ዋልያው በቻን ማጣሪያ የመልስ ጨዋታ ከሩዋንዳ ጋር ኪጋሊ ላይ ይጫወታል

Walias-vs-Zambia

ዳግም በቻን የማለፍ ተስፋን በካፍ ያገኘው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከሩዋንዳ ሽንፈት መልስ በሳምንቱ መጨረሻ የመልሱን ጨዋታ ለማድረግ ወደ ኪጋሊ አቅንቷል፡፡ በፌዴሬሽኑ ሀላፊዎች ትኩረት የተነፈገው ብሄራዊ ቡድኑ እንደት ሰነበትክ ያለው አካል ያልነበረ ሲሆን አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለም ጉዳይ አስፈጻሚ ሆነው ሳምነቱን አሳልፈዋል፡፡

ከፓስፖርት ጋር በተያያዘ የብሄራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች ፓስፖርታቸው የመታደሻ ጊዜ ማለፉን ተከትሎ ኢሚግሬሽን የሰነበቱት የብሄራዊ ቡድኑ አለቃ አሸናፊ በቀለ በዚህ ምክንያት ብሄራዊ ቡድኑን በተገቢው መልኩ አለማዘጋጀታቸው ተነግሯል፡፡ ሆኖም ግን በመጨረሻም ነገሮች ቀና ሆነው ዋልያው በሳምንቱ መጨረሻ ወደ ኪጋሊ  ያቀና ሲሆን ትላንት ማምሻውንም ልምምዱን ሰርቷል፡፡

18 ተጫዋቾችን ወደ ኪጋሊ ይዞ የሄደው ብሄራዊ ቡድኑ አስቻለው ግርማን በጉዳት ምክንያት እንዳጣ ቢነገርም የኢትዮጵያ ቡናውን የመስመር ተጫዋች አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ሀላፊነት ወስደው ወደ ኪጋሊ ይዘውት አቅንተዋል፡፡ በፓስፖርት ችግር ከኪጋሊ ይቀራል ተብሎ የነበረው ግርማ በቀለም ችግሩ ተፈትቶ ወደ ስፍራው ሲያቀና ታሪክ ጌትነት የፓስፖርቱን ጉዳይ አለመቋጨቱን ተከትሎ ከዋልያው ጋር ወደ ሩዋንዳ ሳይጓዝ ቀርቷል፡፡

ብሄራዊ ቡድኑ ወደ ለ2018 የሞሮኮ የቻን አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በሜዳው የደረሰበትን የ3-2 ሽንፈት መቀልበስ የሚጠበቅበት ሰሆን ከ2 እና ከዚያ በላይ ግቦችን አስቆጥሮ ማሸነፍ ደግሞ ለማለፍ ቁልፉ መሳሪያ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ  ቡድን ከሩዋንዳ አቻው ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ነገ (እሁድ) በ10 ሰዓት ይደረጋል፡፡

Advertisements