ሀሪ ኬን ለሰሜን ለንደን የደርቢ ጨዋታ እንደሚደርስ ማውሪሲዮ ፓቸቲኖ አሳወቁ

በጥሩ አቋም ላይ የሚገኘው ነገርግን በጉዳት ከእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ውጪ የሆነው ሀሪ ኬን በቀጣይ ሳምንት ከአርሰናል ጋር በሚደረገው ጨዋታ ላይ እንደሚደርስ ታውቋል።

ስፐርሶች ክሪስታል ፓላስን ባሸነፉበት ጨዋታ ላይ መጠነኛ ጉዳት አጋጥሞት ከጋሪዝ ሳውዝጌቱ የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ውጪ የሆነው ኬን በወሳኙ ጨዋታ ላይ ወደ ሜዳ ይመለሳል።

የቡድኑ አሰልጣኝ የሆኑት ማውሪሲዮ ፓቸቲኖ በቀጣይ ሳምንት መጨረሻ ከከተማቸው ባላንጣ የሆኑት አርሰናሎች ጋር በኤምሬትስ ስታድየም ወሳኝ ጨዋታ ያደርጋሉ።

ለዚህ ጨዋታ ደግሞ በጥሩ አቋም ላይ የሚገኘው የአጥቂያቸውን ሀሪ ኬን አገልግሎትን አጥብቀው ይፈልጉታል።ነገርግን የተጫዋቹ መጠነኛ ጉዳት ምናልባትም ከደርቢው ጨዋታ ውጪ እንዳያደርገው ተሰግቶ የነበረ ቢሆንም የቡድኑ አሰልጣኝ ግን ተጫዋቹ ለጨዋታው ብቁ ሆኖ መሰለፍ እንደሚችል አሳውቀዋል።

“ኬን ደህና ነው።ባለፈው ጨዋታ ላይ እንደተመለከታችሁት መጠነኛ ጉዳት አጋጥሞታል።ነገርግን ለቀጣዩ ጨዋታ ይደርሳል።”ሲሉ ማረጋገጫ ሰጥተዋል።

ኬን አርሰናል ላይ ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች ላይ ስድስት ጎሎችን ማስቆጠር በመቻሉ ለጨዋታው ብቁ መሆኑ ለቶተንሀሞች ጥሩ ዜና ቢሆንላቸውም እንደ ዴሊ አሊ፣ሀሪ ዊንክስ፣ሁጎ ሎሪስ፣ሚሼል ቮርም፣ቶቢ አልደርዊርድ እና ቪክቶር ዋንያማ አሁንም ጉዳት ላይ የሚገኙ ተጫዋቾች በመሆናቸው አርሰናልን ከሚገጥመው የስፐርስ የቡድን ስብስብ ውጪ የመሆናቸው እድል የሰፋ ነው።

Advertisements