ሰርጂዮ ራሞስ የክርስቲያኖ ሮናልዶን አስተያየት አጣጣለ


በእንግሊዙ ዌምብሌይ ስቴዲየም በሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ ምሽት ሪያል ማድሪድ በቶተንሐም ሆትስፐር የደረሰበትን ሽንፈት ተከትሎ ስለቡድኑ ያለውን አስተያየት ሰጥቶ የነበረው ክርስቲያኖ ሮናልዶ ሀሳቡን የሚያጣጥል አቋም ከቡድኑ አምበል ሰርጂዮ ራሞስ ደርሶታል፡፡

ሮናልዶ ከለንደኑ ሽንፈት በኋላ ቡድን ካለፈው የውድድር አመት የወረደ አቋም ላይ እንደሚገኝ ጠቅሶ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ቡድኑ ነባር ከዋክብቶችን ያለተተኪ መልቀቁ እንደሆነ ተናግሯል፡፡

እንደ ሮናልዶ ሀሳብ ክለቡ ሪያል ማድሪድ አልቫሮ ሞራታን ፣ ፔፔን እና ዳኒሎን በሽያጭ ማጣቱ እንዲሁም ሀሜስ ሮድሪጌዝን በውሰት ያጣው እና በለቃቂዎቹ ምትክ ባለልምድ ተተኪዎች ባለመኖራቸው ቡድኑ ከባለፈው አመት ዝቅ ባለ አቋም ላይ ይገኛል፡፡

ጉዳዩን አስመልክቶ ከካዲና ሰር ካር ቆይታ የነበረው አምበሉ ሰርጂዮ ራሞስ የሮናልዶን ሀሳብ ” ስህተት” ሲል አጣጥሎታል፡፡

ጠንካራው የመሃል ተከላካይ እንዳለው ” ቡድኑ ተዳክሟል በሚለው አቋም አልስማማም፡፡ ሱፐር ካፑን ባሸነፍንበት ወቅት ማንም እንደዚህ አይነት ሀሳብ አልነበረውም ፤ አሁን ባለው ስብስብ ዋንጫዎችን አሸንፈናል፡፡ ቡድኖች መቀያየራቸው እንደሆነ የማይቀር ነው፡፡” ሲል ተናግሯል፡፡

ራሞስ ይህን ቢልም ባለፈው የውድድር አመት የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግና ላሊጋውን ደርቦ በማሸነፍ ድንቅ አመትን ያሳለፈው ሪያል ማድሪድ በውድድር አመቱ ከዋነኛ ተቀናቃኙ ባርሴሎና በ 8 ነጥብ ርቆ በውጤት ቀውስ እየታመሰ ይገኛል፡፡

Advertisements