ቀጥታ ስርጭት / የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን 10ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ የመጀመሪያ ቀን ውሎ

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ወሳኝ እና አጨቃጫቂ ውሳኔዎችን ያሳልፍበታል ተብሎ የሚጠበቀውና ዘንድሮ ለአስረኛ ጊዜ ሊደረግ ቀጠነ ቀጠሮ የተያዘለት የመደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ በኢንተርኮንቲነንታል ሆቴል እየተካሄደ ይገኛል። የኢትዮአዲሱ ሚኪያስ በቀለም ጉባኤው ከሚደረግበት ኢንተርኮንቲነንታል የስብሰባ አዳራሽ ወሳኝ ሁነቶችንና የጉባኤውን ሂደቶች እንደሚከተለው በቀጥታ ሊያስመለከተን በእዛ ይገኛል።ምሽት 12:50 ጠቅላላ ጉባኤው የሂሳብ ሪፖርቱን አፅድቆ በቀሩት ጉዳዮች ላይ ለመወያየት በመምሸቱ በቀሪዎቹ አጀንዳዎች ላይ ለመወያየት ለነገ ጠዋት 3:00 ሰአት ቀጠሮ ይዞ የዕለቱን መርሀ ግብር አጠናቋል። እኛም በነገው ዕለት የሚካሄደውን ሁለተኛ ቀን መርሀ ግብር ይዘን ለመገናኘት ቀጠሮ ይዘን ተሰናብተናል። መልካም ምሽት።

ምሽት 12:25 የፌደሬሽኑ የሂሳብ ሪፖርት በውጪ የሂሳብ ኦዲተር ለምላዕተ ጉባኤው እየቀረበ ይገኛል። የሂሳቡ መዝገቡ እንዳሳየው ከሆነም ፌደሬሽኑ 90,000,000 ብር ገቢ ያስገባ ቢሆንም ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት የ 20 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል። 

የፌደሬሽኑ ወጪም ፌደሬሽኑ በአመቱ ካገኘው ገቢ በ 3.5 በመቶ ብልጫ ማሳየቱ ከሂሳብ መዝገቡ ላይ የታየ ሲሆን ጠቅላላ የአመቱ ወጪም 108 ሚሊዮን ብር ገደማ ሆኗል።

ምሽት 12:10 ተጠባቂው 10ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ሰአቱ እየገፋ ሄዶ ይተናቀቃል ተብሎ ከታቀደለት ቀትር 10:30 ለሁለት ያህል ሰአት አልፎ መካሄዱን የቀጠለ ሲሆን በመጨረሻ ጨዋታዎች ባልተገባ መልኩ ወደታችኛው ሊግ ወርደዋል ስለሚባሉት እንደ ጅማ አባቡና አይነት ክለቦችን የተመለከቱ ጥያቄ እየተዥጎደጎደ ይገኛል። ከመድረኩም የተሳታፊውን ጥያቄ ለመመለስ ጥረት ሲደረግ እየታየ ነው። 

በዚህ ሁሉ መሀከል ግን ጉባኤው በመጀመሪያ ዕለት መርሀ ግብሩ  ያካተታቸው የ 2010 በጀት ዕቅድ እና የፌደሬሽኑን መተዳደሪያ ደንብ ማሻሻያ ረቂቅ አቅርቦ ማወያየት እንዲሁም የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ እና የፕሬዝዳንት ምርጫ አስመራጮችን የመምረጡና የመምረጫ ቀን የመወሰኑ ሶስት አበይት ጉዳዮች ገና ያልተጀመሩ በመሆናቸው በይደር ለነገው ዕለት እንደሚተላለፉ ይጠበቃል። 

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ጠቅላላ ጉባኤ ለሶስተኛ ጊዜ ከተደረገ የሻይ እረፍት በኋላ ከተሳታፊዎች እየቀረቡ ባሉ ጥያቄዎች ታጅቦ ቀጥሏል። 

ቀትር 10:30 – በኢንተርኮንቲነንታል ሆቴል እየተደረገ ያለው የ 10ኛው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ጉባኤ ከስራ አፈፃፀም ሂደት ጋር በተያያዘ የተነሱ የተለያዩ ጉዳዮችን የተመለከቱ ጥያቄዎች ከፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንቶችና ስራ አስፈፃሚዎች መልስ እያገኙ ይገኛል።

የጉባኤው ተሳታፊዎቹ የክልል ውክልና፣ የታዳጊዎች የእድሜ ልኬት (MRI)፣ የተጫዋች ፊርማና ግብር ስወራ፣ የፌደሬሽኑ የገቢ ማስገባት ጥረት፣ የኮፓ ኮካኮላና መሰል የታዳጊ ፕሮጀክቶች ስኬት እንዲሁም ሌሎች ጥያቄዎችን አቅርበዋል። ከመድረኩም ምላሽ እየተሰጠ ይገኛል።  

44% – በስራ አፈፃፀም ሪፖርቱ የፌደሬሽኑ ስራ አመራር በአራት አመታት ውስጥ 900,000 ሚሊዮን ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ ከእቅዱ ያሳካው 330,000 ሚሊዮን ብር ወይም የእቅዱን 44 በመቶ ብቻ ነው።

ቀትር 09:00 – 2009 በጀት አመት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ላይ ውይይት እንዲደረግበት ተጠይቆ የስራ አፈፃፀም ሪፖርቱን አባላቱ ከዚህ ቀደም የማንበብ እድል በማግኘታቸው ሪፖርቱ ድጋሚ ከሚነበብ ይልቅ በቀጥታ ተሳታፊዎቹ ያላቸውን ጥያቄና አስተያየት አቅርበው የማፅደቁ ሂደት እንዲከናወን በአንድ ተሳታፊ የቀረበው አስተያየት ተቀባይነት አግኝቶ አስተያየት እየተሰጠ ይገኛል። 

“… አንድ እናት ሽንኩርት ሸጣ ግብር ትከፍላለች … ተጫዋች ከውጪ አምጥተን ስራ ሰጥተን ግን ግብር ይሰወራል” – ከጉባኤው ተሳታፊዎች የተጫዋቾች ግብር ስወራን በተመለከተ የተሰጠ አስተያየት

ቀትር 08:50 – የ 10ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ከሻይ እረፍት መልስ ምርጫው እስኪካሄድ ጊዜያዊ የእግር ኳስ አስተዳዳሪ እንዲመረጥ በሚጠይቁ እና አሁን ያለው አካል እስከ ምርጫው ባለበት እንዲቀጥል በሚፈልጉ ድምፆች ታጅቦ ብዙም ሳይቆይ ለምሳ እረፍት ከተበተነበት ተመልሶ ውይይቱን ለመቀጠል የጉባኤው መሪ አቶ ጁነዲ ተሰብሳቢው ቦታ ቦታውን እንዲይዝ እየጠየቁ ነው። 

አቶ ጁነዲን የ 2009 በጀት አመት ቃለ ጉባኤን ለማፅደቅ ጥያቄ ወይም አስተያየት ያለው የጉባኤው ተሳታፊ አካል ካለ በሚል እየጠየቁ ነው። ነገርግን ጥያቄና አስተያየት ባለመኖሩ ቃለ ጉባኤው በአብላጫ ድምፅ እንዲፀድቅ ተደርጓል። 

ቀትር 06:50 – ጉባኤው ከሻይ እረፍት ተመልሶ ቀጣይ መርሀ ግብሮቹ ላይ ሊመክር በጉባኤው መሪ በጁነዲ ባሻ ንግግር ቀጥሏል። 

ነገርግን ከተሳታፊዎች መሀከል አሁን ያለው ስራ አስፈፃሚና ፕሬዝዳንት የስልጣን ጊዜውን በመጨረሱ እና የአዲስ ስራ አመራር ምርጫው በመራዘሙ ጊዜያዊ አመራር እንዲመረጥ እየተጠየቀ ይገኛል። 

ቀትር 06:20 – የስብሰባው መሪ አቶ ጁነዲ ምርጫ እንዲደረግ አፅንኦት በመስጠት የድምፅ ቆጣሪዎችን እየመረጡ ይገኛል። ነገርግን የመተረማመስ ሂደት በስብሰባው አዳራሽ ላይ ረቧል። 

በመጨረሻም “ምርጫው ለሌላ ጊዜ ይተላለፍ” የሚልና “ምርጫው ዛሬ ይካሄድ” በሚለው ላይ በተደረገ ምርጫ ከ 130 የጠቅላላ ጉባኤ አባላት 68 ያህል ድምፅ “ምርጫው ይራዘም” ሲሉ 62 ድምፅ ሰጪዎች በበኩላቸው ምርጫው ዛሬ ይካሄድ የሚለውን አማራጭ ወስደዋል።

በዚህም መሰረት ትንሽ አለመግባባት ቢኖርም የድምፅ ቆጠራው ፀድቆ የስራ አስፈፃሚና ፕሬዝዳንት ምርጫው ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ተወስኖ ስብሰባው ለሻይ እረፍት ተበትኗል።  

ቀትር 06:10 – ጉባኤው ከተሳታፊዎች አስተያየት በኋላ በፌደሬሽኑ የወቅቱ ፕሬዝዳንት ጁነዲ ባሻ ንግግር እንደቀጠለ ነው። 

“እጅ  መስጠት ወደሚለው ብንሄድ እመርጣለሁ” – አቶ ጁነዲ ባሻ 

ረፋድ 05:40 – አካሄድ በሚሉ ድምፆች ጉባኤው መጋጋል ይታይበታል። ለተሳታፊዎች የጥያቄ እድል በሚሰጥበት ወቅትም ብዙ እጆች እየታዩ ነው። 

ረፋድ 05:16 – በጉባኤው አጀንዳ ዙሪያ የሚሰጡ አስተያየቶች ጋል በረድ እያሉ ቀጥለዋል።

“የህዝቡን ቀልብ የገፈፈው የመገናኛ ብዙሀኑ ነው። … መንግስት በቀጥታም ባይሆን በተዘዋዋሪ እጁን አስገብቷል።”  – በጉባኤው ከተሰጡ አስተያየቶች መሀከል 

ረፋድ 05:00 – የዕለቱን አጀንዳ በተመለከተ የሚሰጡ አስተያየቶች በተጋጋለ መልኩ ቀጥለዋል።

“የኢትዮጵያውያን ፍላጎት እና የእግር ኳሱ እድገት አልተመጣጠነም …ሌላው አጀንዳ እንዳለ ሆኖ የስራ አስፈፃሚና የፕሬዝዳንትነት ምርጫው እንዲራዘም ..” – የስብሰባውን አጀንዳ በተመለከተ የተሰጠ ሌላ አስተያየት

ጠዋት 04:00 – የዕለቱ ቀዳሚ አጀንዳ የሆነው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የ 2009 በጀት አመት የስራ አፈፃፀም የተጀመረ ሲሆን ከመፅደቁ በፊት ግን ከተሳታፊዎች አስተያየት እየተሰጠ ሲሆን አስተያየት ከሰጡት አብዛኛዎቹም የምርጫው ሂደት በአንድ ወር ያህል እንዲራዘም እየጠየቁ ይገኛል።

“ይህ ጉባኤ ከአፋር ወደዚህ የተዘዋወረበት ምክንያት ግልፅ ስላልሆነ በዚህ ጉባኤ ይነገረን” – የአንድ የጉባኤው ተሳታፊ አስተያየት 

“ከግላዊ ምክንያት በስተቀር አጀንዳውን እንድናራዘም የሚያስገድድ ምክንያት ስለሌለ የመጣንበትን ፈፅመን መመለስ አለብን” – አንድ ሌላ የጉባኤው ተሳታፊ የሰጡት አስተያየት

ጠዋት 04:20 – የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ ንግግር እያደረጉ የሚገኝ ሲሆን በጉባኤ የተገኙትን አመስግነው በስልጣን ዘመናቸው በፌደሬሽን የተከናወኑ ብለው የሚያስቧቸውን አንኳር  ስራዎችን እያቀረቡ ይገኛል። 

ጠዋት 04:10 – ይህ ለመካሄድ ብቁ አይደለም ከመባል ጀምሮ ብዙ ንትርኮችን ያስነሳው የ 10ኛው የእግር ኳስ ፌደሬሽን መደበኛ ጉባኤ ለተፈጠረው መንጓተት ይቅርታ በመጠየቅ ባሳለፍነው የውድድር አመት በሞት ላጣናቸው የስፖርቱ አለም ሰዎች የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት ተደርጎ በይፋ ተጀምሯል። 

ጉባኤውን ለመጀመር በፌደሬሽኑ መተዳደሪያ ደንብ አንቀፅ 25(1) መሰረት ድምፅ የሚሰጡ አካላት ምላዕተ ጉባኤ መሟላት ስለነበረበት በተደረገ ቆጠራ ድምፅ ከሚሰጡ 142 አባላት 126 ያህሉ በጉባኤው መገኘት መቻላቸው በተደረገው ቆጠራ መታወቁ ተገልጿል። 

ጠዋት 04:00 – በዛሬው 10ኛ ጉባኤ የመጀመሪያ ዕለት ውሎ የሚኖሩ ዋነኛ ሂደቶችን ስንመለከት

1) የ 2009 በጀት አመት ቃለ ጉባኤ ይፀድቃል፣
2) የ 2009 በጀት አመት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ይቀርባል፣

3) የውጭ ኦዲተር ሪፖርት ይቀርባል፣

4) በቀረቡ ሪፖርቶች ላይ ውይይት ይካሄዳሉ፣

5) የ 2010 በጀት ዓመት እቅድ ቀርቦ ውይይት ይካሄዳል፣የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን መተዳደሪያ ደንብ ማሻሻል ረቂቅ ቀርቦ ውይይት ይካሄዳል።

ከዛም የአብላጫ ድምፅ ድጋፍ የሚገኝ ከሆነ በነገው ዕለት የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ እና የፕሬዝዳንት ምርጫ እንዲደረግ ቀጠሮ ተይዞ ጉባኤው የዛሬ ውሎውን እንደሚጠናቀቅ የወጣው መርሀ ግብር ያሳያል።

 

ጠዋት 03:25 – የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የበተነው የጉባኤው መርሀ ግብር የሚያሳይ በራሪ ወረቀት ከጠዋቱ 3:00 -3:30 ባለው ጊዜ ውስጥ የክብር እንግዳው ቦታቸውን ይዘው የአንኳን ደህና መጣችሁና የመግቢያ ንግግር እንደሚደረግ እንዲሁም የክብር እንግዳው መልዕክትና እንደሚኖር ቢገልፅም ተሳታፊዎች ገና ተሟልተው ወደስብሰባ ማዕከሉ አልገቡም።

ጠዋት 03:04 – ጉባኤው በሚደረግበት ቦታ ተሳታፊዎች፣ የክብር እንግዶች፣ የመገናኛ ብዙሀን እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው አካላት ወደ ስብሰባ አዳራሹ ለመግባት በዝግጅት ላይ ናቸው። 

Advertisements