የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ዲድየር ዴሾ ለአንቶይን ግሪዝማን ድጋፉን ሰጠ

2.jpg

የአትሌቲኮው ማድሪዱ ፈረንሳዊው አጥቂ አንቶይን ግሪዝማን በላሊጋው ከጎል ጋር መጣላቱን ተከትሎ ትችቶች ቢበረቱበትም የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ የሆነው ዲድየር ዴሾ ግን ድጋፉን ሰጥቶታል፡፡

ግሪዝማን እንደ ሮናልዶ እና ስዋሬዝ ሁሉ በላሊጋው የጎሉ መንገዱ ጠፍቶበታል፡፡እስካሁን ድረስ ያስቆጠረው ሁለት ጎሎችን ብቻ ሲሆን በዚህም ምክንያት ትችቶች ከክለቡ ደጋፊዎችም እየቀረበበት ይገኛል፡፡

በተለይም የሚከፈለውን ያህል አገልግሎት አለመስጠቱ ለትችቱ ዋነኛ በር የከፈተ ምክንያት ሆኗል፡፡ሌሎች ደግሞ የተጫዋቹ አቋም ብቻ ሳይሆን የቡድኑም እንቅስቃሴ እና ውጤታማነት በመውረዱ ለአጥቂው አቋም መውረድ ቡድኑን ተጠያቂ አድርገዋል፡፡

የቡድኑ አሰልጣኝ ዲያጎ ሲሞኒ ጭምር ባለፈው ሳምንት ዲፖርተቮ ላካሮኛን ሲገጥሙ በአቋሙ ባለመርካቱ ቡድኑ ጎል በሚያስፈልገው ሰአት ቀይረው ያስወጡት ሲሆን ግሪዝማንም በተጠባባቂ መቀመጫ ላይ ሆኖ የቡድኑን የማሸነፊያ ጎል ለመመልከት ችሏል፡፡

ግሪዝማን ይህን ያህል ትችት እየቀረበበት ቢሆንም ከፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ዲድየር ዴሾ ግን ድጋፍን አግኝቷል፡፡“አንቶይን አሁንም አንቶይን ነው፡፡ሁልጊዜ ያለውን አይነት ብቃት አሁንም አለው፡፡ምናልባት አሁን እንደሚጠበቅበት በከፍተኛ ደረጃ ላይንቀሳቀስ ይችላል፡፡ስለዚህ ምንም የሚያስቆጨኝ ነገር ነገር፡፡ሁሉም ነገር አንጻራዊ ነው፡፡ልንመለከተው የሚገባው የሚጫወትበት ቡድን አቋም ጭምር ነው፡፡አትሌቲኮ ማድሪድም በዚህ አመት በብዙ ጨዋታዎች ላይ አሳማኝ ብቃት እያሳየ አይገኝም፡፡”በማለት የተጫዋቹ የአቋም መውረድ ከቡድኑ አቋም መውረድ ጋርም የተያያዘ መሆኑን በማሳወቅ ድጋፍ ሰጥቶታል፡፡

አትሌቲኮ ማድሪድ በላሊጋው በተደጋጋሚ ነጥብ በመጣሉ ከባርሴሎና በስምንት ነጥብ አንሶ የሚገኝ ሲሆን በቻምፕየንስ ሊጉም  ቼልሲ እና ሮማ በሚገኙበት ምድብ ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል፡፡በተለይም ከአዘርባጃኑ ቃራባግ ጋር ሁለት ጊዜ አቻ ከተለያዩ በኋላ በቀጣዮቹ ጨዋታዎች የራሱን የቤት ስራ ተወጥቶ የአዘርባጃኑ ክለብ ሌሎቹን የምድቡ ቡድኖችን 〈ቼልሲ እና ሮማ〉 ነጥብ እንዲያስጥልላቸው ምኞት ውስጥ ገብተዋል፡፡

ግሪዝማን ለፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን 47 ጨዋታዎችን አድርጎ 18 ጎሎችን ማስቆጠር የቻለ ሲሆን በቀጣይ በአቋም መፈተሻ  ጨዋታ ፈረንሳይ ዌልስን እና ጀርመንን ስትገጥም እንደሚሰለፍ ይጠበቃል፡፡

Advertisements