ፍቺ / ኦሎምፒክ ዲ ማርሴ ከፓትሪክ ኤቭራ ጋር የነበረውን ኮንትራት መቅደዱን አሳወቀ

የፈረንሳዩ ኦሎምፒክ ዲ ማርሴይ ከክለቡ ተጫዋች ከነበረው የ 36 አመቱ የግራ መስመር ተከላካይ ፓትሪክ ኤቭራ ጋር የነበረውን ኮንትራት መቅደዱን ሲያሳውቅ የአውሮፓ እግርኳስ ማህበርም ተጫዋቹ ላይ ቅጣት አስተላልፏል።

የቀድሞ የሞናኮ፣ የማንችስተር ዩናይትድና ጁቬንቱስ የግራ መስመር ተከላካይ የነበረው ፓትሪክ ኤቭራ ከማርሴ ጋር የነበረው ቆይታ በአስገራሚ ሁኔታ ተቋጭቷል።

ተጫዋቹ ባለፈው ሳምንት በዩሮፓ ሊግ ጨዋታ ቪቶሪያ ዲ ጉሜይሬዝን ለመግጠም ወደ ፓርቹጋል ከቡድኑ ጋር አቅንቶ ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ ወደ ማስታወቂያ ቦርዱ ተጠግቶ አንድ የማርሴ ደጋፊን ግራ እግሩን አንስቶ ፊቱን ከረገጠው በኋላ ከሜዳ በቀይ በመውጣቱ በድርጊቱ መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቷል።

የብዙዎቹ ጥያቄ ትላልቅ ቡድኖችን በአምበልነት መምራት የቻለው እና የብዙ አመት ልምድ ባለቤት የሆነው ፓትሪክ ኤቭራ የጨዋታ ዘመኑ ለማጠናቀቅ በተቃረበነት ወቅት የረጅም አመት የእግርኳስ ህይወቱን ጥላሸት የሚያለብስ ተግባር እንዴት ሊፈፅም ቻለ?እንዴትስ በትዕግስት ሊያልፈው አልቻለም? የሚለው ነበር።

ክለቡ ማርሴ ወዲያውኑ ጉዳዩ ተጣርቶ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ ከክለቡ ጋር ልምምድ እንዳያደርግ ሲያግደው የአውሮፓ እግር ኳስ ማሀረበርም ለጊዜም የመጀመሪያ ደረጃ ቅጣት በሚል የአንድ ጨዋታ ቅጣት አስተላልፎበት ነበር።

አሁን ግን ማርሴ ጉዳዩን በጥልቀት ከመረመረ በኋላ ከተጫዋቹ ጋር ያለውን ኮንትራት በጋራ ስምምነት መቅደዳቸውን በማሳወቁ የክለቡና የተጫዋቹ ግኑኝነት አብቅቷል።የአውሮፓ እግርኳስ ማህበርም በበኩሉ እስከ ሰኔ 30/2018 የሚደረጉ ማንኛውም የአውሮፓ የክለብ ጨዋታዎች መሳተፍ እንደማይችል ሲያሳውቅ የ 10 ሺ ዩሮ ቅጣትም ማስተላለፉን አሳውቋል።

የክለቡ መግለጫ ሲነበብ “ኦሎምፒክ ዲ ማርሴ እና ፓትሪክ ኤቭራ በጋራ ስምምነት ግኑኝነታቸውን እንዲያጠናቅቁ ወስነዋል።የተጫዋቹም ኮንትራት በይፋ ተቀዷል።

“ከጥር 2017 ጀምሮ ፓትሪክ ኤቭራ ከቡድኑ ጋር በሜዳ እና በመልበሻ ቤት ውስጥ ነበር።ክለቡም በውጤቱ እንዲያገግም፣እንዲሻሻል፣መነቃቃት በመፍጠር ትልቅ ሚና ተጫውቷል።

“ባለፈው ህዳር 2 በጉይማሬዝ በአንድ ደጋፊ ላይ የማይገባ የስነ ምግባር ጉድለት አሳይቷል።ስለዚህ በአቋሙ እና የኋላ ታሪኩን መሰረት በማድረግ ሳይሆን ይህ ያልተገባ ድርጊት ከአንድ ልምድ ያለው ተጫዋች የማይጠበቅ በመሆኑ፣ በሜዳና ከሜዳ ውጪ የሚያሳየው ባህሪ ለወጣቶች አርአያ መሆን ስለሚገባው ተጫዋቹ ከክለቡ ጋር የነበረው ኮንትራት በስምምነት ተቀዷል።” በማለት ክለቡ አሳውቋል።

“በዚህ መሰረት ሁኔታዎች ለኤቭራ ከክለባችን ጋር እቅዱን ለማሳካት ምቹ ስለማይሆኑ በጋራ ስምምነት ኮንትራታችን ቀደናል።” ሲል ክለቡ በመግለጫው ላይ አሳውቋል።

1995 ላይ ኤሪክ ካንቶና በተመሳሳይ ጥፋት ማቲው ሲሞንስ የተባለውም የክሪስታል ፓላስ ደጋፊን በኩንጉፉ በመማታቱ የአውሮፓ እግርኳስ ማህበር ለስምንት ወራት ቅጣት አስተላልፎበት እንደነበር ይታወሳል።

Advertisements