ቀጥታ ስርጭት / የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን 10ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ የሁለተኛ ቀን ውሎ

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ወሳኝ እና አጨቃጫቂ ውሳኔዎችን ያሳልፍበታል ተብሎ ተጠብቆ የነበረው 10ኛው የመደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ በትናንትናው ዕለት በኢንተርኮንቲነንታል ሆቴል መጀመሩ ይታወቃል። የኢትዮአዲሱ ሚኪያስ በቀለም ጉባኤው ከሚደረግበት ኢንተርኮንቲነንታል የስብሰባ አዳራሽ ወሳኝ ሁነቶችንና የጉባኤውን ሂደቶች ሲያስመለከታችሁ መቆየቱ ይታወሳል። ዛሬም በሁለተኛው ቀን የጉባኤው ውሎ ሽፋን ለመስጠት በዛው ይገኛል። ቀትር 06:30 – በመጨረሻ የጉባኤው መሪ አቶ ጁነዲን የምርጫው ሂደት የሚካሄድበትን ክልል በተመለከተ ውሳኔው በተሳታፊዎች ድምፅ መሰረት እንዲሆን ባቀረቡት ሀሳብ መሰረት አብዛኛውን የጉባኤውን አባላቱን እና ሌሎች በጉባኤው የተገኙ አካላትን ባስደሰተ መልኩ በአፋር እንዲደረግ በአብላጫ ድምፅ (በሙሉ ድምፅ በሚባል መልኩ) ተወስኗል። 

የ 10ኛው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤም የምሳ መርሀ ግብር ከመቅረቱ ውጪ በዚህ መልክ ተደምድሟል። እኛም ከኢንተርኮንቲነንታል የነበረን የቀጥታ ስርጭትም በዚህ መልክ አጠናቀናል። 

ቀትር 06:15 – ጠቅላላ ጉባኤው የምርጫውን መደረጊያ ጊዜ በማስመልከት ባደረገው ጋል በረድ ያለ ክርክር በመድረክ መሪው አቶ ጁነዲ ባቀረቡት 45 ቀን ጊዜ ተስማምቶ ከ 45 ቀናት በኋላ እንዲደረግ ወስኗል። 

በሌላ በኩል የሚደረግበትን ቦታ በማስመልከት ከዚህ ቀደም የተመረጠው የአፋር ክልል ላይ አቶ ጁነዲን በሰጡት አስተያየት ፌደሬሽኑ ፍላጎት እንደነበረው ነገርግን ከተለያየ አካላት በመጣ ጫና ምክንያት ጉባኤው እዛ ሊደረግ ባለመቻሉ ለአፋር የይቅርታ ደብዳቤ መፃፋቸውን እና በፋክስ  መላካቸውን ተናግረዋል። 

በተያያዘ መልኩ ከጉባኤው ተሳታፊዎች አሁንም ምርጫው አፋር ክልል ይደረግ የሚል አስተያየት መምጣቱን አቶ ጁነዲን ተናግረው ነገርግን ለግማሽ ቀን ምርጫ ወደዛ ከመሄድ ይልቅ የሚቀጥለው አመት እዛ እንዲደረግ ሀሳብ እንዳለ ጨምረው አስረድተዋል። 

“.. በቂ ምክንያት አይደለም .. አፋር እኮ ኢትዮጵያ ውስጥ ናት.. አሁንም አፋር ክልል ይደረግ።” – የአፋር ተወካይ የምርጫው በአፋር ክልል አለመካሄድ ተብሎ የቀረበው ምክንያት ትክክል አለመሆኑን እና ነገሩ የፈጠረባቸውን ቁጭት ሲገልፁ

ረፋድ 05:55 – ጉባኤው የመተዳደሪያ ደንቡን በተመለከተ ማሻሻያ አቅርቦ ለማወያየት እና ለማሻሻል የያዘው መርሀ ግብር ከተሳታፊዎች እንዲራዘም በመጠየቁ በአብላጫ ድምፅ ለሌላ ጊዜ ተላልፏል።

“.. እኛም ደም ብዛታችን ይነሳል እኮ .. ምንድነው ይሄ ሁላ እጅ.. ” – የመድረክ መሪው አቶ ጁነዲ ባሻ ከመወያያ ርዕስ እየወጡ በአጀንዳነት ባልተያዙ ጉዳዮች ላይ አስተያየት ለሚሰጡና ያልተፈለገ ክርክር እያስነሱ ላሉ አካላት ጉባኤውን ባልተፈለጉ ጭቅጭቆች ከማንጓተት ይልቅ ተገቢ ውሳኔዎችን አሳልፎ በጊዜ መጨረስ እንደሚያስፈልግ አፅንኦት የሰጡበት ንግግር

የፌደሬሽኑ ተቀዳሚ ፕሬዝዳንት አቶ ተክለ ወይኒ ወደኋላ ተመልሰው የምርጫውን መራዘም የተመለከተ ንግግር በመጀመራቸው ከተሳታፊዎች ባልተያዘ አጀንዳ ላይ መወያየት አይፈቀድም በሚል የአካሄድ ጥያቄ ተነስቶቶባቸው ተቃውሞ እየቀረበባቸው ይገኛል። እሳቸው በሰጡት ምላሽ ደግሞ 2/3 ድምፅ ብልጫ ልዩነት ያስፈልግ ስለነበር የኔ ሀሳብ ይመዝገብልኝ በውሳኔው ላይ ግን ተቃውሞ የለኝም እያሉ ነው።

ከዚህ ጋር በተያያዘም በ 10ኛው መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ መርሀ ግብር መሰረት የሚቀረው ብቸኛ ነገር የአዲሱ ስራ አስፈፃሚዎችና ፕሬዝዳንቶች ምርጫ አፈፃፀምን በተመለከተ (አስመራጮች የሚካሄድበት ዕለትና የመሳሰሉት የምርጫ ሂደቶች) የሚደረግ ውይይትና ውሳኔ ብቻ ይሆናል።

ረፋድ 05:30 – ከሻይ እረፍት የተመለሰውና መሰላቸት አይነት ስሜት ውስጥ ያለው ጠቅላላ ጉባኤ በመድረክ መሪው ጥያቄ የ 2010 በጀት አመትን እቅድ በ 91 ድጋፍ እና በአምስት ድምፅተ አቅቦ አፅድቆ የዕለቱ ሌላኛው መርሀ ግብር ወደሆነው የፊደሬሽኑን መተዳደሪያ ደንብ ማሻሻያ እያመራ ይገኛል። 

የፌደሬሽኑን መተዳደሪያ ደንብ በተመለከተ እየተደረገ ባለ ውይይት እየተሰጡ ካሉ አስተያየቶች መሀከል የደንቡ ማሻሻያ ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ የሚጠይቅ ይገኝበታል።

ረፋድ 04:40 – የጠቅላላ ጉባኤው አባላት በ 2010 በጀት አመት እቅድ ዙሪያ ውይይት ካደረጉ በኋላ ውይይቱ ለሻይ እረፍት ተበትኗል። 

ጠዋት 03:40 – ህዳር 1፣ 2010 ማልዶ በወጣው ፀሀያማ የአዲስ አበባ አየር የታጀበው 10ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ምላዕተ ጉባኤው መሟላቱ ተረጋግጦ እንዲጀመር የጉባኤው መሪ የሆኑት አቶ ጁነዲ ባሻ በጠየቁት መሰረት በደረገ ቆጠራ ጉባኤው ካሉት 130 አባላት 108 አባላት በስብሰባው ላይ መገኘታቸው በመታወቁ ጉባኤው በ 2010 እቅድ ዙሪያ ተሳታፊዎች በሚሰጡት አስተያየት በይፋ የሁለተኛ ቀን ውሎውን ጀምሯል።

“.. የ10 አመት የሚባሉ እቅዶች መቼ ነው የሚቀሩት ..” – የፌደሬሽኑ የከዚህ ቀደም የ 10 አመት እቅድ አለመሳካቱን ተከትሎ አሁንም በድጋሚ በ 2010 ላይ መካተቱን በማስመልከት ከአንድ የጉባኤው ተሳታፊ የተሰጠ አስተያየት

ጠዋት 03:20 – ውድ የኢትዮአዲስ አንባቢያን እንደምን አደራችሁ መልካም ዕለተ አርብ እመኛለሁኝ። ዛሬም እንደ ትናንቱ ጋል በረድ የሚል ሽኩቻ ያረበበትን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን 10ኛ ጠቅላላ ጉባኤ የሁለተኛ ቀን ውሎ ወሳኝ ሂደቶች በቀጥታ የማስመለከታችሁ ይሆናል። ከዕናንተ የሚጠበቀው የዚህን ገፅ በአዲስ መልክ እየከፈቱ (refresh) አዳዲስ ሁነቶቸረን መከታተል ብቻ ነው።

Advertisements