“ማንችስተር ሲቲ ማቆም የሚቻል ስብስብ ነው” – አርሰን ቬንገር

የአርሰናሉ አለቃ አርሰን ቬንገር ከማንችስተር ሲቲ ጋር በነበረውና ቡድናቸው በተረታበት ጨዋታ የፍፁም ቅጣት ምት ለኢትሀዱ ክለብ የሰጡትን ማይክል ኦሊቨርን በተቹበት መግለጫ ሲቲን ማቆም የሚቻል መሆኑን ገልፀዋል። 

የመድፈኞቹ አለቃ ቡድናቸው ባሳለፍነው ወር መጨረሻ ላይ በፔፕ ጋርዲዮላው ስብስብ 3-1 የተረታ ሲሆን በዕለቱ ሲቲ 1-0 እየመራ በነበረበትና ጨዋታው በተጋጋለበት ወቅት ለሲቲ የተሰጠው አከራካሪ ፍፁም ቅጣት ምት የጋርዲዮላ ስብስብ መሪነቱን እንዲያሰፋ ሲያደርገው ቬንገርን እና ቡድናቸውን ያስቆጣ ክስተት ነበር።  

ከዚህ ጋር በተያያዘም የኢትሀዱን ስብስብ ማቆም ከባድ ስለመሆኑ ጥያቄ የቀረበላቸው ቬንገር ቡድናቸው ከጨዋታው የሆነ ውጤት ይዞ መውጣት እንደነበረበት ገልፀው ለሽንፈቱም የዳኛ ውሳኔን ተጠያቂ አድርገዋል።  

ቬንገር ሲናገሩም “እንደማስበው ሲቲ ጥሩ ስብስብ ነው። ነገርግን የማይቆሙ ናቸው ማለት አይደለም። ይቆጠራል ተብሎ የተጠበቀውን የግብ ምጣኔ ብትመለከቱ የእነሱ 0.7 በመቶ እና ለእኛ ደግሞ 0.6 በመቶ ነበር። 

“በጣም እፍንፍን ያለ ጨዋታ ነበር። እነሱ በጣም ትንሽ ከእኛ በአንድ ብቻ ብልጫ ያለው ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ነው ያደረጉት። 

“በአጠቃላይ እንደማስበው በጎሉ በጣም ተቀጥተናል። 2-1 እየተመራን በነበርንበት ወቅት ጨዋታው ውስጥ ነበረን። እነሱ ጥሩ ስብስብ መሆናቸውን አልክድም። ነገርግን ማቆም የማይቻል ስብስብ አይደለም። 

“የጨዋታው ዳኛ በጨዋታው ውጤት ላይ ያልተገባ ነገር ለመፍጠር ትልቅ አቅም ነበረው። ሰዎች በጨዋታው ላይ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ሁሌም መገመት ይፈልጋሉ። እኔ ከእናንተ በላይ ላላውቅም ወይም ደግሞ ላውቅ እችል ይሆናል። 

“ነገርግን በአሁን ሰአት አንድ ቡድን አድርጎታል።” ሲሉ የሲቲን ጥንካሬ አውስተው ለቡድናቸው ሽንፈት ግን ከጋርዲዮላ ስብስብ ጥንካሬ ይልቅ የዕለቱን ዳኛ ተጠያቂ ለማድረግ ጥረት ሲያደርጉ ታይተዋል። 

በዚህ ሰአት ሲቲ በስምንት ነጥቦች ብልጫ የፕሪምየር ሊጉ ሰንጠረዥን ከላይ ሆኖ እየመራ የሚገኝ ሲሆን ከአርሰናልም የ 12 ነጥቦች ብልጫን ይዟል።

Advertisements