ዥሩ ከአርሴናል ጋር ያለው ታሪክ አለመጠናቀቁን ገለፀ

የአርሰናሉ አጥቂ ኦሊቪየ ዥሩ በፕሪሚየር ሊጉ ክለብ ለመቆየት ውሳኔ ላይ በመድረሱ ጉዳይ ፀፀት እንደማይሰማው ገልፅዋል።

የ31 ዓመቱ ተጫዋች በውድድሩ መጨረሻ ከክለቡ ይለቃል በሚል ስሙ ከበርከታ ክለቦች ጋር ተያይዞ ቢቆይም፣ ተጫዋቹ ግን በአርሰናል ለመቆየት ወስኗል።

ነገር ግን ፈረንሳያዊው ተጫዋች በዚህ የውድድር ዘመን በፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ ተሰላፊ ሆኖ መጫወት አልቻለም። ከተቀያሪ ወንበር ላይ በመነሳት ተሰልፎ መጫወት በቻለባቸው 10 ጨዋታዎችም ማስቆጠር የቻለው አንድ ግብ ብቻ ነው።

አርብ ምሽት ሀገሩ ፈረንሳይ ከዌልስ ጋር ባደረገችው የወዳጅነት ጨዋታ 2ለ0 ስታሸንፍ ግብ ማስቆጠር የቻለው ዥሩ በኤመራትስ ለመቆየት በመወሰኑ ደስተኛ መሆኑን ገልፅዋል።

“አሁን ስለወደፊቱ እራሴን የምጠይቅበት ጊዜ አይደለም።” ሲል ለእንግሊዝ ጋዜጦች ተናግሯል።

“በአርሰናል ደስተኛ ነኝ። ለመቆየት ስል በደረስኩት ውሰኔም ደስተኛ ነኝ። ምክኒያቱም [መቆየት] እፈልግ ነበር። በክለቡ እና በእኔ መካከል ያለው ታሪክ ገና እንዳልተቋጨና እንዳላበቃ እያሰብኩ አገኛለሁ።

“በብቃቴ ላይ እምነት እያሳደርኩኝ እና በእምነቴም እየቀጠልኩም እገኛለሁ። ከአርሰናልና ከሃገሬ ጋር በርካታ አላማዎች አሉኝ። ለዚህ ሁልጊዜም ወደፊት እየሄድኩ ግብ ማስቆጠሬን እቀጥላለሁ።”

ዥሩ በዩሮፓ ሊግ የመጀመሪያ ተሰላፊ መሆን በቻለባቸው ሁለት ጨዋታዎች ላይ ሁለት ግቦችን ማስቆጠር ቢችልም በክለቡ በቆየባቸው እያንዳንዱ የውድድር ዘመኖች ያስቆጠራቸው ግቦች ከ10 ያነሱ መሆናቸው ከክለቡ ጋር የሚኖረውን ቆይታ እንዲያበቃ ሊያደረገው ይችላል።

ይሁን እንጂ አጥቂው በአርሰን ቬንገር ላይ እምነት እንዳለው እና ለዚህ እምነታቸውም ለአሰልጣኙ የሚገባቸውን ምላሽ የመስጠት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው ገልፅዋል።

“አርሰን ሁልጊዜም ይደግፈኛል። በመካከላችንም ከፍ ያለ መተማመን አለ።” ሲል ዥሩ ተናግሯል።

“እሱ በእኔ እምነት አለው። በምላሹም በተቻለኝ አቅም በሜዳ ላይ ላሳየው እጥራለሁ።”

Advertisements