“ሀቲም ቤን አርፋ በተሰጥኦ ከሜሲ ጋር እኩል ነው” – ካሪም ቤንዜማ

የሪያል ማድሪዱ የፊት መስመር ተሰላፊ ካሪም ቤንዜማ ለኒዮኔል መሲ ትክክለኛ የተሰጥኦ ተፎካካሪ ሊሆነው የሚችለው ተጫዋች ሀቲም ቤን አርፋ መሆኑን ገልጿል። 

የ 29 አመቱ የሎስብላንኮስ ተጫዋች ሳይጠበቅ በሰጠው በዚህ የማወዳደሪያ ቃለመጠይቁ የብሔራዊ ቡድን አጋሩ የሆነው ቤን አርፋ ከምንግዜዎቹም የእግር ኳስ ኮከቦች ጋር ስሙ ከሚነሳውና ለአምስት ጊዜያት የባለንዶር አሸናፊ ከሆነው ሜሲ ጋር ተመጣጣኝ ተሰጥኦ እንዳለው ተናግሮ ብዙዎችን አስገርሟል።

የፒኤስጂው የክንፍ ተጫዋች ቤን አርፋ ለአራት አመታት ወሳኝ ሚናን ከተጫወተበት የፕሪምየር ሊጉ ክለብ ኒውካስትል ለቆ ለሀገሩ ክለብ ኒስ ተጫውቶ በ 2016 ፒኤስጂ ከመጣ ወዲህ 13 ጨዋታዎችን ብቻ ያደረገ ሲሆን ብቃቱን መልሶ ለማግኘትም በጥረት ላይ ነው።

ነገርግን ይህ የቤን አርፋ ዝቅታ ከቅርብ አመታት ወዲህ በፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን አብሮት የተጫወተው ቤንዜማ ለሚረር ጋዜጣ “ቤን አርፋ ከሜሲ ጋር የሚመጣጠን ተሰጥኦ አለው። አሁን በፒኤስጂ ያለውን ሁኔታ መመልከት ይጎዳኛል” በማለት ምስክርነቱን ከመስጠት አላገደውም። 

ባሳለፍነው ሀምሌ ከክለቡ የቅድመ ውድድር ዝግጅት ውጪ ተደርጎ የነበረው ቤን አርፋ የእግር ኳስ ህይወቱን በፈረንሳዩ ኒስ የገነባ ሲሆን 2016 ሀምሌ ወደፒኤስጂ ከማምራቱ በፊትም በአንድ የውድድር ዘመን 18 ግቦችን ማስቆጠር መቻሉ አይረሳም። 

ቤን አርፋ ወደ ፓሪሱ ክለብ ከመጣ ወዲህ ግን ኑሮ በኡናይ ኤምሪ ስር ከብዶት የሚገኝ ሲሆን ያለውን የበዛ ብቃትም ማውጣት በተሳነው በዚህ ሰአትም የቤንዜማን አድናቆት ማግኘት መቻሉ አነጋጋሪ ሆኗል።

ምልከታ : ውድ አንባቢያን በቤንዜማ አስተያየት ዙሪያ ያልዎት ሀሳብ ምን ይመስላል? ይህ ዘገባ በሚገኝበት የፌስቡክ የሀሳብ መስጫችን ሳጥን ላይ ያስፍሩልን። 

Advertisements