“በአመቱ መጨረሻ ጫማዬን እሰቅላለሁ”- ዣቪ ሄርናንዴዝ


በእግር ኳስ ህይወቱ እጅግ አንፀባራቂ ስኬትን ያሳለፈው የመሃል ሜዳው ኮከብ ዣቪ ሄርናንዴዝ በያዝነው የውድድር አመት መጨረሻ ጫማውን እንደሚሰቅልና ወደአሰልጣኝነት ስራ የመግባት ፍላጎት እንዳለው ተናግሯል፡፡

በባርሴሎና ቤት እንዲሁም በስፔን ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ሁሉንም የቡድን ስኬቶች ያጣጣመው ጠቢቡ አማካይ እግር ኳስን እንደፈለጉ ሲያዙ የነበሩት እግሮቹ መዛላቸውንና ከዚህ አመት በኋላ ከፕሮፌሽናል እግር ኳስ እንደሚገለል አሳውቋል፡፡
ተጫዋቹ ሲናገር “ከጉዳት ርቄ መጫወት መቻሌ ዕድለኛ ያረገኛል ፤ የእግር ኳስ ህይወቴ አሁን ወደመገባደዱ ተቃርቧል፡፡ ከጊዜ ወደጊዜ እየተዳከምኩ እንደሆነ መረዳት በመቻሌ በአመቱ መጨረሻ ጫማ መስቀሌን በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ፡፡” ብሏል፡፡

በተጨማሪም ዣቪ ሲናገር “የፈቃድ ጉዳዮችን በማጠናቀቅ በቀጣዩ አመት የአሰልጣኝነት ስራን እጀምራለሁ” ሲል አጠቃሏል፡፡

የዓለም ዋንጫ ፣ የአውሮፓ ዋንጫን እንዲሁም የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግን ማንሳት የቻለው ዣቪ ባርሴሎናን ከለቀቀ በኋላ በኳታሩ ክለብ አልሳድ እየተጫወተ ይገኛል፡፡

 

Advertisements