“እግርኳስን የምትወድ ከሆነ ሊዮ ሜሲን መመልከት ትወዳለህ” – አርሴን ዌንገር

የአርሰናሉ አለቃ አርሰን ዌንገር አርጀንቲናን ለአለም ዋንጫ እንድትሳተፍ ትልቅ ሚና የተጫወተው ሊዮ ሜሲን  ሞቅ ባሉ ቃላቶች አሞካሽተውታል።

የ 2018 የአለም ዋንጫ ተሳትፎን ለማግኘት ከሁለት ሳምንት በፊት ኢኳዶርን የማሸነፍ ግዴታ ውስጥ ገብታ የነበረችው አርጀንቲና በውድ ልጇ ሊዮ ሜሲ ሶስት ጎሎች አሸናፊ በመሆን ወደ ራሺያ የሚወስዳትን ትኬት መቁረጥ ችላለች።

ከደቡብ አሜሪካም ብራዚልና እና ኡራጋይና ተከትላ ሶስተኛ ሆና ማጠናቀቅ ስትችል ኮልምቢያ አራተኛ ሆና ወደ ራሺያ ማቅናቷ ይታወሳል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ሊዮ ሜሲ ላደረገው አስተዋፅኦ አድናቆትን ከየአቅጣጫው የቀረበለት ሲሆን የአርጀንቲና እግርኳስ ማህበር ፕሬዝዳንት ሀቭየር ቴባስም በስሜት ተጫዋቹን አቅፈው ስቅስቅ ብለው ሲያለቅሱ ታይተዋል።

የቡድኑ ለአለም ዋንጫ ማለፍ የአርሰናሉ አሰልጣኝ አርሴን ዌንገር ጭምር አስደስቷል።ዌንገር ለሜሲ ያላቸውንም አድናቆት ሞቅ ባሉ ቃላት ገልፀዋል።

“በግሌ ሜሲን በአለም ዋንጫው ላይ ስለምንመለከተው ተደስቻለው።አርጄንቲና ለአለም ዋንጫ ባታልፍ እከፋ ነበር።እግርኳስን የምትወድ ከሆነ ሜሲን መመልከት ትወዳለህ።አርጀንቲናንም እንደዛው ትወዳለህ።” ሲሉ ተናግረዋል።

ዌንገር ጨምረው በደቡብ አሜሪካ ለአለም ዋንጫው ለማለፍ የሚደረገው ፉክክር እንደ አውሮፓ ቀላል አለመሆኑን ገልፀዋል።

“በደቡብ አሜሪካ ከ 10 ቡድኖች አራቱ ብቻ በቀጥታ ያልፋሉ።አምስተኛው ደግሞ ለጥሎማለፍ ጨዋታ ያልፋል።ለኔ በጣም ከባድ ውድድር ነው።በዛ ላይ የደቡብ አሜሪካ ቡድኖችን በቀላሉ አታሸንፋቸውም።” በማለት በደቡብ አሜሪካ የሚደረገው ውድድር ጠንካራ መሆኑን አሳውቀዋል።


Advertisements