​ሮናልዶ፣ግሪዝማን እና ስዋሬዝ ከጎል ድርቅ መላቀቅ አልቻሉም

የላሊጋው ኮከቦች የሆኑት የማድሪዱ ሮናልዶ፣የአትሌቲኮው ግሪዝማን እና የባርሴሎናው ስዋሬዝ በጎል ድርቅ መላቀቅ ያልቻሉበት ሌላ ሳምንት ማሳለፍ ችለዋል፡፡

ከሊዮ ሜሲ ጋር ላለፉት አመታት ላሊጋው ኮከብ ጎል አስቆጣሪ በመሆን ሲፎካከር የነበረው ክርስቲያኖ ሮናልዶ ዘንድሮ አጀማመሩ ያማረ ሊሆን አልቻለም፡፡

ከጅምሩ በቅጣት የተወሰኑ ጨዋታዎች ላይ መሳተፍ ያልቻለው ፖርቹጋላዊው ኮከብ ከቅጣት ከተመለሰ በኋላም ከጎል ጋር መተዋወቅ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡

ይህም ከተፎካካሪው ሊዮ ሜሲ ጋር በከፍተኛ ርቀት ላይ አንዲቀመጥ ያስቻለው ሲሆን የዘንድሮ የፒቺቺ አሸናፊ ለመሆን ያለው እድል እየጠበበ መጥቷል፡፡

ትናንት ምሽት ማድሪድ ላስፓልማስን ሲገጥም ሮናልዶ ጎል ሊያስቆጥር እንደሚችል ቢታሰብም ሌላ ያለ ጎል ሳምንት ማሳለፍ ግድ ብሎታል።ሮናልዶ ዘንድሮ በላሊጋው አንድ ጎል ብቻ እንዳስቆጠረ ይታወሳል።

ሁለት ጎሎችን ብቻ ያስቆጠረው የአትሌቲኮ ማድረዱ አጥቂ አንቷን ግሪዝማን ሌላ የጎል መንገዱ የጠፋበት ተጫዋች ሆኗል፡፡

ቡድኑ ከዲፖርቲቮ ላካሮኛ ጋር ሲጫወት ከሜዳ ተቀይሮ እስከመውጣት የደረሰ ሲሆን በጭማሪ ደቂቃ ላይ ቡድናቸው አስቆጥሮ አሸናፊ ሲሆንም የተጠባባቂ ወንበር ላይ ተቀምጦ ተመልክቷል፡፡

ልዊስ ስዋሬዝም እንዲሁ ጎል ካስቆጠረ አምስት ጨዋታዎች የሆኑት በመሆኑና በሜዳ ላይ ያለው እንቅስቃሴ እንደ ቀድሞ አለመሆኑ ለትችት ተጋልጧል።

ስም ካላቸው የላሊጋ አጥቂዎች ምትክ ግን ብዙም ያልተጠበቁ ተጫዋቾች ኮከብ ጎል አስቆጣሪነቱን ከሚመራው ሊዮ ሜሲ ተከትለው ተቀምጠዋል።

ከነዚህ ውስጥ ሲሞን ዛዛ፣ሲድሪክ ባካምቡ፣አንቶኒዮ ሳናብሪያ እና ሮድሪጎ ሞሬኖ ይጠቀሳሉ፡፡

Advertisements