የውጤት መንገዱ የጠፋበት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተመሳሳይ ጉዞን ቀጥሏል

Related image

ዋልያው የቀደመ ስምና ዝናውን ካጣ ከራርሟል። በ2013 የአፍሪካ ዋንጫ የ2014 የብራዚል የአለም ዋንጫ የመጨረሻ ማጣሪያ ምርጥ 10 እንዲሁም ለ2015 የቻን አፍሪካ ዋንጫ ማለፍ ችሎ የነበረው ብሄራዊ ቡድኑ አሁን ባለንበት አመት የውጤት መንገዱ ጠፍቶት በተደጋጋሚ ከተካፈለበት የየቻን የአፍሪካ ዋንጫ እንኳ ማለፍ ተስኖታል፡፡

በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሸማቃቂ የሚባሉ ሽንፈቶችን እያስተናገደ መጓዙን የቀጠለ ሲሆን አሰልጣኙ ብሄራዊ ቡድኑን ከያዙ አንስቶ እስካሁን ካደረጓቸው ዘጠኝ ጨዋታዎች መካከል ድል ማድረግ የቻሉት በአንዱ ብቻ ነው፡፡ ድሉም የተገኘው በእግር ኳስ ስሟ እምብዛም በይነሳው ጅቡቲ ሲሆን በተቀሩት ጨዋታዎች አቻ እና ሽንፈት ደርሶበታል፡፡

በ10ኛው መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ መጥመድ ምክንያት ብሄራዊ ቡድኑን ትኩረት ያልሰጠው የሚመስለው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋልያውን ወደኪጋሊ የሸኘው ሲሆን፣ ብሄራዊ ቡድኑም ከሩዋንዳ አቻው ጋር ባደረገው ጨዋታ 0-0 በሆነ አቻ ውጤት ማጠናቀቁን ተከትሎ የቻን ተሳትፎ ህልሙ መና የቀረ ሲሆን ለሁለት ተከታታይ ጊዜያት ማለፍ ከቻለበት መድረክም መቅረቱን አረጋግጧል፡፡

ከጥቂት አመታት በፊት በርካቶችን ከጨዋታው 24 ሰዓታት በፊት በስቴዲየም ያሳድር የነበረው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከውጤት መጥፋት ጋር በተያያዘ ብዙኃን የእግር ኳስ አፍቃሪያን ማስከፋቱን የቀጠለ ሲሆን በሽንፈቶች ከመበሳጨት ይልቅም የብሄራዊ ቡድኑ ውጤት ሲሰማ ውጤቱን ወደ ቀልድ በመቀየር  ዋልያውን መዛበቻ ማድረግ እየተደጋገመ የመጣ ይመስላል፡፡

ከውጤት ቀውስ እና ከፌዴሬሽኑ ኃላፊዎች ጣልቃ ገብነት ምክንያት በተደጋጋሚ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የልቀቁኝ ጥያቄን ያቀረቡት የብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ አቶ አሸናፊ በቀለ ዋልያውን ባሳለፍነው አመት ሲረከቡ በ2019 የአፍሪካ ዋንጫ የማለፍ እና በውድድሩም እስከ ሩብ ፍጻሜው የመጓዝ ሩቅ ህልምን ይዘው ወደ መንበሩ ብቅ ቢሉም ከወዲሁ በውዝግብ የተሙሉ ወራትን እያሳለፉ ይገኛሉ፡፡

ከዚህ ቀደም ለብሄራዊ ቡድኑ ውጤት ማጣት ግብ ጠባቂውን እና ያረፉበትን ሆቴል ተጠያቂ እስከማድረግ የደረሱት የብሄራዊ ቡድኑ አለቃ ባሳለፍነው እሁድ ብሄራዊ ቡድኑ በሩዋንዳ አቻው ሽንፈት ሲደርስበት ለሽንፈቱ ኃላፊነቱን እንደሚወስዱ በመግለፅ ትችትን ፍራቻ በሚመስል መልኩ  ያልተለመደ አስተያየት እና አጥጋቢ ያልሆነ ምላሽ ለጋዜጠኞች ሰጥተዋል።

ብሄራዊ ቡድኑ 3ለ2 በሆነ ውጤት በሩዋንዳ አቻው ሲሸነፍም የቅዱስ ጊዮርጊሱን ግብ ጠባቂ ለአለም ብርሀኑ ሁለት ስህተቶችን መስራቱን ተከትሎ  ከዛሬ አመሻሽ ጨዋታ ውጪ ያደረጉ ሲሆን ከጨዋታው መገባደድ በኋላም በውጤቱ የተከፉ የመሰሉት አሸናፊ በቀለ ቃላቸውን ለመስማት አቆብቁበው የነበረሩትን ጋዜጠኞች ችላ ብለው ወደ መልበሻ ክፍል ተመልሰዋል፡፡

ብሄራዊ ቡድኑ በወርሃ መጋቢት  በአዲስ አበባ ስቴዲየም በ2019 የካሜሮን አፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ የምድቡን ሁለተኛ ጨዋታ ከሴራሊዮን ጋር የሚያደርግ ሲሆን ከወዲሁም ለዚሀ ጨዋታ ትኩረት ሰጥቶ ካልተዘጋጀ ሁለት ሀገራት ከምድቡ በሚልፉበት የዘንድሮ የማጣሪያ መርሀ ግብር ልክ እንደ ቻን እና መሰል ውድድሮች ከታላቁ የአፍሪካ መድረክ መቅረቱ አይቀሬ ይመስላል፡፡