ሞሮኮ እና ቱኒዚያ አፍሪካን ወክለው ወደ አለም ዋንጫ የሚያቀኑ አራተኛ እና አምስተኛ አገሮች ሆኑ

ሞሮኮ እና ቱኒዚያ በቀጣይ ሰኔ ወር ላይ ለሚጀመረው የ 2018 የራሺያ የአለም ዋንጫ አፍሪካን የሚወክሉት አራተኛ እና አምስተኛ አገር መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የሰሜን አፍሪካ አገራት የእግርኳስ የበላይነታቸው በክለብም ይሁን በብሔራዊ ቡድን በደንብ የበላይነታቸውን ያሳዩበት አመት ይኸው 2017 አመት ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።

ባለፈው ሳምንት ፍጻሜውን ያገኘው የ 2017 የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታ ላይ የተገናኙት ሁለቱ የሰሜን አፍሪካ ፈርጦች የሞሮኮው ዊዳድ ካዛብላንካ እና የግብፁ አል አህሊ ነበሩ።

እልህ አስጨራሽ ፍልሚያ በተደረገበት ጨዋታ የሞሮኮው ዊዳድ ካዛብላንካ በአጠቃላይ ውጤት አህሊን 2-1 በማሸነፍ የ2017 የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ዋንጫ በማንሳት የአፍሪካ የክለቦች የበላይነት ሚዛን በሰሜን አፍሪካ ቡድኖች ቁጥጥር ስር መውደቁን ያረጋገጠ ነበር።

በብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎችም እንዲሁ ለ2018 የአለም ዋንጫ ለማለፍ ሲደረግ የነበረው ውድድር በበላይነት ማጠናቀቅ የቻሉት የሰሜን አፍሪካ አገሮች ናቸው።

አፍሪካ በአለም ዋንጫ ተሳትፎ ከተሰጣት አምስት ኮታዎች ውስጥ በ 2018 የራሺያ የአለም ዋንጫ ላይ ሶስት[ግብፅ፣ሞሮኮ እና ቱኒዚያ] የሰሜን አፍሪካ ቡድኖች ማለፉቸውን ሲያረጋግጡ ምዕራብ አፍሪካ በሁለት አገራት [ናይጄሪያ እና ሴኔጋል] ትወከላለች።

ትናንት ምሽት አፍሪካን የሚወክሉ የመጨረሻ ሁለት አገራትን ለመለየት በተደረገው ጨዋታ ሞሮኮ እና ቱኒዚያ ተጋጣሚያቸው የነበሩት አይቮሪኮስትና ሊቢያን በማሸነፍ እና አቻ በመውጣት ወደ አለም ዋንጫው የሚያስኬዳቸውን ቲኬት መቁረጥ ችለዋል።

በተለይ ሞሮኮ እጅግ ወሳኙን ጨዋታ ወደ አይቮሪኮስት አቢጃን አቅንታ 2-0 በማሸነፍ ጣፋጭ ድል አስመዝግባለች።አቻ በቂዋ የነበረው ሞሮኮ ናቢል ዲራር እና መሀዲ ቤናሺያ ያስቆጠሯቸው ጎሎች ሙሉ ሶስት ነጥብ በማሳካት ምድቧን በበላይነት አጠናቃለች።

አፍሪካን በአለም ዋንጫ የሚወክሉት አገሮች የት ይገኛሉ?

ማሸነፍ ብቻ ወደ አለም ዋንጫው ይወስዳት የነበረችው በማርክ ዊልሞትስ የምትሰለጥነው አይቮሪኮስት ጨዋታውን በሜዳዋ በማድረጓ ልታሳካው የምትችለው ጨዋታ ቢመስልም አልቀመስ ያሉት ሞሮኮዎችን በሜዳቸው ማንበርከክ ከብዷቸው ታይቷል።

የግብ ጠባቂው ሲልቬን ጉቦህዎ ሁለት ስህተቶች አይቮሪኮስት ለአራተኛ ተከተታይ ጊዜ በአለም ዋንጫ ላይ እንዳትሳተፍ እንቅፋት ከሆነባት እና ምሽቱ ለባለሜዳዎቹ ጨለማ እንዲሆን ከተጠቃሽ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ነበር።

በምድብ ጨዋታው ምንም ጎል ያላስተናገዱት ሞሮኮዎች ምን ያህል ጠንካራ የተከላካይ ተጫዋቾች እንዳላት ማሳየት ስትችል፤በተቃራኒው 12 ጎሎችን በተቃራኒ መረብ ላይ በማሳረፍ ወደ አለም ዋንጫ እንድትመለስ ጉልህ አስተዋፅኦ አድርጎላታል።

1998 ላይ እነ ሙስጠፋ ሀጂ፣ኑረዲን ናይቤት እና ዮሱፍ ቺፓን ይዛ በፈረንሳዩ የአለም ዋንጫ ከተሳተፈች በኋላ ላለፉት ድፍን 20 አመታት ወደ ታላቁ መድረክ ድርሽ ያላለችው “የአትላስ አናብስቶቹ”ሞሮኮ አሁን በአዲስ ትውልዷ ወደ አለም ዋንጫው ለመመለስ ችላለች።

የሞሮኮው ዊዳድ ካዛብላንካ የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግን ዋንጫ ካነሳ ከሳምንት በኋላ በድጋሚ በብሔራዊ ቡድናቸው ውጤታማ የሆኑት ሞሮኮዎቹ ሳምንቱ ያማረ 2017 ደግሞ የስኬት አመት ሆኖላቸዋል።

በስድስት አውሮፕላኖች እስከ 3500 የሚደርሱ የሞሮኮ ደጋፊዎች ወደ አቢጃን ቡድናቸውን ለመደገፍ አቅንተው የነበረ ሲሆን በቡድናቸው ውጤት በደስታ ፈንጥዘዋል።

በስኬት የተሽቆጠቆጠ የአሰልጣኝነት ህይወት እያሳለፉ የሚገኙት ሄርቬ ሬናልድ

የቡድኑ አሰልጣኝ ሄርቬ ሬናልድም ያሸበረቀ የአሰልጣኝነት ህይወታቸውን ቀጥለዋል።አሰልጣኙ 2012 ላይ ከዛምቢያ ጋር የአፍሪካ ዋንጫ፣2015 ላይ ከ አይሾሪኮስት ጋር የአፍሪካ ዋንጫ ካሳኩ በኋላ አሁን ደግሞ ሞሮኮን ይዘው ወደ አለም ዋንጫ ማቅናት ችሏል።

እንደ ኤስፔራንስ እና ሴፋክሲያን አይነት የጠንካራ ቡድን ባለቤት የሆነችው ቱኒዚያም ክለቦቿ ምንም እንኳን ዘንድሮ ለዋንጫ ባይታደሉም እስከ ግማሽ ፍጻሜ ደረስ በመጓዝ ጥንካሬያቸውን አሳይተዋል።

ከኢትዮጵያዊ ቅ/ጊዮርጊስ ጋር በአንድ ምድብ ተደልድሎ የነበረው ኤስፔራንስ ደ ቱኒዝ ከምድብ ማጣሪያው ብዙም ሳይቸገር ወደ ፊት መጓዝ ቢችልም በግማሽ ፍጻሜው በሌላ የሰሜን አፍሪካ ቡድን ተሸንፎ ለፍጻሜ ሳይበቃ ቀርቷል።

ነገርግን ቡድኑ ምን ያህል ጠንካራ ተጨዋቾች እና አደረጃጀት እንዳለው እዚሁ መጥተው ቅ/ጊዮርጊስን ሲገጥሙ መታዘብ ተችሏል።የ 2017 የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ኮከብ ጎል አስቆጣሪነት ከኢትዮጵያዉ ሳል ሀዲን ሰኢድ ጋር የተጋራውም የኤስፔራንሱ ጠሀ ያሲን ኬኒሲ እንደነበር ይታወሳል።

ቱኒዚያ በብሔራዊ ቡድኗም ስኬታማ አመት ላይ ትገኛለች።ወደ ራሺያ ለማምራት  አቻ በቂዋ የነበረ ሲሆን ከጎረቤቷ ሊቢያ ጋር በሜዳዋ ያደረገችው የምሽቱን ጨዋታ የፈለገችውን አንድ ነጥብ በማሳካት ሌላኛዋ አፍሪካን የምትወክል አገር ሆናለች።

በአለም ዋንጫው ላይ አፍሪካን የሚወክሉ አምስቱ አገሮች

ቱኒዚያ ከ1998 እስከ 2006 በሶስት ተከታታይ የአለም ዋንጫ ላይ ከተሳተፈች በኋላ ወደ አለም ዋንጫው ስትመለስ ለመጀመሪያ ጊዜዋ ሆኗል።

2014 በብራዚል የአለም ዋንጫ ላይ አፍሪካን ወክለው የነበሩት ጋና፣አይቮሪኮስት፣አልጄሪያ እና ካሜሮን የነበሩ ሲሆን ከነዚህ አገራት ውስጥ በ 2018 የአለም ዋንጫ ላይ አንዳቸው ተሳታፊ አይሆኑም።

በምትካቸው ሞሮኮ እና ቱኒዚያ ቀደም ብለው ካለፉት ናይጄሪያ፣ግብፅ እና ሴኔጋል ጋር በመሆን አፍሪካን በመወከል በራሺያው የአለም ዋንጫ ላይ ተሳታፊ ይሆናሉ።

Advertisements