ስምንተኛው የ”አዝናኑ ሲዝናና” የሚዲያ የፉትሳል ውድድር የምድብ ድልድል ይፋ ሆነ

ለስምንተኛ ጊዜ የሚካሄደውና “አዝናኙ ሲዝናና” የሚል ስያሜን የያዘው የሚድያ አካላት የፉትሳል ውድድር የምድብ ዕጣ አወጣጥ ስነስርአት ትናንት አመሻሹን ሲከናወን ኢትዮአዲስ ስፖርት በምድብ “ሐ” ከኢቢኤስ ቲቪ ፣ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ፣ ከኢትዮ ሲኒማና ከኢትዮጵያን ስፖርት ጋር ተደልድላለች፡፡

የዕጣ አወጣጥ ስነስርአቱ ታዋቂ ኢትዮጵያውያን እንግዶች በተገኙበት በማሪዮት ኤክስኪዩቲቭ ሆቴል የተደረገ ሲሆን ከሚዲያ አካላት ውድድር በተጨማሪ ለሁለተኛ ጊዜ የሚካሄደው የሆቴሎች የእግር ኳስ ሻምፒዮና የምድብ ድልድል ተደርጎበታል፡፡

በዘንድሮው አመት የተወዳዳሪ ቡድኖችን መጠን ወደ 20 ከፍ ያደረገው የሚዲያ ውድድሩ እያንዳንዳቸው አምስት ቡድኖችን የያዙ አራት ምድቦች ያሉት ሲሆን በምድብ “ሀ” ኢትዮፒካሊንክ ፣ ኢ ኤን ኤን ቲቪ ፣ ቃና ቲቪ ፣ ክላሲክ ስፖርትና ሪፖርተር ጋዜጣ ሲደለደሉ በምድብ “ለ” ደግሞ ላይፍ ኢስ ጉድ(Life is good) የሬዲዮ ፕሮግራም ፣ የኔታ ቲዩብ ፣ ሄሎ ኢትዮጵያ ፣ ሶከር ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ዲጂዎች ማህበር ተደልድለዋል፡፡

ኢትዮ አዲስ ስፖርት በተካተተችበት ምድብ “ሐ” ኢቢኤስ ቲቪ ፣ኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ፣ ኢትዮጵያ ስፖርትና ኢትዮ ሲኒማ ተደልድለው ሲጫወቱ በመጨረሻው ምድብ ልዩ አቦል ፣ ፋና ፣አዲስ ቲቪ ፣ዋልታ ኢንፎርሜሽን እና አዲስ ጣህም ተደልድለዋል፡፡

ውድድሩ የፊታችን ቅዳሜ በምድብ “ሀ” ጨዋታዎች ይከፈታል፡፡

Advertisements