗል።

Advertisements