ስኬት / ሴኔጋል ከ 2002 በኋላ አፍሪካን ወክላ ወደ አለም ዋንጫ መመለሷን አረጋገጠች

ሴኔጋል ደቡብ አፍሪካን በማሸነፍ ናይጄሪያ እና ግብፅን ተከትላ ለ 2018 የአለም ዋንጫ ያለፈች ሶስተኛዋ አፍሪካዊት ሀገር መሆኗል አረጋገጠች።

ትናንት ምሽት በፒተር ሞካባ ስታድየም የተደረገው የደቡብ አፍሪካ እና የሴኔጋል ተጠባቂ ጨዋታ በሴኔጋል 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ይህ ጨዋታ ባለፈው አመት ህዳር ወር ላይ ተካሂዶ በደቡብ አፍሪካ 2-1 አሸናፊነት ቢጠናቀቅም በጨዋታ ውጤት ማጭበርበር የእለቱ ዳኛ ጆሴፍ ላምፕቲ ላይ የቀረበው ክስ ተቀባይነት በማግኘቱ ዳኛውን ለቅጣት ዳርጎ ጨዋታው በድጋሚ እንዲካሄድ መወሰኑ ይታወሳል።

ትናንት ምሽት ላይም በተደረገው ጨዋታ ሴኔጋሎች በዌስትሀሙ ዲያፍራ ሳኮ ጎል ገና በ 12ኛው ደቂቃ መሪ መሆን ችለዋል።ለዚህ ጎል መቆጠር ደግሞ ድንቅ ኳስ በማሾለክ ትልቅ ሚና የተጫወተው የሊቨርፑሉ አጥቂ ሳዲዮ ማኔ ነበር።

ባለሜዳዎቹ በመጀመሪያው ግማሽ በኳስ ቁጥጥር ረገድ የተሻሉ ቢሆኑም ረጃጅሞቹን እና በአካል ብቃት ጠንካራ የነበሩት የሴኔጋል የተከለካይ ክፍልን መፈተን አልቻሉም።

ጥንቃቄ ላይ አመዝነው አልፎ አልፎ ሲያጠቁ አስፈሪ የነበሩት ሴኔጋሎች ሁለተኛውን ጎል የደቡብ አፍሪካው ታማሳንቃ ሚኪዜ በራሱ ጎል ላይ በማስቆጠሩ ጨዋታው 2-0 እንዲሆን አስችሎታል።

በሁለተኛው ግማሽ መጀመሪያ ላይ ጨዋታውን የግድ ማሸነፍ ይጠበቅባቸው የነበሩት ባፋና ባፋናዎቹ ተጭነው ቢጫወቱም ውጤቱን ለመቀልበስ ተቸግረው ተሸንፈው ወጥተዋል።

በውጤቱም ሴኔጋሎች ከ 2002 የኮሪያና ጃፓን ድንቅ የአለም ዋንጫ ተሳትፏቸው በኋላ በድጋሜ ወደ አለም ዋንጫው ለመመለስ ያስቻላቸው ሆኗል።

በ 2002 የአለም ዋንጫ ላይ ላይ ሴኔጋል ሳይታሰብ ፈረንሳይን ያሸነፈችበት ድንቅ እንቅስቃሴ እንዲሁም እስከ ሩብ ፍጻሜ የተጓዘችበት አጋጣሚ በወቅቱ የነበሩት የቡድኑ ተጫዋቾች ወደ አውሮፓ ክለቦች እንዲያቀኑ መንገድ የጠረገላቸው ነበር።

የአሁኑ የቡድኑ አሰልጣኝ አሊዩ ሲሴ

በወቅቱ ጠንካራውን ሴኔጋል በአምበልነት ይመራ የነበረው ደግሞ የአሁኑ የብሔራዊ ቡድኑ አምበል አሊዩ ሲሴ ነበር።ሲሴ ቡድኑን ከ16 አመታት በኋላ ዳግም ወደ አለም ዋንጫ በመመለሱ አድናቆት እየቀረበለት ይገኛል።

ወደ ራሺያ ማቅናታቸው የሚያረጋግጠው የመጨረሻ ፊሽካ ከተሰማም በኋላ ተጫዋቾቹ በደስታ ሲደንሱ ታይተዋል።ይህን ሲመራ የነበረው ደግሞ ግብ ጠባቂው ኒዲያዬ ነበር።

ግብ ጠባቂው ኒዲያዬ

ሁለቱ አገሮች የምድባቸውን የመጨረሻ ጨዋታ ማክሰኞ የሚያደርጉ ቢሆንም ሴኔጋል ማለፏን በማረጋገጧ ጨዋታው መርሀግብር ከማሟላት ውጪ ያለፈ ትርጉም አይኖረውም።

እስካሁን ድረስ አፍሪካን መወከላቸውን ያረጋገጡት ናይጄሪያ፣ግብፅ እና ሴኔጋል ሲሆኑ ቀሪዎቹ ሁለት ቡድኖች በመጨረሻዎቹ የምድብ ማጣሪያ ውጤቶች የሚየሚለዩ ይሆናል።

Advertisements